ኢትዮ ሄልዝ ዓውደ ርዕይን አስመልክቶ መግለጫ ሲሰጥ

ማኅበራዊ አዳዲስ የሕክምና ቴክኖሎጂዎች እንደሚተዋወቁበት የሚጠበቀው መድረክ

የማነ ብርሃኑ

ቀን: February 16, 2025

በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የሕክምና አገልግሎት ፍላጎት ለማሳካት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችና መፍትሔዎችን የሚያቀርቡ በአሥር አገሮች የሚገኙ ኩባንያዎች ይሳተፉበታል የተባለው ዘጠነኛው ኢትዮ ሄልዝ ዓውደ ርዕይ ከየካቲት 13 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡

ከዓውደ ርዕዩ ጎን ለጎንም በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አማካይነት አራተኛው ዓለም አቀፍ የመድኃኒት አቅራቢዎች ጉባዔ የሚካሄድ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ናሆም ገመቹ እንደተናገሩት፣ ተቋሙ በጥራት የተረጋገጡ መድኃኒቶችን፣ የላቦራቶሪ ኤጀንቶች፣ የሕክምና መሣሪያዎችና የጤና አቅርቦቶችን በመግዛትና በማሠራጨት ከ70 ዓመት በላይ ልምድ ያለው ነው፡፡ በዓመት ከ989 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ግዥ በመፈጸም አገር አቀፍ የሕዝብ የጤና ተቋማት አስፈላጊ የጤና ግብዓቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ተቋሙ ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የመድኃኒት አቅራቢዎች ጉባዔ የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የተሻሻሉና ዘመናዊ ዘዴዎችን እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እየሰራ መሆኑን ለማስተዋወቅ የሚረዳ ነው፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ፣ ጉባዔው የመድኃኒት አቅራቢዎችን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ የመንግሥት አካላትን፣ የምርምር ተቋማትንና ሌሎች ተሳታፊ አካላትን በማሰባሰብ የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎትን ለማሻሻል ይጠቅማሉ የሚባሉ ውይይቶችና ተሞክሮዎች የሚቀርቡበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመድኃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል የተለያዩ አሠራሮችን ዘርግቶ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል የኤሌክትሮኒክስ የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓቶች፣ የሰው ኃይል ሥልጠናና የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን የማጠናከር ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡

በአራተኛው ዓለም አቀፍ የመድኃኒት አቅራቢዎች ጉባዔ ላይም ሌሎች አዳዲስና ተጨማሪ የአገልግሎት ማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች ይቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮ ሄልዝ የላይፍ ሳይንስ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዳዊት ተስፋ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በዓውደ ርዕዩ ከአሥር አገሮች የተውጣጡ ከ90 በላይ ኩባንያዎች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አቅራቢዎችን ለኢትዮጵያ በማስተዋወቅ ረገድ የጎላ ፋይዳ የሚኖረው ከመሆኑም በላይ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግርን በማምጣት ለዘርፉ ልማት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይታመናል፡፡

‹‹ከአራት ሺሕ የሚበልጡ የጤና ባለሙያዎችና የዘርፉ የንግድ ማኅበረሰብ አካላት ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት ነው›› ያሉት ፕሮጀክት አስተባባሪው፣ ከሃያ በላይ በሆኑ የሙያ ማኅበራትና አጋር ድርጅቶች የሚዘጋጁ ጉባዔዎች ከመኖራቸው በተጨማሪ ሁለተኛው የዲጂታል ሄልዝ ሃካቶንና (ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች) የጀማሪዎች ፒች ውድድር እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡

የዲጂታል ሄልዝ ሃካቶን በጤናው ዘርፍ ላይ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለማበረታታት በወጣቶች መካከል የሚደረግ ውድድር ሲሆን፣ በዲጂታል ጤና ላይ ጀማሪ ድርጅቶች ሐሳባቸውን በማቅረብ ተጨማሪ ሥራ ማስኬጃ ፈንድ የሚያስገኝላቸውን ዕድል የሚያመቻቹበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳዊት (ዶ/ር)፣ ኢትዮ ሄልዝ በጤና ዘርፍ የተሰማሩ የንግድ ማኅበረሰብ አካላትና የጤና ባለሙያዎችን በአንድ በማሰባሰብ የጤና እንክብካቤ አገልግሎት ተደራሽነትንና ጥራትን ማሳደግ በሚቻልባቸውና በመድኃኒት አቅርቦት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍትሔ ሐሳቦች የሚቀርቡበት ነው፡፡

በዓውደ ርዕዩም የጤና ዘርፍ አመራር ጉባዔ፣ የዲጂታል ኸልዝ ፎረም፣ የሜዲካል ቱሪዝም ጉባዔ፣ ሳይንሳዊ ኮንፈረንስ፣ የሥራ ፈጣሪዎች ፎረም፣ ሴቶችና ጤና በሚሉና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቶች የሚደረጉባቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ የግል ሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የመድኃኒትና ሕክምና መገልገያ አምራቾች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የመድኃኒት የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችና የላቦራቶሪ ኬሚካል አስመጪና አከፋፋዮች ማኅበር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የፓን አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ለዓውደ ርዕዩ ድጋፍ ያደረጉ ተቋማት ስለመሆናቸውም ተገልጿል፡፡