
By አንባቢ
February 16, 2025
በቶማስ በቀለ
ይቺ አገራችን ብዙ ተብሎላታልም፣ ብዙ ተወርቶባታልም፣ አገሪቱ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አገር (ላይቤሪያን ጨምሮ) ከመሆኗ አኳያ የሚነገርላት ብዙ ጥሩና የሚገርሙ ነገሮች ያሉትን ያህል፣ ከረሃብ ከጦርነትና ከድህነት ጋር ተያይዞ ደግሞ ክብረ ነክና አሳዛኝ የሆኑ ነገሮች ሲነገሩ እንሰማለን፡፡ እስቲ ከነዚህ ጉዳዮች ለአጠቃላይ ግንዛቤ ሁለቱን በዚህ አጭር ጽሑፌ ውስጥ አንስቼ በእነሱ ላይ የተወሰኑ ሐሳቦች ልስጥ፡፡
ዕርዳታ በኢኮኖሚ ያደጉ አገሮች ላላደጉት አገሮች የተለያዩ ዓይነት ዕርዳታዎች እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ ጽሑፌ በሁለቱ ላይ ማለትም ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚጠቅም ዕርዳታ (Development Aid) እና ለዕለት ፍጆታ የሚውል ዕርዳታ (Subsistence Aid) በሚባሉት ላይ ያተኩራል፡፡ ይህን ታሪክ የሰማሁት በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ ነው፡፡ ስለ ዕርዳታ ዓይነቶች በተለይም ‹‹Development Aid›› እና ‹‹Subsistence Aid›› በተባሉት የዕርዳታ ዓይነቶች ላይ ለማን እንደሚሰጥ የሚወያይ በምዕራብ አገሮች በአንዱ በተካሄደ ብዙ አገሮችን ያሳተፈ አንድ ትልቅ ስብሰባ መካሄዱን አንድ ጓደኛዬ አጫወተኝ፡፡ ከዚያም ጓደኛዬ ጨዋታውን እንዲህ ቀጠለ፡፡ ‹‹በስብሰባው ላይ ‹‹Development Aid›› እና ‹‹Subsistence Aid›› ስለተባሉ የዕርዳታ ዓይነቶች በሰፊው ማብራሪያ ተሰጠ፡፡ በመቀጠልም የትኞቹ አገሮች የትኛውን የዕርዳታ ዓይነት እንደሚሰጣቸው በአጭሩ ማብራሪያ ተሰጠ፡፡ በስብሰባው ላይ ከኢትዮጵያ የተሳተፉ ተወካዮች ነበሩ፡፡ በአጋጣሚ የኢትዮጵያ ስም በስብሰባው ላይ አልተነሳም፡፡ በመሆኑም በውይይቱ ሰዓት ከኢትዮጵያ ከሄዱ አንዱ ተወካይ እጁን አነሳ፡፡ ተራው ሲደርስ ሐሳቡን እንዲያቀርብ ዕድል ተሰጠው፡፡ ከዚያም እጁን ያነሳው ተወካይ ስለ ‹‹Development Aid›› እና ‹‹Subsistence Aid›› የተሰጠን ማብራሪያ ጥሩ ግንዛቤ እንድናገኝ ረድቶናል፡፡ የትኞቹ አገሮች የትኛውን ዓይነት ዕርዳታ እንደሚያገኙ ተገልጾልናል፡፡ ከተጠቀሱት አገሮች ውስጥ ግን ኢትዮጵያ የለችም፡፡ እውነታው ግን ኢትዮጵያ የሚሰጣት ‹‹Subsistence Aid›› (ለዕለት ፍጆታ የሚጠቅም) ነው፡፡ በእሱ በኩል ችግር የለብንም፡፡ ‹‹Development Aid›› (ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚረዳ ዕርዳታ) ግን አግኝታ አታውቅም፡፡ ሁልጊዜ ‹‹Subsistence Aid›› እየሰጣችሁን ከምናስቸግራችሁ ‹‹Development Aid›› ሰጥታችሁን ኢኮኖሚያችን እንዲያድግ ብታደርጉ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት አይሆንም ወይ?›› የሚል መንፈስ ያለው ጥያቄ ጠየቀ፡፡ ከዚያም ዋናው አወያይ ፈረንጅ ቀበል አደረገና ፍርጥም ብሎ ‹‹Excuse me sir, we don’t want to create another Japan›› በአማርኛ ሲተረጎም ‹‹ይቅርታ አድርጉልኝ ጌታው፣ ሌላኛዋን ጃፓን መፍጠር አንፈልግም›› አለው ብሎ አጫወተን፡፡
