
ከ 8 ሰአት በፊት
ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በጥይት ተደብድበው የተገደሉት የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ ግድያቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎችን እና የህክምናውን ማኅበረሰብ አስደንግጧል።
“በስንት ዘመን አንዴ የሚፈጠር ልጅ ነው” ሲሉ ዶ/ር አንዱዓለምን የሚገልፆቸው አብሮ አደጋቸው እና የሙያ አጋራቸው፤ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ሦስት ዩኒቨርስቲዎችን ባዳረሰው የሕክምና ትምህርታቸው ተሸላሚ እንደነበሩ ያነሳሉ።
“በዘመን እና በጊዜ መሀል ብቅ ከሚሉ ዓለም አቀፍ ጭንቅላቶች አንዱ ነው” ሲሉ የሚገልፆቸው ሌላ የቅርብ ጓደኛቸው፤ ምድር ላይ ከኖሩበት 37 ዓመታት 26ቱን ትምህርት ላይ ማሳለፋቸውን ገልፀዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዶ/ር አንዱዓለም ወዳጆች እና ባልደረቦች ከግላዊ ሰብዕናቸው ጀምሮ አንቱታን ያተረፉ ሐኪም እንደሆኑ ይመሰክራሉ።
“ሕክምና ማንን ይመስላል ከተባለ ዶ/ር አንዱዓለምን ነው የሚመስለው” ሲሉም የሙያቸው ቁንጮ እንደሆኑ የሚያሰምሩ አንድ አብሮ አደጋቸው እና የሙያ አጋራቸው፤ በሁሉም ዘርፍ የተካኑ ነበር ይላሉ።
“ክፉ የማይወጣው፤ ታካሚዎቹን በሙሉ በእንክብካቤ የሚያክም” ሲሉ ሰብዓዊነታቸውን የሚገልፁት ወዳጃቸው “ታካሚዎችን በመንከባከብ፤ በማከም ብቻ ሳይሆን አንድ ሐኪም ከዕውቀት ባለፈ ታካሚዎችን የሚይዝበት መንገድ ምን ይመስላል ከተባለ ዶ/ር አንዱዓለምን ነው የሚመስለው” ብለዋል።
ዶ/ር እንዱዓለም ዳኜ በኢትዮጵያ የላቀ የካንሰር ቀዶ ሕክምና ማዕከል ማቋቋም ህልማቸው እንደነበር የጥበበ ጊዮን ሆስፒታል ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር የሺጌታ ገላው ተናግረዋል።
በካንሰር ለሚሰቃዩ ሕሙማን “ጥራት ያለው ሕክምና ከሰብዓዊ ግልጋሎት ጋር” መስጠት የሚችል ማዕከል በማቋቋም ከሕክምና ባለፈ ለታካሚዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ተስፋ፣ ድጋፍ እና ሰብዓዊ ክብር እንዲያገኙ ሩቅ አልመው በቅርብ መቅረታቸውን ጠቁመዋል።
“ካለው ሰብዕና፣ ከሚሰጠው አገልግሎት እና ካለው ተቀባይነት አንፃር” ግድያው እንደረበሻቸው ያልደበቁ ሌላ ባልደረባቸው፤ ግድያውን “የሙያን ድንበር የጣሰ” ብለውታል።
“ከባህሪ እስከ እውቀት” ተክነዋል የተባሉት ሐኪም ቅዳሜ ጥር 24/2017 ዓ.ም. ከባሕር ዳር ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቆሼ በተባለ አካባቢ ደረታቸውን በጥይት ተመተው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ግድያው ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል።
“[ሞትን] እሱ ላይ የምጠብቀው አልነበረም። ምናልባት ብዙዎቻችን ካለቅን በኋላ፤ መጨረሻ ላይ ለሞት ይታጫል ብለን የምናስበው ሰው በእንደዚህ ዓይነት አደጋ መሞቱ. . .” አስደንጋጭ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር አንዱዓለም በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ስር የሚገኘው ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጉበት፣ የቆሽት ሰብ እና የሃሞት ከረጢት ስፔሻሊት ሐኪም፣ ተመራማሪ እንዲሁም መምህር ነበሩ።
በዩኒቨርስቲው ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አንዷለም ዳኜ የጉበት፣ የሀሞት ከረጢት እና የቆሽት ሰብ ስፔሻላይዜሽን ትምሕርታቸውን ባለፈው ዓመት ነበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያጠናቀቁት።
በባሕር ዳር ከተማ በትርፍ ሰዓት ከሚሠሩበት አፊላስ ሆስፒታል ሥራቸውን ጨርሰው ከከተማ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው (የሆስፒታሉ ባለሞያዎች መኖሪያ) እየተመለሱ ሳለ ነበር አመሻሽ 12፡30 አካባቢ የተገደሉት።
- ጂቡቲ በአፋር ክልል በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 8 ሰዎች ሲገደሉ፤ ሌሎች 6 ሰዎች ቆሰሉ3 የካቲት 2025
- የምታጌጥበትን ወርቅ ሸጣ የኦቲዝም ማዕከል የከፈተችው እናት3 የካቲት 2025
- የቀን ሠራተኛው ኢትዮጵያዊ በዱባይ የፋሽን ሞዴል እንዲሆን በር የከፈተለት አስደናቂ አጋጣሚ2 የካቲት 2025
