

ማኅበራዊ የአየር ንብረት ለውጡን ጫና ለመቋቋም
ቀን: February 16, 2025
በመስኖ ልማትና አየር ንብረት ለውጥ ላይ የተሻለ ትብብርና ግንኙነቶችን ለመፍጠር ያስችላል የተባለ ዓለም አቀፍ ‹‹የመስኖና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነት ጉባዔ›› ከየካቲት 5 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በዓድዋ ሙዚየም ተካሂዷል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በጉባዔው መክፈቻ ወቅት እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምን መሠረት ያደረጉ የምግብ ምርታማነት ሥራዎችን በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ነው፡፡ በመርሐ ግብሩም ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ ይህም የደን ሽፋንን ከማሳደግ በተጨማሪ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የምግብ ሉዓላዊነታቸውን እንዲያረጋግጡ እያገዘ ነው፡፡
‹‹ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነትን የምናከናውንበት ሌላው ዘርፍ የግብርና የበጋ ስንዴ ልማት ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ለዚህም ከውጭ የሚገባ ስንዴ በማቆም የስንዴ ምርት ፍጆታችንን በራሳችን አቅም በማምረት በመሸፈን ላይ እንገኛለን፡፡ ይህም ተሞክሮ አፍሪካ በራሷ አቅም የምግብ ፍጆታዋን መሸፈን እንደምትችል ማረጋገጫ ነው›› ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት፣ የሌማት ትሩፋትን በመጀመር በቤተሰብ ደረጃ የተመጣጠነ የምግብ ሥርዓትን የሚያረጋግጡ ምርቶች ላይ በማተኮር ውጤታማ ሥራዎች በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ አፍሪካውያንም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለመስኖ ልማት፣ ለግብርና ኢንቨስትመንትና ለቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይገባቸዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በመስኖ ልማት ላይ ያላት ልምድና ተሞክሮ ውስን የነበረ በመሆኑ፣ በዘርፉ ውጤት ማምጣት አልተቻለም ነበር፡፡ ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተሠሩ በሚገኙ ሥራዎችና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ምጣኔ ሀብት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው፡፡
የውኃ ሀብትን በአግባቡ በማልማት፣ የመስኖ ልማትን በማስፋፋትና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በኩል ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ውጤቶች ሊገኙ መቻላቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ፣ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ምጣኔ ሀብት ለመገንባት የምግብ ሉዓላዊነትን፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ አሠራሮችንና ውኃ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለምታደርገው ጥረት መንግሥታትና የፋይናንስ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡
በዓለም አቀፉ የመስኖና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የልማት ጉባዔ ላይ ከተለያዩ የዓለም አገሮች የተውጣጡ ከአንድ ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ የመስኖ ሥራዎችን የሚያሳይ ኤግዚቢሽንም ለዕይታ ክፍት ሆኗል፡፡