ማኅበራዊ
የጤናው ዘርፍ ባለፉት ስድሥት ወራት

አበበ ፍቅር

ቀን: February 16, 2025

የወባ በሽታ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ዋነኛ የጤናና የማኅበራዊ ቀውስ መንስዔ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2024 ያወጣው መረጃም 263 ሚሊዮን ሰዎች የወባ በሽታ ተጠቂ እንደነበሩ ያሳያል፡፡

ከተመዘገበው ውስጥ 94 በመቶ የሚሆኑት የወባ ተጠቂዎች ከአፍሪካ ሲሆኑ፣ 95 በመቶ (597,000) የሚሆነው ሞት የተመዘገበውም በዚሁ አኅጉር መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አመላክ~ል፡፡

የታማሚዎች ቁጥርም እ.ኤ.አ. ከ2023 ጋር ሲነፃፀር የ11 ሚሊዮን ጭማሪ ማሳየቱን፣ የጤና ሚኒስትር ደኤታው ደረጄ ድጉማ (ዶ/ር) የዓለም ጤና ድርጅት በ2024 ያወጣውን መረጃ ዋቢ አድርገው ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ደኤታው በጥር ወር መጨረሻ ላይ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የግማሽ ዓመቱን የሥራ ክንውን ሪፖርት ለጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር 75 በመቶ የሚሆነው ለወባ በሽታ ሥርጭት አመቺ ሲሆን፣ 69 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በእነዚህ አካባቢዎች ስለሚኖር ለበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ነው፡፡

ወባ የሚከሰተው ዋናውን የክረምት ዝናብ ተከትሎ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ድረስ ባለው በምርት መሰብሰቢያ ወቅት ሲሆን፣ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባለው ወቅት በመካከለኛ ደረጃ ስለሚተላለፍ አስቀድሞ በሽታውን መከላከል ካልተቻለ ዜጎችን ለሕመምና ለሞት እንዲሁም ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያ ችግር እንደሚዳርግ ጠቁመዋል፡፡

አገሪቱ ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት የወባ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም በወባ በሽታ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባ እንደነበር የጠቀሱት ደረጀ (ዶ/ር)፣ እ.ኤ.አ በ2030 ወባን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶና ስትራቴጂ ተነድፎ በተመረጡ ወረዳዎች ላይ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አክለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት በሽታው ባልተጠበቀ መልኩ እየጨመረ በመምጣት፣ በተለይ በ222 ወረዳዎች ላይ የወባ ሕሙማን ቁጥር ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡

በዋናነት በአገሪቱ 76 በመቶ የሚሆነው የወባ ሥርጭት መጠን የያዙት 222 ወረዳዎችን በመለየት በተደረገ ክትትል ለውጦች መታየታቸውን አብራርተዋል፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የዝናብ መቆራረጥ በመኖሩ፣ የወንዞች መቆራረጥና በየአካባቢው ያቆረ ውኃ መኖር እንዲሁም የድርቅ መከሰትና ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች አገልገሎቶችን ለመስጠት አስቸጋሪ መሆን፣ ‘ወባ ቀንሷል’ በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ በኅብረተሰቡ እንዲሁም በየደረጃው ባለው ባለሙያና አመራር ዘንድ መዘናጋት መኖር፣ የአልጋ አጎበር በትክክል አለመጠቀምና አለመያዝ፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በጤና ኬላ ይሰጥ የነበረው የወባ መከላከል፣ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት በሚጠበቀው ደረጃ አለመሆን የሚሉት ሚኒስትር ደኤታው ለወረርሽኙ መጨመር እንደ ምክንያት የጠቀሷቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡

