ዶናልድ ትራምፕ

16 የካቲት 2025, 07:13 EAT

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ፕሮጀክት 2025 የተሰኘው ቀኝ አክራሪዎች አስተዳደራቸው ሊከተለው ይገባል ብለው የተመኙት እና የነደፉት ፍኖተ ካርታ እየተነሳ ይገኛል።

ዘጠኝ መቶ ገጾች ያሉት ይህ ፍኖተ ካርታ የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን አስፍቶ የሚያጠናክር እና ወግ አጥባቂ ማኅበራዊ ራዕይን ያነገበ ነው።

ፕሮጀክት 2025 የሚያቀርባቸው ሃሳቦች ጽንፈኛ ናቸው በሚል በርካታ ትችቶች መቅረባቸውን ተከትሎ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በተደጋጋሚ ውድቅ ሲያደርጉት ተሰምተዋል።

ሆኖም ፕሮጀክት 2025ን ከጻፉት በርካቶቹ በትራምፕ አስተዳደር ቁልፍ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተሹመዋል። በተጨማሪም ትራምፕ ያስተላለፏቸው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞች ይህንን ፍኖተ ካርታ በጥብቅ የሚከተሉ ሆነው ታይተዋል።

ትራምፕ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት አገሪቷን እንዴት ሊያስተዳድሩ ይችላሉ የሚለውን ሊያሳይ የሚችለው የፕሮጀክት 2025 ራዕይ የሚከተለውን ይመስላል።

ፕሮጀክት 2025 እንዴት ተጠነሰሰ?

‘ፕሮጀክት 2025’ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያለው እና በቀኝ አክራሪው ‘ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን’ በተሰኘው ከ100 በላይ ወግ አጥባቂ ድርጅቶችን የተሳተፉበት ተቋም የተነደፈ ነው።

ተቋሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ለወደፊቱ የሪፐብሊካን አስተዳደር ፖሊሲ ዕቅዶችን የነደፈው በአውሮፓውያኑ 1981 ሮናልድ ሬጋን የፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን ሊረከቡ ሲሉ ነው።

በቀጣዮቹ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ላይ ተመሳሳይ ሰነዶችን ያዘጋጀ ሲሆን፣ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ባሸነፉበት በአውሮፓውያኑ 2016 በተመሳሳይ ይህንኑ አድርጓል።

የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩዎች ፕሬዚዳንት ሆነው ወደ ሥልጣን በሚመጡበት ወቅት ተቋሙ ተጽእኖው ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ማየት ይቻላል።

የትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን አንድ ዓመት ሲቀረው ሁለት ሦስተኛ የሚሆነውን ሃሳባቸው በአስተዳደሩ ተግባራዊ መደረጉን ተቋሙ አስታውቆ ነበር።

ተቋሙ ለአሁኑ ፕሬዚዳንት ያወጣቸውን ፖሊሶች ይፋ ያደረገው በአውሮፓውያኑ 2023 ቢሆንም ብዙም ትኩረት አልተደረገበት ነበር። ነገር ግን የአሜሪካ የምርጫ ቅስቀሳን ተከትሎ ፕሮጀክት 2025 መወዛገቢያ ሆነ።

የዲሞክራቲክ ፖለቲከኞች ፕሮጀክት 2025ን ለማስቆም ግብረ ኃይል ከማቋቋም በተጨማሪ ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን የተሰኘው ተቋም እንቅስቃሴዎችን የውስጥ መረጃዎች ለመሰብሰብ የሚያስችል የጥቆማ የስልክ መስመር አዘጋጅተው ነበር።

የካማላ ሐሪስ የምርጫ ዘመቻ ቡድንም ፕሮጀክት 2025ን በቃለ መጠይቆች እና በንግግሮቻቸው ላይ በተደጋጋሚ ይጠቅሱት ነበር።

ትራምፕ ከሐምሌ 2024 በኋላ ሰነዱን ወደ ጎን ገሸሽ ሲያደርጉት ተሰምተዋል።

“ስለ ፕሮጀክት 2025 ምንም የማውቀው ነገር የለም” ሲሉ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ትሩዝ ሶሻል ላይ አውጥተዋል። “ከሚናገሯቸው አንዳንድ ጉዳዮች ጋር አልስማማም። አንዳንዶቹ ጉዳዮች አስገራሚ እና አጸያፊ ናቸው” ብለውም ነበር።

ፕሮጀክት 2025ን ከነደፉት መካከል አብዛኞቹ በትራምፕ የቀድሞ አስተዳደር ወቅት አማካሪ የነበሩ ይገኙበታል። ከእነዚህም መካከል የሠራተኞች አስተዳደር የጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ፖል ዳንስ ይገኙበታል። ፖል በኋላ ፕሮጀክት 2015ን መተዋቸው ተነግሯል።

ነገር ግን ሌሎች የፕሮጀክት 2025 ደራሲዎች በአዲሱ የትራምፕ አስተዳደር አቀባበል ተደርጓላቸዋል።

ራሳቸውን የክርስቲያን ብሔርተኛ ብለው የሚጠሩት ራስል ቫውት በሰነዱ ውስጥ ቁልፍ የሚባለውን ምዕራፍ ጽፈዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ 6.75 ትሪሊዮን የሚሆነውን የፌደራል በጀት የሚያስተዳድረውን የበጀት መምሪያ ቢሮ እንዲመሩ መሾማቸው በሴኔቱ ተረጋግጧል።

በአንድ ዲሞክራት ዘንድ የፕሮጀክት 2025 ዋና መሐንዲስ የተባሉት ራስል ቫውት የትራምፕ አስተዳደር መዘጋት አለበት የሚለው የሸማቾች የፋይናንስ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ሆነው በተጨማሪ ተሹመዋል።

ሌሎች ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በዕጩነት የቀረቡ የ2025 ፕሮጀክት አዘጋጆች መካከል የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ፣ የፌደራል ኮሙኒኬሽን ኮሚሽንን እንዲመሩ የተመረጡት ብሬንዳን ካር ይገኙበታል።

በተጨማሪ ቶም ሃማን በትራምፕ “የድንበር ንጉሥነት”፣ ፓውል አትኪንስ ‘ሴኩሪቲስ ኤንድ ኤክቼንጅስ’ የተሰኘ ኮሚሽን እንዲሁም በንግድ አማካሪነት ፒተር ናቫሮ ዕጩ ሆነዋል።

ከ100 በላይ ወግ አጥባቂ ድርጅቶች ለሰነዱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን አስታውቋል።

ሰነዱ አራት የፖሊሲውን ዋነኛ ዓላማዎችን አስቀምጧል። ቤተሰብን የአሜሪካ ማኅበረሰብ ሕይወት ማዕከል አድርጎ መመለስ፣ የግዛቶችን አስተዳደሮች ማፍረስ፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንዲሁም ዳር ድንበር ማስጠበቅ እና አምላክ ለሰው ልጅ በነጻነት የመኖር የሰጠውን ግለሰባዊ መብት ማስከበር የሚሉ ናቸው።

በፍኖተ ካርታው ላይ የሰፈሩት ሃሳቦች ለትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞች መሠረት መሆናቸው ተጠቅሷል።

የመንግሥት አወቃቀር

ፕሮጀክት 2025 እንደ ፍትህ ቢሮ ቤት ያሉ ገለልተኛ መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ መላው የፌደራል መሥሪያ ቤቶች በቀጥታ በፕሬዚዳንቱ ቁጥጥር ስር እንዲቀመጥ ሃሳብ አቅርቧል። ይህ አወዛጋቢ ሃሳብ ሁሉንም አሃዳዊ በሆነ መልኩ እንዲፈጸም ሊያደርግ ያቀደ ነው።

ፕሬዚዳንቱ በተለያዩ መስኮች በቀጥታ ፖሊሲዎችን እንዲተገብሩ እና የውሳኔ ሂደቶችን እንዲቀላጥፉ ያደርጋቸዋል። በተጨማሪም በሺዎች ለሚቆጠሩ የመንግሥት ሠራተኞች የተሰጣቸውን የሥራ ጥበቃ እንዲነሳ ሃሳብ የሚያቀርብ ሲሆን ከዚያም በፖለቲካ ተሿሚዎች ሊተኩ ይችላሉ።

