ማህሙድ አሊ ዩሱፍ
የምስሉ መግለጫ,ማህሙድ አሊ ዩሱፍ

15 የካቲት 2025

ተቀራራቢ ፉክክር በተካሄደበት ምርጫ የጂቡቲው ዕጩ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ስድስተኛ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።

ከኬንያው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የተቃዋሚ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ጋር ለስድስት ዙር በተካሄደ የምርጫ ሂደት የጂቡቲው ተወካይ አሸናፊ ሆነዋል።

የ60 ዓመቱ ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ለ20 ዓመታት የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሆነው እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን፣ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር መሆናቸውን ተከትሎ የሚኒስትርነት ሥልጣናቸውን ይለቃሉ።

አፋርኛ፣ ሶማሊኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ እና አረብኛ አቀላጥፈው የሚናገሩት ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ ወሳኝ በሚባለው የቀይ ባሕር የንግድ መሥመር ላይ ከሶማሊያ የባሕር ዳርቻ በመነሳት የባሕር ላይ ውንብድና የሚፈጽሙትን በመከላከል ላበረከቱት አስተዋጽኦ በአውሮፓ ኅብረት ተሸልመዋል።

ከኬንያ እና ከማዳጋስካር ከተወከሉ ዕጩዎች ጋር ለኅብረቱ ሊቀመንበርነት የተፎካከሩት ጂቡቲያዊው ዕጩ ማህሙድ ከባድ ፉክክር የገጠማቸው ከኬንያው ራይላ ኦሞሎ ኦዲንጋ ነበር።

እስከ ሦስተኛው ዙር ድምጽ አሰጣጥ ድረስ ከማዳጋስካር የተወከሉት ዕጩ ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ ዝቅተኛ ድምጽ በማምጣት በፉክክሩ ውስጥ የቆዩ ሲሆን፣ ከሦስተኛው ዙር በኋላ ወጥተዋል።

የቀሩት ማህሙድ እና ኦዲንጋ በተቀራራቢ የድምጽ ልዩነት በጂቡቲው ዕጩ መሪነት እስከ 6ኛው ዙር ድረስ ተፎካክረው የኬንያው ዕጩ ከውድድሩ በመውጣታቸው ጂቡቲያዊው ዕጩ የብዙኃኑን 33 ድምጽ አግኝተው የሊቀመንበርነቱ ፉክክር አሸናፊ ሆነዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የአህጉሪቱ ዋነኛው ተቋም ሲሆን፣ በአፍሪካ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብት እና ሌሎችን ቁልፍ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር አቅሙ ደካማ ነው በሚል ይተቻል።

በኢትዮጵያው ንጉሥ አጼ ኃይለ ሥላሴ ጥረት እና መሪነት በግንቦት 16/1955 ዓ.ም. የተመሠረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በዋናነት አፍሪካውያንን በማስተባበር በቅኝ ግዛት ስር የነበሩት የአህጉሪቱ አገራት ነጻ እንዲወጡ መርዳት ዋነኛ ዓላማው ሆኖ ለአራት አሥርት ዓመታት ያህል ሠርቷል።

በአውሮፓውያኑ 2000 ላይ የሊቢያ መሪ በነበሩት ሙአመር ጋዳፊ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከዘመኑ ጋር በሚሄድ አዲስ ድርጅት እና አወቃቀር ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲሸጋገር ያቀረቡት ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ከሁለት ዓመታት በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረትነት ተሸጋገረ።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ከተሸጋገረ በኋላ አሁን የተመረጡትን ጂቡቲያዊውን ሊቀመንበር ጨምሮ ስድስት የኮሚሽኑ ሊቀመናብርትን አስተናግዷል።

በዚህም የመጀመሪያው የኅብረቱ ሊቀመንበር አይቮሪኮስታዊው አማራ ኤሴ የነበሩ ሲሆን እሳቸውን ተከትሎም፣ ማሊያዊው አልፋ ኦማር ኮናሬ፣ ጋቦናዊው ጂያን ፒንግ፣ ደቡብ አፍሪካዊቷ ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ እና የአሁን መንበራቸውን የሚያስረክቡት ሙሳ ፋኪ ማሐማት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል።