
16 የካቲት 2025, 07:14 EAT
የ11 ዓመት ታዳጊው ዘካሪያ የሚኖረው በጋዛ ነው።
በጋዛ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ አስከሬኖችን ማየቱን ይናገራል።
በመማሪያ ክፍል ውስጥ መገኘት በነበረበት በዚህ ዕድሜው፣ ዘካሪያ በጋዛ ውስጥ ከሚገኙ ጥቂት ሆስፒታሎች በአንዱ፣ አል አቅሳ፣ በበጎ ፈቃደኝነት እየሠራ ነው።
በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ሙታን እና ቁስለኞችን ከአምቡላንሶች ወደ ሕክምና ክፍሎች ያመላልሳል።
በርካታ አምቡላንሶች በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በሚደረገው ጦርነት የተጎዱ ሰዎችን በማዕከላዊው ዲር አል ባላህ ሲያመጡ፣ ዘካሪያ አዲስ የመጡ ታካሚዎችን ለሕክምና ወደ ውስጥ ለማስገባት በጭንቅንቅ እና ግፊያ መካከል ወዲያ ወዲህ ይላል።
ከትንሽ ቆይታ በኋላ በሆስፒታሉ መተላለፊያዎች ውስጥ በተዘረጋው ክፍል እየሮጠ ወደ ድንገተኛ ክፍል ህሙማኑን ሲያደርስ ይታያል።
ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ተገድለዋል።
በሆስፒታሉ አካባቢ ውሎውን ያደረገው ዘካሪያ በርካታ አስደንጋጭ ትዕይንቶችን ተመልክቷል።
አንድ ዕለት እስራኤል የአየር ጥቃት ከፈጸመች በኋላ አንድ ልጅ ከፊት ለፊቱ በእሳት ተቃጥሎ ሲሞት ማየቱን ይናገራል።
“ቢያንስ 5,000 አስከሬኖች ሳላይ አልቀረሁም። በዓይኔ በብረቱ አይቻቸዋለሁ” ሲል ይናገራል።
ዘካሪያ ቢቢሲ ‘ጋዛ፡ ሕይወት በጦርነት ቀጠና ውስጥ’ በሚል ለሠራው ዘጋቢ ፊልም ለዘጠኝ ወራት ያህል ከተከታተላቸው ሕጻናት እና ወጣቶች መካከል አንዱ ነው ።
ይህ ዘጋቢ ፊልም የተሠራው ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ጋዛ ሰርጥ ገብተው እንዳይዘግቡ እስራኤል ክልከላ በማድረጓ የቢቢሲ ባልደረቦች ከለንደን በመሆን ጋዛ ውስጥ ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋር በትብብር በመሆን ነው።
ቀረጻውን ለማካሄድ እና ቃለ ምልልሶቹን ለመሰብሰብ በጋዛ ከሚኖሩ ሁለት የካሜራ ባለሙያዎች፤ አምጃድ አል ፋዩሚ እና ኢብራሂም አቡ ኢሻይባ ጋር በመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች፣ በኢንተርኔት በሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች እና ሞባይል ስልክ አዘውትረው ይገናኙ ነበር።
ቢቢሲ ይህንን ዘጋቢ ፊልም ለመሥራት የፈለገው በዚህ የማያባራ ጦርነት መካከል የዕለት ተዕለት ሕይወት ለጋዛ ሰዎች ምን እንደሚመስል ለማሳየት ነው።
ቀረጻውን የተጠናቀቀው ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተኩስ አቁም በተጀመረበት ዕለት ነው።
ዘጋቢ ፊልሙ በሦስት ታዳጊዎች እና አንዲት ጨቅላ ሕጻን ያላት ወጣት ሴት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።
- ከቢቢሲ አማርኛ ዜና እና ታሪኮች በቀጥታ እንዲላክልዎ የዋትስአፕ ቻናላችን አባል ይሁኑ5 ታህሳስ 2024
- የተከፋፈሉት የህወሓት አመራሮች ለፖለቲካ ግቦቻቸው “ኃይል ላለመጠቀም” መፈራረማቸው ተገለጸ14 የካቲት 2025
- ትክክለኛ የሕይወት አጋር ማግኘት እና ስኬታማ ግንኙነት መመሥረት ለምን አስቸጋሪ ሆነ?14 የካቲት 2025

በእስራኤል ጥቃት ጋዛ ውስጥ ከ48 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይናገራል።
የእስራኤል ወታደራዊ እርምጃ የጀመረው በደቡባዊ እስራኤል ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጥቃት ፈጽሞ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች ከተገደሉ እና 251 ከታገቱ በኋላ ነው።
ቀረጻው የተከናወነው የእስራኤል ጦር “የሰብዓዊ ቀጠና” ሲል በሰየመው እና ፍልስጤማውያን ለደኅንነታቸው ሲባል እንዲሄዱ በተነገራቸው ደቡባዊ እና መካከለኛው ጋዛ አካባቢ ነው።
ምንም እንኳ ይህ አካባቢ የሰብዓዊ ቀጠና ቢባልም ቢቢሲ እንዳረጋገጠው ባለፈው ዓመት ግንቦት እና በዚህ ዓመት ጥር መካከል ብቻ አካባቢው 100 ያህል ጊዜ ጥቃት ተፈጽሞበታል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በአካባቢው የሚንቀሳቀሱትን የሐማስ ተዋጊዎችን ዒላማ ማድረጉን ይገልጻል።
ቢቢሲ ሕጻናት እንዴት ምግብ እንደሚያገኙ፣ የት ለመተኛት እንደሚወስኑ እና በሕይወት ለመኖር በመሞከር ውስጥ እንዴት ቀናቸውን አንደሚያሳልፉ ለማወቅ ፈልጓል።
የ13 ዓመቱ አብዱላህ ፊልሙን ይተርካል። ከጦርነቱ በፊት በጋዛ በሚገኘው የብሪቲሽ ትምህርት ቤት የተማረ በመሆኑ ጥሩ አንግሊዘኛ ይናገራል። ትምህርቱንም ለመቀጠል የተቻለውን ሁሉ አድርጓል።
የ10 ዓመቷ ሬናድ በታላቅ እህቷ እርዳታ በቲክ ቶክ የምግብ ዝግጅት ትዕይንት ትሠራለች።
ምንም እንኳ በጦርነቱ ምክንያት የሚያስፈልጋቸውን ቅመማ ቅመሞች ሁሉ ማግኘት ባይችሉም፤ ብዙ ዓይነት ምግቦችን ያዘጋጃሉ፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተከታዮችን አፍርተዋል።
በተጨማሪም የሴት ልጅ እናት የሆነችው [ከመወለጃ ቀኗ ቀድማ ነው የወለደችው] የ24 ዓመቷ ራናን የዕለት ውሎም ዘጋቢ ፊልሙ ያስቃኛል።
ሦስት ጊዜ የተፈናቀለችው ራና ከሁለት ልጆቿ እና ከወላጆቿ ጋር በሆስፒታሉ አቅራቢያ ትኖራለች።

የዘጋቢ ፊልሙ የተወሰነ ክፍል በጥር 2024 በብሪታንያ የሕክምና ባለሙያዎች በማዕከላዊ ጋዛ ብቸኛው በሥራ ላይ ያለው ሆስፒታል በተባለው በአላ-አቅሳ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያዎች የሚያደርጉትን ርብርብ ያሳያል።