ወባን ለመከላከልና ለመቀነስ የተሠሩ ሥራዎችን ያጋጠሙ ችግሮችን እንዲሁም በሒደት ላይ ያሉ ጉዳዮችን በዳሰሳ ያቀረቡት ሚኒስትር ደኤታው፣ በ2017 በጀት ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ 13,917,829 የወባ ተጠርጣሪ ሕሙማን ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 5,961,704 ያህሉ የወባ ተህዋስ ስለተገኘባቸው ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ መደረጉንና  7.2 ሚሊዮን ሕሙማንን ማከም የሚያስችል የተለያየ የፀረ ወባ መድኃኒቶች ተገዝተው መሠራጨታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት 19.7 ሚሊዮን አጎበር ለኅብረተሰቡ መሠራጨቱን ያስታወቁት ደረጀ (ዶ/ር)፣ በ2016/17 በጀት ዓመት ደግሞ 2.2 ሚሊዮን የመኝታ አጎበር ግዥ ተፈጽሞ በከፍተኛ ሁኔታ በተጠቁ ወረዳዎች ውስጥ ለሚኖረው ኅብረተሰብ መሠራጨቱን አስታውሰዋል።

በአጠቃላይ በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር 8.1 ሚሊዮን ሕዝብ ከወባ በሽታ እንዲጠበቅ መደረጉን በሪፖርታቸው ገልጸው፣ በኢንተለጀንስ ታግዘው በመድኃኒት ግዥና ሥርጭት በተደረገ ኦፕሬሽን የጤና ተቋማት ኦዲቲንግ፣ የገበያ ቅኝት የቅድመና ድኅረ ፈቃድ ጥራት ምርመራ፣ የወባ መድኃኒቶች አስመልክቶ የተሠሩ የቁጥጥር ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡

በዚህም በ56 የመንግሥት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያ እንዲሁም ክሊኒኮች ኦዲት የተሠራ ሲሆን፣ 78 በሚሆኑ የመድኃኒት መደብርና ፋርማሲ የገበያ ቅኝት እንዲሁም በ49 ተቋማትና በተለያዩ መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር በአጠቃላይ 450 ኩንታል ወይም 45 ቶን ሕገወጥ የወባ መድኃኒቶች በቁጥጥር ሥር በማዋል በኅብረተሰቡ ላይ ሊደርስ የነበረ ጉዳትን ማስቀረት መቻሉንና በብር ሲተመን 313,906,382.00 እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ዘጠኝ ኩንታል መድሃኒት ከመንግሥት ተቋማት ወደ ሌሎች ፋርማሲዎች ሲዘዋወርም ተይዟል። ይህንን ሲያደርጉ የተገኙ 156 ፋርማሲዎችና መድኃኒት መደብሮች ፈቃዳቸው የተሰረዘ ሲሆን፣ 21 ክሊኒኮች፣ ፋርማሲዎችና መድኃኒት መደብሮች ከሦስት ወራት እስከ 6 ወራት ፈቃድ ዕገዳ እንዲሁም ከ10,000 ብር እስከ 60,000 ብር ቅጣትና 60 ክሊኒኮች የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ተመላክ~ል፡፡

ካጋጠሙ ዋና ዋና ተግዳሮቶችም መካከል የበጅት እጥረት በአንዳንድ ቦታዎች የግብዓት አቅርቦት መቆራርጥ እንዲሁም ግብዓትን እስከ ታችኛው ዕርከን ድረስ ለማውረድ መቸገር የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምና የመሠረታዊ ጤና ክብካቤ መላላት፣ በታችኛው መዋቅር ለፕሮግራሙ ያለው ትኩረት ማነስ፣ ከሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር ቅንጅታዊ አሠራር አለመዳበር የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡

ከወባ ወረርሽኝ ባሻገር እንደ ኮሌራና ኩፍኝ ያሉ በሽታዎች ያሉበትን ደረጃ በሪፖርታቸው ለማካተት የሞከሩት ደረጀ (ዶ/ር) የኮሌራ ሥርጭት ከ432 ወረዳዎች ውስጥ በ432 ወረዳዎች ቁጥጥር ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በአንድ ወረዳ ብቻ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ወረርሽኙ ባለባቸው አካባቢዎች በአሥር ዙር በተሰጠ ክትባት 13 ሚሊዮን ሰዎች መዳረሳቸው ተነግሯል፡፡

የኩፍኝ ሥርጭትን በተመለከተ ደግሞ 463 ወረዳዎች ላይ በተደረገ ቁጥጥር በሰባት ክልሎች በሚገኙ 20 ወረዳዎች ወረርሽኙ አሁንም መኖሩን አምነዋል፡፡

