
February 16, 2025

የቁም እንስሳት አቅራቢ ነጋዴዎች በደረሰኝ እንዲሸጡ መንግሥት ትዕዛዝ በማስተላለፉ ምክንያት፣ ሥጋ ላኪዎች የአቅርቦት ችግር እንደገጠማቸውና ከገበያ ውድድር ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሥጋት እንዳላቸው ተናገሩ፡፡
የአቢሲኒያ ቄራ ድርጅት ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ መንግሥት የቁም እንስሳት የሚያቀርቡ ነጋዴዎችን በአንድ ጊዜ በደረሰኝ እንድትሸጡ በማለቱ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቁም እንስሳት የግብይት ሥርዓት የዘመነ አለመሆኑንና ከሌሎች አገሮች አሠራር ጋር የሚሄድ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
የቁም እንስሳት የሚያቀርቡ ነጋዴዎች እንስሳቱን የሚሰበስቡት ከአርሶ አደሮችና ከደላሎች በመሆኑ፣ ለላኪዎች ሲያቀርቡ በደረሰኝ እንዲሆን እንደማይፈልጉና ድርጅታቸው ከዚህ በፊት ከአንድም ሁለት ጊዜያት ከደረሰኝ ውጪ አልገዛም ብሎ ከአቅራቢዎች ጋር ድርድር ቢያቀርብም መልካም ምላሽ አለማግኘቱን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት የቁም እንስሳት ግብይት በደረሰኝ እንዳልነበረና ያልተለመደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ላኪዎች ሥራቸውን ሊያቆሙ ይችላሉ ብለዋል፡፡
ሁኔታው በዚህ ከቀጠለና ሥጋ ላኪዎች የአገር ውስጥ የአቅርቦት ችግር ከገጠማቸው፣ ከሌሎች አገሮች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚቸገሩና የውጭ ገበያውም ሊወሰድባቸው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የአቢሲኒያ ቄራ ድርጅት ለረዥም ዓመታት በዋጋም ሆነ በጥራት የውጭ ገበያውን ሲመራ መቆየቱን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፣ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎች በኮንትሮባንድ የቁም እንስሳት በከፍተኛ መጠን ይወጡ ስለነበር ድርጅታቸው የአቅርቦት ችግር ገጥሞት ለስምንት ወራት ያህል ሥራ አቁሞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በወቅቱ በርካታ የቄራ ድርጅቶች ሥራቸውን አቁመው እንደነበር፣ በቅርቡም መንግሥት ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሠረት አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ወደ ሥራ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በርካታ ላኪዎች ወደ ገበያው መግባት ሲገባቸው ኬንያ በጥራትም ሆነ በሽያጭ ከኢትዮጵያ ላኪዎች በልጣ መገኘቷን ገልጸው፣ አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ኪሎ የኬንያ ሥጋ ሰባት ዶላር ከአርባ ሳንቲም እየተሸጠ ነው ብለዋል፡፡
አንድ ኪሎ የኢትዮጵያ ሥጋ ግን በሰባት ዶላር እየተሸጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ከአንድ ዓመት በፊት የአቢሲኒያ ቄራ ድርጅት አንድ ኪሎ ሥጋ ስድስት ዶላር ከሃምሳ ሳንቲም ሲሸጥ፣ የኬንያ በአምስት ዶላር ከስልሳ ሳንቲም ይሸጥ እንደነበር አክለዋል፡፡ የአቢሲኒያ ቄራ ድርጅት የፍየልና የበግ ሥጋ ወደ ዓረብ አገሮች እየላከ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የሥጋ ላኪዎች ማኅበር ጉዳዩን በተመለከተ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካል ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን በመግለጽ፣ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ከመንግሥት ጋር ውይይት እየተደረገበት መሆኑን፣ ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ እንዳላገኙትና ችግሩ ሲፈታ እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የገቢዎች ሚኒስቴር የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች በስልክ ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