አንባቢ የሰብሳቢውን አባባል በጥሞና እንዲመረምር እፈልጋለሁ፡፡ ምን ማለቱ ነው? ለምን ኢትዮጵያ ከጃፓን ጋር ተወዳደረች? ለምን ኢትዮጵያ እንደ ጃፓን እንድታድግ አልተፈለገም? ምን አስፈራው? ይህ ለኛስ ለኢትዮጵያውያን ምን ይነግረናል? አገራችን በቅኝ የተገዛች አገር አይደለችም፡፡ ሕዝቡ ከነኩት የጦረኝነትና የአትንኩኝ ባይነት ሥነ ልቦና ያለው ነው፡፡ ጃፓን በሁለተኛ የዓለም ጦርነት የጦረኝነት መንፈስ ባላቸው የሚሊታሪ ጄኔራሎች የተሞላች ስለነበረ ከጀርመን ናዚና ከጣሊያን ፋሺስት ጋር በማበር የቃል ኪዳን አገር የተባሉትን አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ሌሎች አገሮችን መውጋቷና በዚህ መነሻነት የአቶሚክ ቦምብ በሂሮሺማና ናጋሳኪ ከተሞቿ ላይ እንደተጣለ በታሪክ ይታወቃል፡፡ በመጨረሻም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተጠናቆ እነ ጃፓን እጃቸውን ከሰጡ በኋላ ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ በእነጃፓን ላይ የመሣሪያ ማዕቀብ ስትጥል፣ ለካሳ በሚል ለጃፓን ‹‹Development Aid›› ሰጠች፡፡ ጃፓኖቹም በጦርነት ሐሳብ የተሞላ ህሊናቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ኢኮኖሚ ግንባታ በማዞራቸው አሁን የደረሱበት የዕድገት ደረጃ ደረሱ፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮጵያም ‹‹Development Aid›› ካገኘች የማደግ አቅም፡፡ ማለትም፣ የተፈጥሮና የሰው ሀብት ስላላት ማደግ ትችላለች፡፡ ይሁን እንጂ በታሪኳ ክብሬን አላስነካም ባይነቷ፣ ለሌሎች ጥቁር ሕዝቦች አርዓያ ከመሆን አቅሟና በተለያዩ የፖለቲካ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ማደግ ስለማይፈለግ ‹‹Development Aid›› ማግኘት አልቻለችም፡፡ እንደ ቻይናም በራሷ ጥረት እስካሁን ድረስ ማደግ አልሆነላትም፡፡ በመሆኑም ሌላውን ትናንሽ ነገር ሁሉ ትተንና ያገኘነውን አጋጣሚና የራሳችንን ጥረት ተጠቅመን ከድህነት የምንወጣበት መንገድ ላይ ብናተኩር ያዋጣናልና ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡
ጦርነት በዓለማችን ላይ ከተካሄዱ ጦርነቶች መካከል ሁሉም ጦርነቶች ከጥፋት፣ ከውድመትና ከሰቆቃ ውጭ የፈየዱት ምንም ጥሩ ነገር እንደሌለ ታሪክ በተደጋጋሚ ያረጋገጠው ሀቅ ነው፡፡ ምናልባት ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር ያደረገችው ዓይነት ጦርነት ከተወራሪው ማለትም ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ ትክክለኛ ጦርነት ነው ቢባልም ጦርነት ነውና የመጨረሻው ውጤቱ ግን በሰቆቃ የተሞላ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ በአንዱ ወገን በሚታይ ጀብደኝነት ወይም ተቀራርቦ ባለመወያየት ምክንያት በሚፈጠሩ ጦርነቶች ዓለማችን ቁም ስቅሏን ማየቷ አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡
እስኪ ካደጉ አገሮች በአንዱ ውስጥ በተደረገ ኢንተርናሽናል ስብሰባ ላይ ስለተነሳ አንድ ጉዳይ ላጫውታችሁ፡፡ ስብሰባው የሦስተኛ ዓለም አገሮች በኢኮኖሚ ያላደጉት ለምንድነው? በሚለው ርዕስ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነት ያላቸው ባለሙያዎች በሦስተኛ ዓለም አገሮች ላይ ተመድበው (አንድ ባለሙያ ለአንድ አገር) ዝርዝር ጥናት ካደረጉ በኋላ የባለሙያዎቹ ሪፖርት የሚሰማበት ስብሰባ ነበር፡፡ ይህንን ታሪክ የሰማሁት በ1988 ዓ.