ዶናልድ ትራምፕ ከሥራቸው ለመልቀቅ ለሚስማሙ ሁሉም የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የስምንት ወር ደመወዛቸውን በቅርቡ እሰጣለሁ ማለታቸው ይታወሳል። ትራምፕ የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን መጠን ለመቀነስ በያዙት ዕቅድ ነው ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት።

ፍኖተ ካርታው የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይን) “የተለጠጠ፣ እብሪተኛ እና ሕገወጥ ድርጅት” የሚል ስያሜ ሰጥቶታል።

ቢሮውን ጨምሮ የተለያዩ ኤጀንሲዎች እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴር ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ ይጠይቃል። ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ብዙም ሳይቆዩ የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ጥበቃን ማስወገድ እንዲሁም የፌደራል ወጪዎችን ለማቆም ተንቀሳቅሰዋል።

ቢሊየነሩ ኢሎን መስክ በፕሬዝዳንት ትራምፕ አዲስ መሥሪያ ቤት እንዲመራ ከተሾመ በኋላ በአሜሪካ በርካታ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ሲታመሱ ሰንብተዋል።

እሱ የሚመራው መሥሪያ ቤት በእንግሊዝኛው ‘ዶጅ’ በሚል ምህጻር የሚታወቅ ሲሆን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ወጪ መቀነስ እና ሥራቸውን የሚያሳልጡበት መንገድ የማፈላለግ ሚና እንዲወጣ ይጠበቅበታል።

ከዚህ ባሻገር እጅግ ተለጥጠዋል ያላቸውን የፌደራል መንግሥቱን መሥሪያ ቤቶች እንዲታጠፉ ወይም ደግሞ እንዲያንሱ ይሠራል።

ይህን ለማሳካት በበርካታ ፌዴራል መሥሪያ ቤቶች በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞችን እየቀነሰ ይገኛል። ትራምፕ የፌደራሉን በጀት እንዲሁም ሠራተኞች ለመቀነስ እየሄዱበት ያለው ሂደት ከፕሮጀክት 2025 ግቦች ጋር የተስማማ ነው።

ጽንስ ማቋረጥ እና ቤተሰብ

ፕሮጀክት 2025 ጽንስ ማቋረጥን በተመለከተ 200 ያህል ጊዜ በሰነዱ ጠቅሷል። እነዚህም በርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮችን ያስነሱ ናቸው።

ሰነዱ በአገር አቀፍ ደረጃ ጽንስ ማቋረጥ እንዲታገድ በቀጥታ አይጠይቅም። እንዲሁም ትራምፕ እንዲህ ያለውን ሕግ እንደማይፈርሙም ተናግረዋል።

ሆኖም ጽንስ ለማቋረጥ የሚጠቅመውን ሜፌፕሪስቶን የተባለውን እንክብል ከገበያ እንዲወገድ በግልጽ አስፍሯል።

ሰነዱ ጽንስ ማቋረጥን በተመለከተ አዳዲስ የመረጃ አሰባሰብ ጥረቶችን አቅርቧል።በዚህም መሠረት በአጠቃላይ የጤና እና ሰብዓዊ አገልግሎት መሥሪያ ቤቶች “መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያላቸው እንዲሁም በማኅበራዊ ሳይንስ የተደገፈ የጋብቻ እና የቤተሰብ ትርጉም” እንዲኖረው ይጠቁማል።

ትራምፕ በአንጻሩ የጽንስ ማቋረጥ ሕጎች በአብዛኛው ለተለያዩ ግዛቶች መተው አለባቸው ብለው ነበር።

ሆኖም የጤና ሚኒስትሩ ሮበርት ኬኔዲ ጁኒየር የሜፊፕሪስቶን እንክብል ደኅንነትን እንዲሁም የመድኃኒቱን ቁጥጥርን በተመለከተ እንዲመረምሩ በትራምፕ እንደታዘዙ ተናግረዋል።

