ወደ ፍርስራሽነት የተቀየሩ የጋዛ አካባቢዎች

ዓለም የትራምፕ ጋዛን የመሰልቀጥ ውጥንና የተቃውሞ ድምፆች

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: February 12, 2025

የጋዛ ሰርጥ በሜዲትራኒያን ባህር 41 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን ይጋራል፡፡ በሰርጡ አገረ መንግሥት እንዳይኖራቸው ተደርገው 2.3 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ይኖራሉ፡፡ ጋዛን በደቡብ ምዕራብ ግብፅ፣ በምሥራቅና ሰሜን ደግሞ እስራኤል ያዋስኗታል፡፡ የራሴ ብላ የምታስተዳድረው የባህርም ሆነ የአየር ክልል እንዳይኖራትም ተከልክላለች፡፡ እስራኤል ነች የጋዛን የባህርና የአየር ክልል የምትቆጣጠረው፡፡ ሕዝቡ ወደ ግብፅም ሆነ ወደ እስራኤል እንዳይንቀሳቀስ በሁለቱም አገሮች ወታደሮች ከላይም ከታችም ታግዶ ላለፉት በርካታ አሠርት ዓመታት እየኖረ ነው፡፡

የትራምፕ ጋዛን የመሰልቀጥ ውጥንና የተቃውሞ ድምፆች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጋዛ ሪማል አካባቢ እ.ኤ.አ. ከ2023 በኋላ

ጥንት ጋዛ የበለፀገችና በበረሃ መሃል እንዳለ ልምላሜ ትቆጠር የነበረች ግዛት እንደነበረች የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ የጥንት የመካከለኛው ምሥራቅ ኃያላን (Empires) ግብፅን ሲያስገብሩ ጋዛን እንደ መስፈንጠሪያ ተጠቅመው ነበር፡፡ ከዓባይ ተፋሰስ የሚነሱ ኃያላንም ጋዛን እየተስፈነጠሩ ሌቫንትን አስገበሩ፡፡

እ.ኤ.አ. ወደ 1967 መለስ ስንል፣ የግብፅና የእስራኤል ጦርነት በእስራኤል አሸናፊነት ሲቋጭ ጋዛ በእስራኤል እጅ ወደቀች፡፡ እ.ኤ.አ. ኦገስት 15 ቀን 2005 ደግሞ በጊዜው በነበሩት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪየል ሻሮን ጎትጓችነት እስራኤል ከጋዛ የባህር ወሽመጥና ከሰሜናዊ ሳማሪያ አፈገፈገች፡፡ ሻሮን ያን ያደረጉት የእስራኤልን ደኅንነት ለማስጠበቅና ከፍልስጤማውያን ጋር የሰላም ድርድር በሌለበት ሁኔታ የአገራቸውን ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ለማሻሻል በሚሉ ምክንያቶች መነሻነት እንደነበር ይነገራል፡፡

የትራምፕ ጋዛን የመሰልቀጥ ውጥንና የተቃውሞ ድምፆች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጋዛ ሪማል አካባቢ እ.ኤ.አ. ከ2023 በፊት

እ.ኤ.አ. ጁን 14 ቀን 2007 ከዓመታት ፖለቲካዊ መቆራቆስ በኋላ በፍልስጤሞችና በእራኤላውያን መካከል ሁለት አገረ መንግሥታት የመመሥረት ውጥን የተነሳ፣ ሐማስ ጋዛን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ፡፡

እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 7 ቀን 2023 የሐማስ ታጣቂዎች እስራኤል ዘልቀው በመግባት ጥቃት ሰነዘሩ፡፡ 1,200 እስራኤላውያንን ሲገድሉ፣ 250 የእስራኤልንና የሌሎች ዜጎችን አግተው ወሰዱ፡፡ ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል የአገሯ ወታደር በጠላት ከሚያዝ ሞቱን የተሻለ አማራጭ የሚያደርገውን የ‹‹ሃኒባል መመርያ›› ተግባራዊ በማድረግ ወደ ሙሉ የማጥቃት ዕርምጃ ገባች፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ እስከ የ2025 የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ድረስ 48,181 ፍልስጤማውያን ተገደሉ፣ የጋዛ ሕዝብ በቀዬው ስደተኛና ተቅበዝባጭ እንዲሆን ተገደደ፡፡ የጋዛ ሕንፃዎች ወደ ፍርስራሽነት ተለወጡ፡፡ መሠረተ ልማቶች ወደሙ፡፡ ሆስፒታሎች መቀበሪያ ሆኑ፣ ዛጉ፣ ተዘጉ፡፡ ሕዝቡ በድስት ሾርባ ተሻምቶ የሚሠፈርለት ሆነ…፣ እሱም ከተገኘ፡፡