ም. ነበር፡፡ በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱት የሦስተኛ አገሮች ውስጥ አንዷ የእኛው ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ በመቀጠል በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት አገሮች ሪፖርት አንድ በአንድ መቅረብ ጀመረ፡፡ በመሀከል የኢትዮጵያ ተራ ደረሰ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ጥናት አድርጎ ሪፖርት ያዘጋጀው ባለሙያ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ማደግ ያልቻለችበት ምክንያቶችን አንድ በአንድ ካቀረበ በኋላ ከምክንያቶቹ ዋናው ብሎ ያቀረበውን ምክንያት በሚቀጥለው አኳኋን ገለጸ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ባለፉት 800 ዓመታት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ለአንዲት አሥር ተከታታይ ዓመታት እንኳን ከጦርነት ነፃ የሆነችበት ጊዜ የለም፡፡ ጦርነት ባለበት ቦታ ደግሞ የኢኮኖሚ ዕድገት አይታሰብም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ያላደገችበት ዋና ምክንያት ታሪኳ በተለያዩ ጦርነቶች የተሞላ በመሆኑ ነው፤›› ብሎ ሪፖርቱን ማጠናቀቁን ጓደኛዬ አጫወተኝ፡፡ ይህን ታሪክ ስሰማ ገረመኝ፣ አዘንኩም፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ ታሪክ በጦርነቶች የተሞላ ታሪክ እንደሆነ አውቀዋለሁ፡፡ በጣም የገረመኝ ግን በስምንት መቶ ዓመት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ለአንዲት አሥር ተከታታይ ዓመታት እንኳን ከጦርነት ነፃ የሆነችበት ጊዜ የለም የሚለው እውነታ ነው፡፡ ያስደነግጣል፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት ይህን ታሪክ የሰማሁት በ1988 ዓ.ም. ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ከሻዕቢያና ሕወሓት ጋር ይደረጉ የነበሩ ጦርነቶች በመቆማቸው ታሪኩን እስከ ሰማሁበት ጊዜ ድረስ ለአምስት ዓመታት፣ አገሪቱ በአንፃራዊነት በሰላም ውስጥ ነበረችና ከ800 ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ለአሥር ተከታታይ ዓመታት ከጦርነት ነፃ ልትሆን ነው ብዬ በጉጉት እየጠበቅሁ እያለሁ በሚያሳዝን ሁኔታ በሰባተኛ ዓመት ማለትም በ1990 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ ገባች፡፡ በመቀጠል በ1997 ዓ.ም. በተፈጠረው የምርጫ ሸፍጥ መነሻነት በአገሪቱ ትርምስ ተፈጥሮ የተወሰኑ ወገኖች ነፍጥ ይዘው ጫካ ገቡ፡፡ ከ1990 ዓ.ም. የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ካበቃ በኋላም አሥር ዓመት ሳይሞላው ወደ ጦርነት መግባታችንን አንባቢ ልብ ይበል፡፡ ከዚያም ነፍጥ ያነሱት በሽምቅ ውጊያቸው ላይ እያሉ በ2008 ዓ.ም. በወያኔ ሥርዐት ላይ የተፈጠረው ተቃውሞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በሒደት በ2010 ዓ.ም. የሪፎርም ለውጡ ተካሂዶ ለአንድ ዓመት ከምናምን ያህል ሰላም ካገኘን በኋላ በተለያዩ አካላት የሚታገዘው ሸኔ በየቦታው ችግር መፍጠር ጀመረ፡፡ በሪፎርም ለውጡ የፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣኑን የተነጠቀው ሕወሓት በ27 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ያጠራቀመውን መሣሪያና ከሌሎች የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ከፍቶ ለሁለት ዓመታት ያህል መከራችንን አየን፡፡ ከሕወሓት ጋር በፕሪቶሪያ ከተደረገው የሰላም ስምምነት አንስቶ ለተወሰኑ ወራት ዕፎይ ካልን በኋላ የአማራው ፋኖ ጥያቄዎቼ አልተመለሱም በሚል በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ጦርነት ከፈተ፡፡ አሁንም አንባቢው ልብ እንዲለው የምፈልገው ነገር እስካሁን ማለትም እስከ 2015 ዓ.ም. መገባደጃ ቀናት ድረስ አገራችን ለአንዲት አሥር ዓመታት ጊዜ ያህል እንኳን ሰላም አጥታ የመከራ ጊዜዋን እየገፋች መሆኑን ነው፡፡