ከፍተኛ የሆነ የአምቡላንስ እጥረት ማጋጠሙ የተነሳ ሲሆን፣ ችግሩን ለማቃለል ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሕክምና ከመጣው በጀት በመቀነስ 370 አምቡላንሶችን ከውጭ አገር በግዥ እንደገቡ ያስረዱት ሚኒስትር ደኤታው፣ ይህም የተወሰኑ ችግሮችን ሊቀርፍ ከቻለ እንጂ ማርካት እንደማይቻል እንገነዘባለን ሲሉ ተደምጠዋል። ጥገና ከሚያስፈልጋቸው 960 አምቡላንሶች መካከል ለ100 አምቡላንሶች የሚሆኑ 40 ሚሊዮን ብር መመደቡን አክለዋል፡፡

  የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚዎች አቀረቡት ለተባለው ቅሬታ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትር ደኤታው፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በመድኃኒት አቅርቦት ዙሪያ ባለው ክፍተት ለአላስፈላጊ እንግልትና ወጪ ተዳርገናል የሚለውን ቅሬታ በማጥናት በአንዳንድ ጤና ተቋማት ላይ በግልጽ የሚታይና እውነትነት ያለው በመሆኑ ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመሆን ለጤና ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በመስጠትና የጤና መድንን ብቻ የሚያስተናግድ መስኮት በመክፈት ቅሬታን የመቅረፍ ሥራን እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የጤና ተቋማትን የጤና መድን የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተ የቀረበው ቅሬታ ሲጠና፣ ወረዳዎች የሰበሰቡት የጤና መድን መዋጮና የተጠቃሚዎች የጤና ተቋም ክፍያ የሚጠየቀውን ያህል ተመጣጣኝ ያለ መሆን በተቃራኒው ደግሞ የጤና መድህን አገልግሎት የአገልግሎት አሰጣጥ ኦዲት ሲደረግ በጤና ተቋማት አመዘጋገብና ክፍያ ጥያቄ ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ከሚወስደው ጊዜ አንፃር ቅሬታዎች እንደሚቀርቡ ተናግረው፣ ይህም ለወደፊቱ የሚፈታበት የኤሌክትሮኒክስ ምዝገባና ክፍያ መንገድ እየተሠራ እንደሆነ አክለዋል።

የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በሁሉም ጤና ተቋማት የወሊድ የክትባትና የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና በነፃ እንዲሰጥ ከጤና ሚኒስቴር በተላለፈው መመርያ መሠረት፣ ሁሉም ጤና ተቋማት አገልግሎቱን መስጠት ላይ ቢሆኑም፣ ለዚህ አገልግሎት የወጣው ወጪ ባለመተካቱ በጤና ተቋማት በኩል ሰፊ ቅሬታ ያስነሳ ሲሆን፣ በአንደንድ ቦታዎችም እናቶችን ማስከፈል እንደተጀመረ መስማታቸውን የጠቀሱት ደረጀ (ዶ/ር)፣ ለዚህም የጤና ሚኒስቴር ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለእናቶችና ለሕፃናት የወጣውን ወጪ የሚመለስበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ ነው ብለዋል።

የጤና ባለሙያዎችን የተጋላጭነት ክፍያ በተመለከተ በየጊዜው የሚነሱ ቅሬታዎችን በሜዲካል ሰርቪስና በሰው ሀብት ልማት በኩል እንዲጠኑ በማድረግ ዕልባት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ የመንግሥት ሠራተኞችና የጡረተኞች የጤና መድን ሽፋን በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው ሶሻል ሔልዝ ኢንሹራንስ በሥራ ላይ ሲውል እንደሚፈታው፣ በሌላ መልኩ አዲስ እየተሠራ ባለው የጤናው ዘርፍ ሪፎርም ውስጥም የመንግሥት ሠራተኞች በያዙት የፋይዳ መታወቂያ የሕክምና አገልግሎትን ጨምሮ በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲያገኙ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር እየተሠራ ስለመሆኑ አብራርተዋል።