ትራምፕ የፌደራል በጀት ጽንስ ለማቋረጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ያስተላለፉ ሲሆን፣ ይህም በፕሮጀክት 2025 ሰፍሯል።

በድንበር ላይ የሚገኙ ስደተኞች

ኢሚግሬሽን

ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት አሜሪካ እና ሜክሲኮ በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ ለሚገነባው ግዙፍ አጥር ከፍተኛ ገንዘብ መመደባቸው ይታወሳል።

ይህም በዚህ ፍኖተ ካርታ ላይ የተጠቀሰ ነው። ነገር ግን ትራምፕ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞች ከአገር ለማባረር በተደጋጋሚ የሚናገሩት ጉዳይ በዚህ ሰነድ አልተካተተም።

ነገር ግን ከኢሚግሬሸን ጋር በተገናኘ የሀገር ውስጥ ደኅንነት የሚባለውን መሥሪያ ቤት ማፍረስን እና ጠንካራ የድንበር ማስፈጸሚያ ክፍል እንዲቋቋም ይጠይቃል።

በተጨማሪም በወንጀል እና በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂ ለሆኑ ሰዎች የሚሰጠውን ቪዛ ማስቀረት እና ለስደተኞች የሚደረገውን የቪዛ ክፍያ መጨመርን ፍኖተ ካርታው አካቷል።

ንግድ

ፍኖተ ካርታው በታሪፍ ላይ ሁለት ተፎካካሪ ጉዳዮችን አስቀምጧል። አንደኛው ነጻ ንግድን ማስፋፋት ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ታሪፍን መጫን የሚመለከት ነው።

ትራምፕ በካናዳ፣ በሜክሲኮ እና በቻይና ላይ ታሪፍን በመጫን የትኛውን ፖሊሲ እንደሚከተሉ አሳይተዋል።

ትምህርት እና ብዝኃነት

ትራምፕ ሥልጣን እንደያዙ ታሪካዊ ኢፍትሃዊነትን ለማስተካካል የተዘረጉ እንደ ብዝኃነት፣ እኩልነት እና አካታችነት የተሰኙ ፕሮግራሞችን አጥፈዋል። እንዲሁም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለሁለት ጾታዎች ብቻ እውቅና እንዲሰጡ ውሳኔ አስተላልፈዋል።

ይህ የትራምፕ እርምጃዎች ከፕሮጀክት 2025 ሰነድ ጋር በእጅጉ የሚጣጣም ነው።

ፍኖተ ካርታው ትምህርትን በተመለከተ ለሃይማኖታዊ እና ለግል ትምህርት ቤቶች ድጎማ ማድረግን ይጠቅሳል።

ይህ ደግሞ ትራምፕ ባስተላለፉት የትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ላይ ተንጸባርቋል። ትራምፕ ሌላኛው የሚደግፉት እና በሰነዱ ላይ የሰፈረው የትምህርት ሚኒስቴርን ማጠፍ ነው።

ፕሮጀክት 2025ን ለመንደፍ 22 ሚሊዮን ዶላር በጀት ወጥቶበታል።

በጀቱ ፖሊሲዎች የሚፈጸሙበትን ስልቶችንም አካቷል። ለምሳሌ ያህል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ቁልፍ ስፍራ እንዲይዙ ታማኝ የሆኑ የወግ አጥባቂ ፖለቲከኞችን ዝርዝር የያዘ የመረጃ ቋት መፍጠር እንዲሁም አዳዲስ ሠራተኞችን የማሠልጠን መርሃ ግብርን ያጠቃልላል።

ሰነዱ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ሁለት አገራትን ብቻ ይጠቅሳል፣ ሶማሊላንድ እና ጂቡቲን። “አሜሪካ በጂቡቲ ያላት ተጽእኖ ማሽቆልቆልን ለመቋቋም ሶማሊላንድን እንደ አገር ዕውቅና መስጠት” የሚል ነው።

በዚህ ከ900 በላይ ገጾች ባሉት ሰነድ ከሰሃራ በታችን የተመለከተው ክፍል ከሁለት ገጾች በታች መሆኑ አህጉሪቱ የሚሰጣት ቦታ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ተብሏል።