ቢቢሲ ዘካሪያን ያገኘው እዚያ ነው።
በሆስፒታሉ ውስጥ የሚሠሩ ሁሉ ዘካሪያን ያውቁታል።
በእርግጥ ገና ታዳጊ ነው። የሠለጠነ ሐኪም አይደለም ነገር ግን ሁል ጊዜ በሆስፒታሉ ክፍሎች አንድን ሰው ለመርዳት፣ በምላሹ የተወሰነ ምግብ ወይም ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ ከሆስፒታሉ አይጠፋም።
አንዳንድ ጊዜ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች እቃዎቻቸውን በመሸከም ያግዛል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የተጎዱ ወይም የሞቱ ሰዎችን በቃሬዛ ላይ አድርጎ ይገፋል።
ፀጥ ያለ ጊዜ ሲኖር ደም እና ቆሻሻ የተጋገረባቸውን አምቡላንሶች በማጽዳት ይረዳል።
የሚማርበት ትምህርት ቤት የለም፤ ከቤተሰቡ መካከልም የተገኘውን ሠርቶ ገንዘብ የሚያመጣው እርሱ ብቻ ነው።
ቤተሰቦቹ ምግብ እና ውሃ ስለሌላቸው አብሯቸው አይኖርም፤ ይልቁንም በሆስፒታል አካባቢ ብቻውን እንደሚኖር እና ባገኘው ስፍራ እንደሚተኛ ይናገራል።
አንዳንድ ምሽት በሲቲስካን ክፍል ውስጥ፣ ሌላ ቀን በጋዜጠኞች ድንኳን ወይም ከአምቡላንስ ጀርባ ይተኛል።
ብዙ ምሽቶች ባዶ ሆዱን እየራበው ወደሚተኛበት ስርቻ መሄዱን ያስታውሳል።
የሆስፒታሉ ሠራተኞች የቻሉትን ያህል ቢሞክሩም ተጎጂዎችን ከመንከባከብ ትርምስ ሊያርቁት አልቻሉም።

ዘካሪያ ለአደጋ ጊዜ ሕክምና ባለሙያዎች (ፓራሜዲክስ) የተለየ ክብር እና ፍቅር አለው። እንደ ቡድኑ አባል ተደርጎ እንዲቆጠርም ይፈልጋል።
ከሕክምና ቡድኑ መካከል አንዱ የሆነው ሰይድም ይህንን የዘካሪያ መሻት አልነፈገውም። “ልክ እንደ ልጅ የሚያየው ሰው ሲኖር ይቆጣል” ይላል ሁኔታውን ሲገልጸው።
ሌሎች ሠራተኞች በበኩላቸው ዘካሪያ ለእነሱ እና በሆስፒታሉ ውስጥ ለታካሚዎች የሚሰጠውን እንክብካቤ እና ትኩረት አይተው ለህሙማን በደም ስር የሚሰጥ ጠብታ (ጉልኮስ) መስጠት አስተምረውታል።
ለጥረቶቹ ሁሉ እውቅና ለመስጠት፣ ትንሽ ሰማያዊ የደንብ ልብስ አሰፍተውለታል። እርሱም በዚህ በጣም ይኮራል።
ሰይድ ልጁ አሁንም ልጅነቱን አለመነጠቁን ለማረጋገጥ ይሞክራል፤ እናም በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ወደ ባሕር ዳርቻ ሲሄዱ ካሜራው ይከተላቸዋል።
ከዛፍ ጥላ ስር ተቀምጠው ዘካሪያ ሰይድ የገዛውን ምሳ ይመገባል። “ሻዋርማው ጣፋጭ ነው” ይላል። ሰይድ ዘካርያ “ዝም የሚለው” ሲበላ ብቻ ነው ሲል ይቀልዳል።
ሰይድ፣ ዘካሪያ ብዙ ሞቶችን እና ውድመቶችን ስላየ ከእኩዮቹ ጋር ፈጽሞ ሊስማማ አይችል ይሆን የሚለው ያስጨንቀዋል።
ዘካሪያ ራሱን ከልጅነት በላይ አድርጎ እየተመለከተ ነው።
“ፓራሜዲክ መሆን እፈልጋለሁ” ይላል። “በመጀመሪያ ግን ከዚህ መውጣት አለብኝ።”