ዴልካት ኤዴንጎ

ከ 3 ሰአት በፊት

ታዋቂው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሙዚቀኛ አማጺያኑ በተቆጣጠሯት ጎማ ከተማ የሙዚቃ ቪዲዮ ቀረጻ እያከናወነ ባለበት ወቅት ተገደለ።

ሙዚቀኛው ኤም23 የተሰኙት የኮንጎ አማጺያን ከተማዋን መቆጣጠራቸውን የሚያወግዝ ዘፈን በቅርቡ ለቅቆ ነበር።

በመድረክ ስሙ ዴልካት ኤዴንጎ በመባል የሚጠራው ዴልፊን ካቴምቦ ቪኒስዋኪ አስክሬን ሐሙስ ዕለት ጎዳና ላይ ተገኝቷል። ጭንቅላቱም በከፊል በደም መሸፈኑም ታይቷል።

ያልተረጋገጡ ዘገባዎች አርቲስቱ የተገደለው በጥይት መሆኑን ሪፖርት አድርገዋል።

ሙዚቀኛው በግጭቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ወገኖች በመተቸት ይታወቃል።

በፖለቲካዊ መልዕክቶቹ በዲሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት ጥርስ ውስጥ የገባው ሙዚቀኛው በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጎ ነበር።

አማጺያኑ ባለፈው ወር ጎማን በተቆጣጠሩበት ወቅት ሙዚቀኛው በከተማዋ በእስር ላይ ነበር።

አማጺያኑ ከተማዋን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ሲያመልጡ ሙዚቀኛውም ወጣ።

በማዕድን የበለጸገችው ምስራቃዊቷ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ለመቆጣጠር የተለያዩ ኃይሎች እየተፋለሙ ይገኛሉ።

ከሙዚቀኛው ግድያ ጀርባ ማን እንዳለ ግልጽ አይደለም።

የመንግሥት ቃል አቀባይ ፓትሪክ ሙያዬ የሙዚቀኛውን ግድያ “አጸያፊ ተግባር” ሲሉ ፈርጀው “ፍትህ ይሰፍናል” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

ቃል አቀባዩ ለሙዚቀኛው ግድያ ኤም23ን ተጠያቂ አድርገዋል።

ኤም23 በበኩሉ ጣቱን ወደ መንግሥት ኃይሎች ከመቀሰር በተጨማሪ መሳሪያቸውንም እንዲያስረክቡ ጠይቋል።

በማህበራዊ ድረገጾች ላይ የተለቀቁ ቪዲዮዎች በሰሜን ጎማ ኪሊጂዌ አካባቢ ጎዳና ላይ የሙዚቀኛው አስከሬን ተንጋሎ አሳይተዋል። ኤዲንጎ ለቪዲዮው ወታደራዊ መለዮ ለብሶ እንደነበር የተናገሩ የአይን እማኞች ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ መሞቱን ገልጸዋል።

የኮንጎ የስነ ጥበብ እና ባህል ሚኒስቴር ድርጊቱን “ግድያ” ሲል ገልጾታል።

“በሙዚቃው ለመላው ትውልድ ምኞትን እና ተስፋን የፈነጠቀ ቁርጠኛ ድምጽ ነበር” ሲል ሚኒስቴሩ በኤክስ ገጹ አስፍሯል።

ኤዴንጎ በአገሪቱ ያሉ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማህበረሰቡ መሳሪያ እንዲያነሱ አነሳሰቷል የሚል ክስ ባለፈው ዓመት ከታሰረ በኋላ የፍርድ ሂደት እየጠበቀ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2012 የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ትሺሴኪዲን በመዝለፍ እንዲሁም ፕሬዚዳንቱ የገቡትን ቃል አልፈጸሙም በሚል “ሃሰተኛ ዜናዎችን አሰራጭቷል” በሚል ተከስሶ ነበር።

በነዚህ ክሶች 10 ዓመት ተፈርዶበት የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን በነጻ ተለቅቋል።

የኤዴንጎን ሞት በመቃወም እንዲሁም ፍትህን ለመጠየቅ በተወለደበት በሰሜናዊ ኪቩ በምትገኘው ቤኒ ከተማ በርካቶች የአደባባይ ላይ ተቃውሞ አድርገዋል።

ግድያው የተፈጸመው በሩዋንዳ የሚደገፈው ኤም23 ታጣቂ ቡድን በአገሪቱ በተደረገ ከፍተኛ ጦርነት ጎማን መቆጠጣሩን ተከትሎ ከፍተኛ ውጥረት በነገሰበት ወቅት ነው።

በቅርቡ በአገሪቱ በተፈጠሩ ግጭቶች 2 ሺህ 900 ሰዎች ሲገደሉ ወደ 700 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት የቀጣናው አገራት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ያላፈራ ሲሆን አማጽያኑ ወደ ደቡባዊ ኪቩ መዲና ቡካቩ እየገሰገሱ ይገኛሉ።