ካለፉት ሦስት ሳምንታት ወዲህ በእስራኤልና በሐማስ በተደረገ የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት፣ ፍልስጤማውያን የተሻለ ዕርዳታ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን፣ ሁለቱ ወገኖች የእስረኞችና የታጋቾች ልውውጥ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ባለፈው ሳምንት የእስራኤል ፕሬዚዳንት ቤንያሚን ኔታንያሁ አሜሪካን ጎበኙ፡፡ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 20, 2025 ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቃለ መሃላ በመፈጸም ተከታታይ ያልሆነ የሁለተኛ የመሪነት ሥልጣን ዘመናቸውን ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት በመግባት ከጀመሩ በኋላ ለመጀመሪያ የተቀበሉት የውጭ መሪም ኔታንያሁ ሆነዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ነበር ትራምፕ ጋዛን የመረከብ ውጥናቸውን ደግመው በአጽንኦት የተናገሩት፡፡

ይህ ንግግራቸው በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ቁጣ፣ በተቀረው ዓለም ደግሞ በተለያዩ ደረጃዎች የሚታይ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የትራምፕን ያልተጠበቀ እወጃ፣ ‹‹እስካሁን ከማንም ያልተሰማ ማለፊያ ሐሳብ›› ሲሉ አሞካሽተውታል፡፡ ይህንን በመከተል ደግሞ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ፍልስጤማውያንን ‹‹በፈቃዳቸው›› ከጋዛ ለማስወጣት የምዝገባ እንቅስቃሴ እንደጀመረ ተሰምቷል፡፡  

ትራምፕ ዕቅዳቸውን ሲያሳውቁ በግልጽ ያመለከቱት ነገር ቢኖር፣ ዮርዳኖስና ግብፅ የጋዛን ሠፋሪዎች መቀበል እንደሚኖርባቸው ነው፡፡ ከዚያ የጋዛን ፍርስራሽ አስጠርገው ውብ አዲስ ከተማ በሜዲትራንያን ባህር ዳርቻዋ ጋዛ ይገነባሉ፡፡ ለዚህም ጦርነቱ እንዳበቃ እስራኤል ጋዛን ለአሜሪካ አሳልፋ ታስረክባለች፡፡ አሜሪካ ጋዛን ‹‹የመካከለኛው ምሥራቅ ሪቬራ›› ታደርጋለች፡፡ ይህ የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ የቀጠለ ዱብ ዕዳ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮና በመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴዝ ተሞካሽቷል፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ የትራምፕን ውጥን መስተጋባት ተከትሎ እንደተናገሩት፣ መንግሥታቸው ከፍልስጤም ጠቅላይ ሚኒስትር መሐሙድ ሙስጠፋ ጋር ጋዛ በአፋጣኝ መልሳ በምትገነባበትና የተፈናቀሉ ወደ ቀዬአቸው በሚመለሱባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል፡፡ የዓረብ ሊግ ዘዋሪ እንደሆነች ከሚነገርላት ግብፅ ከዚህ በተለየ ያን ያህል ጠንከር ያለ ምላሽ አልተሰጠም፡፡ ግብፅ ከአሜሪካ በየዓመቱ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያዎች ትደጎማለች፡፡ ትራምፕ ግብፅ ማንገራገሯ ሲነገራቸው፣ ‹‹ከእኛ ብዙ ታገኛለች›› የሚል ነበር መልሳቸው፡፡

የዮርዳኖስ ንጉሥ አብደላ እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 11 ነጩን ቤተ መንግሥት እንደሚጎበኙ በመገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ ባፈለው ሳምንት ደግሞ የትራምፕ ውጥን ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ የጆርዳን ንጉሣዊ መንበር (Jordanian Royal Court) በኤክስ ገጹ፣ ‹‹ግርማዊነታቸው ንጉሥ አብደላ ዘ ዳግማዊ የእስራኤላውያን ሠፈራ በፍልስጤም ምድር በአስቸኳይ እንዲገታ አበክረው በማሳሰብ፣ የፍልስጤማውያንን መሬት የሚቀማ ብሎም ፍልስጤማውያንን የሚያፈናቅል የትኛውንም ጥረት እንደሚቃወሙ አጽንኦት ሰጥተዋል፤›› ብሏል ሮይተርስ፡፡