ዶ/ር አንዱዓለም ከመገደላቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሌላ ሐኪም ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ማምለጣቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የታጠቀ እና “ሲቪል” የለበሰ ግለሰብ ወደ መንገድ ገብቶ ሐኪሙን ሊያስቆማቸው ሲሞክር በድንጋጤ ማምለጣቸውን አንድ የሙያ አጋራቸው ተናግረዋል።
“አንገቱን ቀርቅሮ ነዳጁን ተጭኖ መኪናዋን ነዳት። መኪናዋ በሦስት ጥይት ተመታች። እንደ አጋጣሚ ሆኖ [ሐኪሙ] አልተመታም። እንደዚያ ሆኖ አመለጠ” ብለዋል።
ይህ በሆነ በደቂቃዎች ልዩነት አካባቢው ላይ የደረሱት ዶ/ር አንዱዓለም ማንነታው ባልታወቁ ታጣቂዎች እንደተገደሉ የልጅነት ጓደኛቸው እና የሥራ ባልደረባቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
“የቤት መኪና ይዞ የሚንቀሳቀስ ማንም የለም። በዚያች መስመር የቤት መኪና ይዘው የሚሄዱት ሐኪሞች ናቸው” የሚሉት ግለሰቡ፤ ጥቃቱ ግን ዝርፊያ እንዳልነበር ተናግረዋል።
“የተወሰደ ነገር የለም። ስልኩም እዚያው ነው የተገኘው። ምንም የተዘረፈ ነገር የለም” ያሉት የሟች ጓደኛ፤ ጥቃቱ ዶ/ር አንዱዓለም ላይ ያነጣጠረ ነው ለማለት እንደሚቸገሩ ጠቁመዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ሥራ ኃላፊ ዶ/ር አንዱዓለም ያሽከረክሩት የነበረው መኪና እና ንብረታቸው ባለመዘረፉ ጥቃቱ እሳቸው ላይ ያነጣጠረ ነው ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
‘ግድያው የተቀነባበረ ነው’ ብለው የሚያምኑት የሥራ ኃላፊው “ቀጥታ ረሽነውት ነው የሄዱት። ሞባይሉ አልተነካ፤ መኪናው አልተነካ፤ ጥለውት ነው የሄዱት” በማለት ግድያው ተራ ግድያ አይደለም ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ከዚህ ቀደም የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ላይ በሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ ዝርፊያ እና ዛቻ “የደኅንነት ዋስትና” በመጠየቅ ለቀናት ሥራ እንዳቆሙ መዘገቡ ይታወሳል።
ከሳምንታት በፊትም የሆስፒታሉ የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ ሆስፒታሉ ውስጥ መገደላቸውን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
ለሁለተኛ ጊዜ የሆነው በዶ/ር አንዱዓለም ላይ የተፈጸመው ግድያ በሕክምና ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ጭንቀት እና ድንጋጤ እንደፈጠረ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
“የሚችል ሰው ጓዙን ጠቅልሎ ከዚያ ጊቢ ለመውጣት እያሰበ ነው። ለመሥራት ምንም አይነት ዋስትና የለም። የሆነ ነገር ሲፈፀምም የሚደርስ አካል የለም። ከተፈጸመ በኋላም አጣርቶ ፍትሕ የሚሰጥ የለም። በመሀል የሕክምና ባለሙያው ነው እየተጎዳ ያለው” በማለት አንድ ሐኪም ድባቡን ተናግረዋል።
ሌላ የዩኒቨርስቲው ሠራተኛ በበኩላቸው “ተረጋግተው የሕክምና አገልግሎት እንዳይሰጡ እየተደረገ ነው” ሲሉ በሆስፒታሉ ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ተደጋጋሚ ጥቃት ውጤት ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ያለው ግጭት እና የፀጥታ ሁኔታ ዳፋ ተደርጎ የታው የዶ/ር አንዱዓለም ግድያ፤ የክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ለሕክምና ባለሙያዎች መጠቃት “ክፍተት” እንደፈጠረ አንድ ሐኪም ጠቁመዋል።
ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባት የሆኑት ዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ የቀብር ሥነ ሥርዓት እሁድ ጥር 25/2017 ዓ.ም. በባሕር ዳር መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
እስካሁን ከዶክተሩ ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠረም ሆነ የተያዘ ሰው የለም። የባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ ግድያው “ባልታወቁ ኃይሎች” እንደተፈፀመ በመግለጽ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አሳውቋል።