
February 12, 2025
https://www.ethiopianreporter.com/138297
አቶ አብነት ተክሌ የሥነ ምግብ ባለሙያ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪውን ምግብና ምግብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ነው ያጠናው፡፡ በመጀመሪያ ዲግሪው በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ፉድ ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ›› በሚል ለአራት ዓመታት ያጠና ሲሆን ማስተርሱን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ ‹‹ፉድ ሳይንስ ኤንድ ኒውትሬሽን በሚል ተመርቋል፡፡ ተመርቆ ከወጣ በኋላም ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቶ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ‹‹ኒውትሬሽናል ፕሮዳክት ኤንድ ሰርቪስ›› የተባለ የግል ድርጅት በማቋቋም ከአመጋገብ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን በተመለከተ የማማከር አገልግሎትን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹ኒውተሬሽናል ፕሮዳክት ኤንድ ሰርቪስ የተባለው የግል ድርጅት ከምግብና ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ለማኅበረሰቡ ምን ዓይነት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል የሚለውን የድርጅቱን ባለቤት አቶ አብነት ተክሌን አበበ ፍቅር አነጋግሮታል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደዚህ ሥራ እንዴት ገባህ?
አቶ አብነት፡- ከልጅነቴ ጀምሮ ምግብና የአመጋገብ ሥርዓት ላይ የነበረኝ አስተሳሰብ በጣም ጥሩ የሚባል ነበር፡፡ አብሮኝ ያደገው ፍላጎቴ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ዘልቆ ‹‹ፉድ ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ›› በሚል በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ለአራት ዓመታት ተከታትያለሁ፡፡ በመቀጠልም ካለኝ ፍላጎት በመነሳት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፉድ ሳይንስ ኤንድ ኒውትሬሽን በሚል አጥንቻለሁ፡፡ ቀስ በቀስ ግንዛቤዬ እየጨመረ ሲመጣ ከአመጋገብ ሥርዓታችን ጋር ያሉትን ክፍተቶች ማየት ጀመርኩ፡፡ በተለይ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ትልቅ ክፍተት ተደርጎ ይወሰድ የነበረው የምግብ እጥረትና ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግሮች ነበሩ፡፡ ትምህርታችንም በአብዛኛው የሚያተኩረው በእነዚህ ዙሪያ ነው፡፡ እኔ በግሌ የተለያዩ ነገሮችን ሳስተውል አገራችን ከምግብ እጥረት ባሻገር ከአመጋገብ ሥርዓታችን ጋር ተያይዞ የሚመጣው ችግርም ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ ላይ በስፋት ለመሥራት ነበር ድርጅት በማቋቋም ወደ ሥራ የገባሁት፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ላይ በዋናነት ምን ላይ ትኩረት አድርገህ ነው እየሠራህ ያለኸው?
አቶ አብነት፡- በዋናነት በሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጌ ነው የምሠራው፡፡ በምግብ እጥረት የሚመጡ በሽታዎችና በአመጋገብ ሥርዓት መጓደል ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ በሽታዎችን በተመለከተ በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- በአመጋገብ ሥርዓት ጉድለት የሚከሰቱ በሽታዎች የትኞቹ ናቸው?
አቶ አብነት፡- ተመሳሳይ ምግቦችን የምንመገብ ከሆነ ለምሳሌ እንደ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ማሽላም ሆነ ሌሎች ጥራጥሬዎች እንዲሁም ሥጋና የሥጋ ውጤቶች ላይ የምናተኩር ከሆነ የማወፈር ባህሪ ስላላቸው እንደ ስኳር፣ ደም ግፊትና የመሳሰሉ በሽታዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ተመሳሳይ ሥራዎችን የሚሠሩ ሌሎች ተቋማት አሉ፡፡ የእናንተ ድርጅት በዋናነት ለየት የሚያደርገው ነገር ካለ?
አቶ አብነት፡- እኛ ከሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት ሰጭዎች ለየት የሚያደርገን ሰዎች እንዲጠቀሙ የምንመክረውና እኛም የምናቀርበው ሙሉ በሙሉ አገራችን ውስጥ የሚመረቱና የሚዘጋጁ ምግቦችን ነው፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የምናየው ነገር ቢኖር ግን ከውጭ የሚመጡ ምግቦችን እንደወረዱ እንዲጠቀሙ ማድረግ እንጂ ብዙ ጊዜ በቀላሉ በአካባቢ የሚገኙ ምግቦችን ማቅረብ የተለመደ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ለተለያዩ በሽታዎች የማጋለጥ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ላይ ያጋጠማችሁ ነገር አለ?