ጉዳዩ ለዮርዳኖስ ለየት ብሎ የሚቆጠቁጥ ነው፡፡ ለዮርዳኖስ የትራምፕን ውጥን መቀበል በአገር ውስጥ የባሰ ምስቅልቅል መጋበዝ ነው፡፡ ሕዝቡ ዓመቱን ሙሉ እስራኤል ጋዛ ላይ የምታደርገውን ድብደባ ሲቃወም ነው የሰነበተው፡፡ ለዚያ ጥያቄያቸው መንግሥታቸው ያሳየው ማንገራገር ዮርዳኖስ ምን ያህል በአሜሪካና በእስራኤል ጥገኛ መሆኗን ያሳያል፤›› ሲል ተንትኗል ሮይተርስ በዘገባው፡፡

ጆርዳን ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሁሉ የላቀውን የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታና ትብብር የምታገኝ አገር ነች፡፡ በቅርቡ የወጣ የአሜሪካ ፓርላሜንታዊ ሪፖርት እንደሚያሳው፣ ከስምንት ሚሊዮን የዮርዳኖስ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ የፍልስጤማውያን ዝርያ አላቸው፡፡

‹‹ጋዛ የፍልስጤም ግዛት አካል ነች፣ የሕዝባችን መብቶች በዚህ መንገድ እንዲደፈጠጡ አንፈቅድም፤›› ሲሉ የፍልስጤም አስተዳደር መሪ መሐሙድ አባስ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ሕዝቦችን በኃይል ማፈናቀል የከፋ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነውም ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ይህንን የአባስን ብሶት በመደገፍ ጠንከር ባሉ ቃላት ባወጡት መግለጫና ማስጠንቀቂያ፣ ‹‹አንድ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ፣ የተቀናጀ ከሰውነት የማሳነስና ማሰይጠን ሲፈጸም ዓለም እየተመለከተ ነው፤›› ሲሉ ኒውዮርክ በተደረገ ስብሰባ ተደምጠዋል፡፡ እንደ እሳቸው አባባል ጋዛ ወደፊት ለሚመሠረተው የፍልስጤም አገረ መንግሥት አንድ አካል ናት፡፡  

ባለፈው ሳምንት ትራምፕ የጋዛ ነዋሪዎች የሚነቀሉት ለአንዴና ለመጨረሻ እንደሆነ ቢጠቁሙም፣ በነጋታው ረቡዕ የነጩ ቤተ መንግሥት ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት፣ ‹‹ትራምፕ ጋዛን መልሶ ለመንባትና ሕዝቡንም ‹በጊዜያዊነት› ወደ ሌሎች ቦታዎች ለማዛወር ፅኑ ፍላጎት አላቸው፤›› ሲሉ ነበር ነገሩን በትንሹም ቢሆን ያለሳለሱት፡፡ ሴክሬታሪዋ እንዳሉት፣ የትራምፕ ውጥን ከተለምዶ ወጣ ያለ ሐሳብ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ይህንን ውጥን ለማስፈጸም አሜሪካ ወደ ጋዛ ወታደሮች መላክ እንደማይጠበቅባት በመናገር የፕሬዚዳንቱን የቀደመ ንግግር አስተጋብተዋል፡፡

በሐማስ ቁጥጥር ሥር ያለው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳሳወቀው፣ በ15 ወራት የእስራኤል ድብደባ 48,181 ሰዎች ሲገደሉ 111,600 ያህል ደግሞ ቆስለዋል፡፡ ወደ 70 በመቶ የሚጠጉ ሕንፃዎች ፈራርሰዋል፡፡ አብዛኛው የጋዛ ነዋሪ ከአንድ በላይ ጊዜ ቀዬውን ጥሎ ተሰዷል፡፡ የጤና ጥበቃ፣ የውኃ፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና ጥበቃ ሥርዓቶች ፈራርሰዋል፡፡ ሕዝቡ ለምግብ፣ ለነዳጅ፣ ለመድኃኒትና ለመጠለያ ችግሮች ተዳርጓል፡፡