በአሁን ወቅት ሁላችንም በተለይ መንግሥትና የተቃዋሚ ወገኖች የተለያዩ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች ምን እያደረግን እያለን እንደሆነ ቆም ብለን የምንመረምርበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡ (እዚህ ውስጥ ሕዝቡን (The Silent Majority የሚባለውን) ማስገባት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም እሱ በብሔር፣ በሃይማኖትና በተለያዩ ነገሮች ሳይከፋፈል ተደጋግፎ፣ ተቻችሎና ተዛዝኖ የመኖር የቆየ ባህሉን ይዞ እየተጓዘ እንደሆነ ስለማውቅ ነው፡፡ ማለትም የሚባለው ኤሊቱ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በኤሊቱ መባላት ገፈት ቀማሹ ሕዝቡ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በላይ እንደጠቀስኩት የኢትዮጵያን ታሪክ የመረመረው ባለሙያ ኢትዮጵያ ባለፉት 800 ዓመታት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ለአንዲት አሥር ተከታታይ ዓመታት እንኳን ከጦርነት ነፃ የሆነችበት ጊዜ የለም ያለውን ታሪክ አሁን ያለው ትውልድ በ1988 ዓ.ም. ላይ 27 ዓመታት ጨምሮ ኢትዮጵያ ባለፉት 827 ዓመታት ውስጥ በየትኛውም ጊዜ ለአንዲት አሥር ተከታታይ ዓመታት እንኳን ከጦርነት ነፃ የሆነችበት ጊዜ የለም ወደሚለው ታሪክ ለውጦታል፡፡ይሄ ነው ለአገራችን የሰጠናት የዘመኑ ስጦታ!
ታዲያ ምን እያደረግን ነው? አገሪቷን ወዴት እየወሰድናት ነው? ይህ ሥራችን አላዋቂ አያስብለንም? 827 ዓመታት ባልነው ላይ አሁንም ሌላ ዓመታት መጨመር እንፈልጋለን? ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አለማደግ ዋናው ምክንያት ጦርነት መሆኑን እያወቅን፣ እየተነገረን የሐሳብ ልዩነቶቻችንን በጦርነት ለመፍታት መሞከራችን ለአገሪቷ ይበጃል ትላላችሁ? እርስ በርስ በተዋጋንበት ጊዜ ሁሉ ሕዝብ ከማስጨረስና አገር ከማራቆት ውጭ የፈታነው ችግር አለ? (በነገራችን ላይ ይህ ጥያቄ በተለያየ ምክንያት ኢትዮጵያ በብሔርና በሃይማኖት ሳትከፋፈል በአንድነት ወደ ትልቅ የኢኮኖሚና የሠለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዳታድግ የማይፈልጉ ወገኖችን (ካሉ ማለቴ ነው) አይመለከትም)፡፡
በመሆኑም ይድረስ ለመንግሥት ተቃዋሚ ወገኖችና አክቲቪስቶች የእናንተ የሐሳብ ልዩነት አገሪቷ ሰላም በመሆኗ ሊመጣ ከሚችለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ባህል ዕድገት ጋር ሲነፃፀር ኢምንት ነው፡፡ ይህንን እናንተም ትቀበሉታላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ በሌላ አነጋገር ለአገራችሁ ሰላም ስትሉ የሐሳብ ልዩነቶቻችሁን በማቻቻል (Compromise በመደራረግ) በክብ ጠረጴዛ እንደምትፈቱት አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ ሕይወት ሳይቀጠፍና የአገር ሀብት ሳይወድም፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሐሳብ ልዩነቶቻችሁን በክብ ጠረጴዛ እንድትፈቱና ወደ ሠለጠነ የፖለቲካ ባህል እንድታሻግሩን በኢትዮጵያ በአገራችን ስም እማፀናችኋለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው thomasbekeleol@gmail.com. ማግኘት ይቻላል፡፡