አቶ አብነት፡- ችግራችን ምን መሰለህ በዘርፉ ዕውቅና የሌላቸው ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም የምክር አገልግሎት ለመስጠት የሚሞክሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከሙያው ጋር የሚጣረሱ መረጃዎችን ለማኅበረሰቡ ያደርሳሉ፡፡ ውፍረትን ለመቀነስ የተለያዩ ነገሮችን በጥብጣችሁ ጠጡ እያሉ ያለ በቂ ዕውቀት በማኅበራዊ ሚዲያ ምክር የሚሰጡ ሰዎች መበራከት ችግሩን እያባባሱት ነው፡፡ እንደዚህ የምልህ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎች በቲክቶክና በሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያዩትን መረጃ በመከተል ያልሆነ ነገር ጠጥተው በከፍተኛ ሁኔታ ታመው ከእኛ ዘንድ መጥተው የገጠማቸውን ችግር ስላካፈሉን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህንና መሰል የተሳሳቱ መረጃዎች ለማኅበረሰቡ ሲደርሱ የእናንተ ምላሽ ምን ነበር?
አቶ አብነት፡- እንደዚህ ዓይነት የተሳሳቱ መረጃዎች ሲበራከቱ እኛም በተለያዩ ሚዲያዎች በመቅረብ የተለያዩ ሙያዊ አስተያየቶችንና ትምህርቶችን በመስጠት ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚህ ባሻገር ትኩረታቸውን በምግብ ላይ አድርገው የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሲመጡ አብረን በመሥራትና የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ለሕፃናትና ለአዋቂዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን እንሰጣለን፡፡
ሪፖርተር፡- አመጋገባችን ምን መምሰል አለበት ትላለህ?
አቶ አብነት፡- ምናልባት የአመጋገብ ሁኔታዎችን ይለያዩ ይሆናል እንጂ የሰው ልጅ ሳይበላ አይኖርም፡፡ በየቀኑ የሚወሰዱ ምግቦች ደግሞ ጉዳትም ጥቅምም አላቸው፡፡ ስለዚህ ምን መደረግ አለበት ለሚለው ዝቅተኛ የሚባል ገቢ ላለው የማኅበረሰብ ክፍል በቂ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር መንግሥት በስፋት መሥራት ይኖርበታል፡፡ አገራችን ደግሞ ለዚህ የሚሆን በቂ የእርሻ ቦታ ባለቤት ናት፡፡ የሰው ኃይሉም ገና አልተነካም፡፡ ነገር ግን ይህንን አስተባብሮና አጠናክሮ በመሥራት ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰቡ ክፍል አንዴ አገር የምግብ ፍጆታቸውን እንዳሟሉ በስፋት መሠራት አለበት ባይ ነኝ፡፡ ነገር ግን ሰዎች ባላቸው አቅርቦት እንዴት መጠቀም አለባቸው ለሚለው በየዕለቱ የሚመገቡትን ምግብ በተቻለ መጠን በቀላሉ የሚገኙ ምግቦችን መጠቀም ለጤንነት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ በሌላ በኩል የተሻለ የምግብ አቅርቦት ያላቸው ሰዎች የምግብ እጥረት ሳይሆን የአመጋገብ ችግር ነው ያለባቸው፡፡ ብዙ ሰዎች መወፈር ምቾት መስሎ የሚታያቸው አሉ፡፡ መወፈር በራሱ ችግር ባይኖረውም ነገር ግን ከመወፈር ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎች አሉ፡፡ ከውፍረት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎች ደግሞ በሕክምና የሚሻሻሉ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የስኳር በሽታ ከሕክምና ይልቅ የተስተካከለ አመጋገብን በመከተል ማሻሻል በእጅጉ ውጤታማ ነው፡፡ በሌላ በኩል ረጅም ዕድሜን ከጤና ጋር ለመኖር ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የእግር ጉዞና ሌሎች ሥራዎችን መሥራት ተገቢ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የምግብ እጥረት እንደ አገር ምን ዓይነት ችግሮችን ያመጣል ትላለህ?
አቶ አብነት፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በሁለት በኩል የሚቆርጥ መጋዝ ነው ያለው፡፡ ይህ ማለት ግማሹ ማኅበረሰብ በረሃብ ሲሰቃይ ቀሪው ደግሞ ከአመጋገብ ዕውቀት ማነስ የተነሳ በበሽታ እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ ስለዚህ የተመጣጠነ ምግብ ሳያገኙ የሚያድጉ ሕፃናት እንደ አገር የማሰብና የመሥራት አቅሙ ዝቅተኛ የሆነ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ምግብን መመገብ ብቻ ሳይሆን የአመጋገብ ሥርዓትንም ማስተካከል ተገቢ ነው ባይ ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- በድርጅታችሁ ምን ዓይነት ምግቦችን ነው የምታቀርቡት?
አቶ አብነት፡- ቀደም ሲል እንደነገርኩህ ሙሉ በሙሉ የአገር ውስጥ ምርት ውጤቶችን በመጠቀም የሕክምና ባለሙያ በሚያዛቸው መሠረት በማቅረብና ቤታቸው ድረስ በማድረስ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ በዚህም ብዙ ሰዎች ካለባቸው ሕመም በምግብ ብቻ እንደዳኑ ለማየት ችለናል፡፡
