
ከ 5 ሰአት በፊት
የአተነፋፈሳችን ሁኔታ በጤናች ላይ የራሱ የሆነ ውጤት አለው። የተለያዩ የአተነፋፈስ ዘዴዎችን በመጠቀም በሰው ልጆች ጤና ላይ ለውጥ ማምጣት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የታወቀ ነው።
ዘመናዊው ህክምናም የተለያዩ ዓይነት የአተነፋፈስ መንገዶችን በመጠቀም በሰዎች ጤና ላይ አውንታዊ ለውጥ ለማምጣት ጥቅም ላይ ይውላል።
የምድራችን ቀደምት ማኅበረሰቦች ባህል አተነፋፈስ ከአእምሮ እና ከሰውነት ጋር ያለውን ትስስር ተገንዝበው አካላዊ እና መንፈሳዊ ጤናን ለመጠበቅ ጥቅም ላይ ሲያውሉት ቆይተዋል።
‘ብሪስቶል ብሪዝወርክ’ የአተነፋፈስ ትምህርት የሚሰጥበት ተቋም ነው። በተቋሙ የምትሠራው ሊንዚ ማርዮት እንደምትለው ምዕራቡ ዓለም ስለ አተነፋፈስ ለማወቅ ጊዜ ወስዷል።
“ምን ያህል ምግብ እና መጠጥ መውሰድ እንዳለብን እንማራለን፤ ስለአተነፋፈስ ግን ማንም አያስተምረንም” ትላለች።
ልጆች እንደተወለዱ ሆዳቸው እስከሚሞላ ድረስ ትንፋሽ ሲስቡ ይስተዋላል።
“ሆኖም ግን ከፍ እያልን ስንሄድ ስሜታችንን እንድናምቅ ይነገረናል” ትላለች ሊንዚ።
“ተቀባይነት ለማግኘት ራሳችንን እንድናርም ይነገረናል። ስሜታችንን ስናምቅ በጣም አቅማችንን ይወስደዋል። ላለማልቀስ መሞከር እንዴት እንደሚከብድ አስቡት። ደረት ላይ የሚፈጥረው ጭንቀት ከባድ ነው” ስትል ሊንዚ ታስረዳለች።
ሰዎች ስሜታቸውን አውጥተው እንዲያብላሉ ስለማይፈቀድላቸው ጫና ውስጥ እንደሚኖሩ ትናገራለች።
ጌታኖ አሪና ላለፉት 18 ወራት አተነፋፈሱን አስተካክሏል።
“መጀመሪያ ትምህርቱን ስጀምር ሰውነቴን ነጻ ማድረግ ነው የተማርኩት። ህመሙም አብሮ ጠፋ” ይላል።
- ከቢቢሲ አማርኛ ዜና እና ታሪኮች በቀጥታ እንዲላክልዎ የዋትስአፕ ቻናላችን አባል ይሁኑ5 ታህሳስ 2024
- በስተርጅና የልጅ አባት መሆን ያሉት አደጋዎች ምንድን ናቸው?18 ጥቅምት 2024
- ለሞት አደጋ የሚያጋልጠው ‘ቢቢኤል’ የተባለው የመቀመጫ መጠን የሚያሳድገው ሕክምና29 መስከረም 2024

የአተነፋፈስ ትምህርቱ አምቆት የቆየውን ስሜት እንዲለቅ እንዳስቻለው ይናገራል።
“መተንፈስ በተፈጥሮ የሚሰጠውን ጥቅም እንዲሰጥ መፍቀድ ነው። ይህም ስለ ሰውነት እና አእምሮ የተሻለ ግንዛቤ ይሰጣል” ይላል።
የታመቁ ስሜቶችን ማለፍ ከተቻለ በቀጣይ ነገሮችን በግልጽ መረዳት እና መመልከት እንደሚመጣ ይናገራል።
የአተነፋፈስ ትምህርት የምትሰጠው ዴቦራ ማዲሰን አተነፋፈስን ማስተካከል ጭንቀት፣ ሐዘን፣ ድባቴ እና ህመም ያስወግዳል።
“በጣም አስደናቂ አቅም ነው ያለው። ተማሪዎቼ ላይ የማየውን ለውጥ ማመን አንዳንዴ ይከብደኛል” ትላለች።
የአእምሮ ጤና ምርምር እና ሕክምና የሆነው ኒውሮሳይንስ አተነፋፈስ ያለውን ዋጋ እያረጋጠ ነው።
“መተንፈስ አእምሮን ያረጋጋል። የሚያስብ አእምሮን ገታ አድርጎ ስሜትን ለመረዳት ክፍተት ይሰጣል” ትላለች መምህርቷ።
አተነፋፈስ ሲስተካከል ከልጅነት አንስቶ የገጠሙ አሳዛኝ ክስተቶችን በማስታወስ መፍትሔ ለመስጠት ይረዳል።
ቪክቶሪያን ኮክሰን የአተነፋፈስ ትምህርትን “ሐሳቤን አልፌ ውስጣዊ አእምሮዬን እንድረዳ አግዞኛል” ትላለች።
“በቤተሰቤ ያለ ሐዘን እያሳደረብኝ ከነበረው ጫና እንድላቀቅ አድርጓል” ስትልም ታክላለች።
የአተነፋፈስ ሕክምና ታዋቂ እየሆነ ነው። ጭንቀት እና ድንጋጤ ሲገጥም በቤት ውስጥ አተነፋፈስን በማስተካከል ማስወገድ በባለሙያዎች ይመከራል።
“ተማሪዎቻችን ቤታቸው ሳሉም እንዲተነፍሱ እናበረታታለን። በሕይወት የሚገጥመውን ለመወጣት እና ራሳቸውን ለማከም ይጠቀሙበታል። በውስጥ ሁሉንም አምቆ ከማቆየት የተሻለ ነው” ትላለች አስተማሪዋ።
ተማሪዋም “ራሴን ያገኘሁበት እና ያከምኩበት መንገድ ነው” ስትል ትገልጸዋለች።
ብዙዎች በሕይወት አጣብቂኝ ውስጥ ሲሆኑ ከመምህርቷ ምክር ይጠይቃሉ።
ከትምህርቱ በኋላ በሕይወታቸው በሰላም ወደፊት ሲቀጥሉ፣ አዲስ ሥራ እና የፍቅር ግንኙነት ሲጀምሩ አያለሁ ትላለች።
ተማሪዋ ደግሞ “በሕይወቴ ወደ የት መሄድ እንደምፈልግ ያሳየኛል። በጣም ሕይወቴን የለወጠ ታላቅ ኃይል ያለው ነገር ነው” ትላለች።