እንደ ቢቢሲ ዘገባ፣ ፍልስጤማውያን እ.ኤ.አ. የ1948 የእስራኤል አገረ መንግሥትን ተከትሎ በተደረገ ጦርነትና ከጦርነቱም በኋላ በመቶ ሺዎች ተገደው የተፈናቀሉበትን ‹‹ናቅባ›› ድጋሚ መምጣት ይሠጋሉ፡፡ በዚያን ጊዜ ከተፈናቀሉት የሚበዙት ጋዛ ውስጥ ነበር የሠፈሩት፡፡ ሌሎች 900,000 የሚሆኑት እንደ ስደተኛ ተቆጥረው በዌስት ባንክ ሲገኙ፣ 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑት ፍልስጤማውያን ደግሞ በዮርዳኖስ፣ በሶሪያና በሊባኖስ ይገኛሉ፡፡

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አዲሱ የትራምፕ ዕቅድ ፍልስጤማውያንን ለባሰ እንግልት የሚዳርግ፣ እንደ ሕዝብ ያላቸውን መብቶች የሚነሳ እንደሆነ ያስጠነቅቃል፡፡

የፈረንሣይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ እንዳሳወቀው፣ ሁኔታው ፍልስጤማውያን ያላቸውን የመጨረሻ ተስፋ የሚያጨልም፣ የዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥስ፣ ብሎም ‹የሁለት አገረ መንግሥታት› መፍትሔ ላይ ጋሬጣ የሚሆን ነው፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የትራምፕን ሐሳብ ያለማንገራገር ውድቅ አድርጓል፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር ‹‹ፍልስጤማውያን አገር ሊተውላቸው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹መልሰው እንዲገነቡ ማስቻል ይገባናል፣ ወደ የሁለት አገረ መንግሥታት መፍትሔ እንዲያመሩም ከጎናቸው ልንቆም ይገባናል፤›› ሲሉ ስታርመር ለፓርላማ ተናግረዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋዛን የመሰልቀጥ ዕቅድ ከአሜሪካ ሴናተሮችና ከሲቪል ማኅበረሰብ ተዋናዮች ዘንድም ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ የአሜሪካ እስላማዊ ግንኙነት ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ጋዛ የፍልስጤማውያን እንጂ የአሜሪካ አይደለችም፡፡ ስለሆነም የፕሬዚዳንት ትራፕም ፍልስጤማውያንን ከመሬታቸው የመንቀል ሐሳብ የሚያዋጣ አይሆንም፤›› ብሏል፡፡

ክሪስ መርፊ ዴሞክራት የአሜሪካ ሴናተር ሲሆኑ፣ ‹‹አሜሪካ ጋዛን ብትወር በሺዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገደሉበትና ለአሠርት ዓመታት የሚዘልቅ ጦርነት የሚጀመርበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አይሆኑ ቀልድና ስላቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው የዴሞክራት ሴናተር ክሪስ ቫን ሆለን፣ ‹‹የትራምፕ ፍልስጤማውያንን ነቅሎ ጋዛን መሰልቀጥ፣ ዘር አጠባን በሌላ ስም እንደ መጥራት ነው፡፡ ይህ ሐሳብ ለኢራን ጥይት እንደማቀበል ሲሆን፣ የዓረብ አጋሮቻችንን የሚያሳጣ ይሆናል፤›› ብለውታል፡፡

ስፔን፣ አውስትራሊያ እንዲሁም አየርላንድ የትራምፕን ውጥን ከተቃወሙ በርካታ አገሮች ተርታ ይገኙበታል፡፡

ይህ ሁሉ ተቃውሞ እስካሁን ትራምፕን ከውጥናቸው የመለሳቸው አይመስልም፡፡ ‹‹ጋዛን እንረከባለን፣ በቦታው የፈሰሰውን ያልፈነዳ ቦምብ በሙሉ ለማፅዳት ኃላፊነቱን እንወስዳለን፤›› ሲሉ የተደመጡት ትራምፕ፣ ጋዛን እንደገና ገንብተው የመካከለኛው ምሥራቅ ውቧ የባህር ዳርቻ ፈርጥ እናደርጋታለንም ብለዋል፡፡ ንግግራቸው አገራቸው ጋዛንና አካባቢውን ለረዥም ጊዜ የመቆጣጠር ትልም እንዳላት ሳያሳብቅ እንደማይቀር አንዳንድ ተንታኞች ጠቁመዋል፡፡.