February 16, 2025

ርዕሰ አንቀጽ

የአፍሪካ ኅብረት 38ኛው የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ሲካሄድ ብዙ ትዝ የሚሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ እጅግ በጣም አሰልቺ፣ ውጣ ውረድ የበዛበትና ታላቅ ተጋድሎ ተደርጎበት ከከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በኋላ በአዲስ አበባ ምሥረታው በ1955 ዓ.ም. የተካሄደው የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጀት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት የታላቁ የዓድዋ ጦርነት ድል ውጤት ነበር፡፡ በጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ወደር የሌለው መስዋዕትነት በዓድዋ ተራሮች ውስጥ በዘመኑ ኃያል ቅኝ ገዥ ላይ የተገኘው አንፀባራቂው ድል፣ በመላው ዓለም በሚገኙ ጥቁር ሕዝቦችና በቅኝ ግዛት በሚማቅቁ ወገኖች ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ሲሰማ ኢትዮጵያ የግፉዓን ተምሳሌት ሆና ስሟ አስተጋባ፡፡ ለአርነት የሚፋለሙ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ የደቡብ አሜሪካ፣ የእስያና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጭምር የነፃነት ምሳሌ አደረጓት፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ጅማሮ መሠረት የሆነው ታላቁ የዓድዋ ድል ነበር፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካውያን መሰባሰቢያና የኅብረቱ መቀመጫነትን ክብር ያጎናፀፋት፡፡

ብዙዎቹ አፍሪካውያን በተለያዩ መድረኮች ሲያረጋግጡ እንደኖሩትና ሰንደቅ ዓላማዋን እንደተጋሩት፣ ኢትዮጵያ የነፃነታቸው ዓርማና ምልክት ከመሆን አልፋ የሚኮሩባት እናታቸው ነበረች፡፡ ይህንን የመሰለ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን መክቶ ከማባረር ባሻገር፣ በዘመኑ አስፈሪ የነበረውን የአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይል አከርካሪውን በመስበር በዓለም አደባባይ ደማቅ አሻራ አሳርፋለች፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር እንዲላቀቁ ዕገዛ በማድረግና የጋራ መሰባሰቢያ ማኅበር እንዲኖራቸው በተደረገ ጥረት፣ ከአፍሪካ ኅብረት በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጽሕፈት ቤት የተለያዩ ድርጅቶችና በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ በማድረግ አዲስ አበባ እንደ ኒውዮርክና ጄኔቭ የዓለም መናኸሪያ ሆናለች፡፡ ይህ ሁሉ ክብር የተገኘው ከራሳቸው ይልቅ ለአገራቸው ከፍተኛ ፍቅር በነበራቸው ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ነው፡፡

በአርቆ አሳቢዎቹና በጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ የአፍሪካውያን የጋራ መሰባሰቢያ ለመሆን የበቃችው ኢትዮጵያ፣ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ከገባችበትና አሁንም አጠናክራ ካስቀጠለችው የጥፋት አዙሪት ውስጥ መውጣት ካልቻለች የዘመናት ልፋት ከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ምንም ዓይነት ዓላማ፣ ራዕይ፣ ሕልም ወይም ሌላ ዕሳቤ ይኑራቸው ከራሳቸው በላይ ኢትዮጵያ እንዳለች በውል ካልተገነዘቡ ፍላጎታቸው ሁሉ መና ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ስህተቶችን እየደጋገሙ ውጤት መጠበቅ እንደማይቻለው ሁሉ፣ ከተለመደው የጥፋት አዙሪት ውስጥ ለመውጣት ፍላጎት አለማሳየት የእነዚያን ሩቅ አሳቢዎች ልፋትና መስዋዕትነት ማኮላሸት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከእነ ልዩነቶቻቸው በጋራ ለታላቅ ድልና ክብር ያበቁ ጀግኖች ታሪክ ተከብሮ እንዲኖር ማድረግ ሲገባ፣ የልዩነትና የጥፋት መንገድ ተከትሎ አፍሪካውያን ፊት በድፍረት መቆም አይቻልም፡፡ ይሞከርም ቢባል አፍሪካውያን ራሳቸው ይታዘባሉ፡፡

መሰንበቻዋን አምራና ተውባ አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች ስታስተናግድ እንደ ሰነበተችው አዲስ አበባ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሄዱ ጦርነቶች፣ ግጭቶች፣ ጥቃቶች፣ ዕገታዎች፣ ግድያዎች፣ ዝርፊያዎችና ሌሎች እኩይ ድርጊቶች ባይኖሩ ኖሮ እንግዶቹ በአምስቱም በሮች ያለ ሥጋት ወጥተው ዘና እያሉ ሌሎች አካባቢዎችም የበረከቱ ተቋዳሽ ይሆኑ እንደነበር ማንም አይስተውም፡፡ ነገር ግን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረው አገርን የማስቀደም፣ የመከባበር፣ የመተሳሰብ፣ ልዩነትን አቻችሎ እንግዳን ተቀብሎ የማስተናገድና መሰል ማኅበራዊ እሴቶች ተበጣጥሰው ሥጋት መንሰራፋቱ በእጅጉ ያስቆጫል፡፡ በኢትዮጵያ ዙሪያ ገብ ጉዳዮች በጨዋነትና በስክነት መነጋገር አቅቶና በቆላም በደጋም ሰላም ጠፍቶ፣ ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ የማያስችል ጭንቅ ጊዜ ውስጥ መገኘት ያሳቅቃል፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለአገራቸው የሚያቆም አማካይ ጠፍቶባቸው፣ አፍሪካውያንን እየተታኮሱና እየተኮራረፉ ማስተናገዳቸው በታሪክና በመጪው ትውልድ ጭምር ትዝብት ውስጥ የሚከት ኃፍረት ነው፡፡

ከእንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመውጣት ምን ይደረግ ተብሎ በሀቅና በቅንነት ለመነጋገር መድረክ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን የሚያስፈልጋት በጠመንጃ መነጋገር ሳይሆን፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሚሰነዘሩ ጠቃሚ ሐሳቦች ላይ በጥልቀት መምከር ነው፡፡ ምክክሩ የይስሙላ እንዳይሆንም ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚወክሉ ያልተንዛዙና ዘመኑን የሚዋጁ ሐሳቦች ላይ ቢተኮር ይመረጣል፡፡ የዘመኑ ሰው የራሱን ታሪክ መሥራት ሲገባው ያልኖረባቸውን ጊዜያት የታሪክ ክስተቶችን እየመዘዘ ሲጣላ ከሥልጣኔ መራቅን ነው የሚያሳየው፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ ምሁራንና ልሂቃን ከበፊቱ መልካሞቹን በመንቀስና የማይጠቅሙትን በስምምነት በመተው፣ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት እጅና እግሯን አስሮ ከሚያሰቃያት መከራ ውስጥ ማውጣት አለባቸው፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪዎቹ፣ እንዲሁም በትጥቅ ጭምር የሚፋለሙ ወገኖች ጭምር ለኢትዮጵያ ህልውና ሲሉ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ልዩነቶቻቸውን ይዘው ይነጋገሩ፡፡

አፍሪካውያን የነፃነታችን እናት እያሉ የሚመኩባት ኢትዮጵያ ከገባችበት የግጭት አረንቋ ውስጥ መውጣት አለባት፡፡ ለሦስተኛው የዓለም ጦርነት መነሳት ምክንያት ይሆናል ተብሎ የተፈራውን የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ለመቋጨት ጫፍ ላይ ተደርሶ፣ የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል የሆነችው ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ የምትዳክርበት ምንም ዓይነት ምክንያት መኖር የለበትም፡፡ ከታሪካዊ ጠላቶች በስተቀር አፍሪካውያንም ሆኑ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወኪሎች በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ሲገኙ፣ ከምንም ነገር በላይ የሚያሳስባቸውና የሚያስጨንቃቸው የኢትዮጵያ ሰላም ማጣት ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም አጥታ በሥጋት ውስጥ መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን በመረዳት፣ ለህልውናዋ ሲባል ሁሉም አለመግባባቶችና ግጭቶች በፍጥነት መላ ይፈለግላቸው፡፡ የግጭት አዙሪት ውስጥ ሆኖ የአፍሪካ ማዕከል መሆን ያዳግታልና!