እኔ የምለዉ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በባለሙያ ዓይን

አንባቢ

ቀን: February 16, 2025

(በጎ ጎኖችና እርምት የሚፈልጉ ጉዳዮች)

በዮሐንስ መኮንን

በጥር ወር 2016 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዋና ዋና ኮሪደሮችን በማዘመን ከተማዋን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ምቹ ያደርጋታል የተባለ ፕሮጀክት በ43 ቢሊዮን ብር መጀመሩ የታወሳል። የፕሮጀክቱ ከተማዋን እንደ አዲስ መልክ በማስያዝ ዘመናዊ ሜትሮፖሊታንና የቱሪዝም ማዕከል ማድረግን ያለመ መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል። ፕሮጀክቱ አዳዲስ የመኪና፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶችን፣ አረንጓዴ መናፈሻዎችን፣ እንዲሁም ድልድዮችን በመገንባት የከተማዋን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ከፍ የሚያደርግ ከባቢ ለመፍጠር ያለመ መሆኑም እንዲሁ፡፡

ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ድጋፍና ተቃውሞ ማስተናገዱ አልቀረም። ትችቱና ምሥጋናው በሁለት ወገን ከፍሎ ማየት የሚቻል ሲሆን፣ የባለሙያዎችና የሌሎች ብሎ መለየት ይቻላል። ባለሙያዎች ፕሮጀክቱን በጥቅሉ በበጎ ጎኑ ተቀብለው ሊሻሻሉ ይገባቸዋል የሚሏቸውን ከሕግና ከሳይንስ አንፃር ሙያዊ ሐሳብ የሚያጋሩ ሲሆን፣ ሌሎች ያልኳቸው ደግሞ ጉዳዩን ከፖለቲካዊ ትርፍና ኪሳራ አንፃር ብቻ በመመዘን ወይ ጠቅልለው የሚያመሠግኑ፣ ወይም በተቃራኒው ጠቅልለው የሚወቅሱ ናቸው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ፕሮጀክቱን ከሙያዊና ከሕጋዊ መርሆዎች አንፃር በመቃኘት ሊታረሙ የሚገባቸው ጉዳዮችን ለይቶ ማሳየት ነው፡፡

የፕሮጀክቱ በጎ ጎኖች

የኮሪደር ልማቱ ዋነኛ ትሩፋት ተደርጎ የሚወሰደው አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ሳቢና ተመራጭ ከተማ በማድረግ፣ ቱሪዝምንና ኢንቨስትመንትን እንድትስብ ማድረጉ ነው። ዘመናዊ መሠረተ ልማት የሆኑት መንገዶች፣ የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች፣ የተሳለጠ የመገናኛ አውታሮችን መገንባት ከተማዋን የኢኮኖሚ ዕድገት ማዕከል ያደርጓታል። ከዚህም በተጨማሪ ፕሮጀክቱ የከተማዋን ልማት ያልተማከለ በማድረግ በተወሰኑ የከተማዋ ማዕከላት ላይ ተወስኖ የነበረውን መጨናነቅ የማስተንፈስ አቅም አለው።

የፕሮጀክቱ ሌላኛው ትሩፋት የኢኮኖሚ ዕድገትን ማነቃቃቱ ነው፡፡ የአዳዲስ መሠረተ ልማቶች ዝርጋታን ተከትሎ ከፍ ያሉ የኢኮኖሚ ዕድሎች ይመጣሉ። የተሻሻሉ መንገዶች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሕንፃዎችና የሕዝብ መገልገያዎች የአገር ውስጥና የውጭ አልሚዎችን እንደሚስቡ ይጠበቃል። ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ታድሰው መቅረባቸው የአገልግሎት ፍላጎትን ይጨምረዋል። ይህም አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ስለሚያሰፋ በተለይ የሪል ስቴትና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት (ለምሳሌ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶችና የሽያጭ መደብሮች ወዘተ) እንዲነቃቁና እንዲስፋፉ ዕድል በመክፈት አዲስ አበባን በምሥራቅ አፍሪካ ሳቢ የኢኮኖሚ ማዕከል የማድረግ አቅም አለው። ፕሮጀክቱ ሥራን በመፍጠር፣ የተሻሻለ የመኖሪያ አካባቢን በመፍጠርና የከተማዋን ገጽታ በማዘመን ንቁና ሳቢ የከተማ ከባቢን ይፈጥራል።

የተሻሻሉ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች የከተማዋ ዋነኛ ችግር የሆነውን የትራፊክ መጨናነቅ በተወሰነ ደረጃ ይቀርፉታል። ከዚህም በተጨማሪ የተሻሻለ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ምርትን ከማሳደጉም በላይ ከተማዋን ለእንቅሰቃሴ የተመቸች ያደርጋታል። ከተማዋን ማዘመን ቀልጣፋ የግንኙነት መስመሮችን አንድትዘረጋ ያስችላታል። የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ ተጨማሪ የመኪና ማቆሚያዎችና የሕዝብ ትራንስፖርት መገልገያዎች ቦታዎች የፕሮጀክቱ አካል መሆናቸው የተሟላ የከተማ መሠረተ ልማትን በፍትሐዊነት ለነዋሪዎች ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው። ይህም ተደራሽ ያልነበሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ከማስታወሱም በተጨማሪ፣ በሒደት የተጋነነ የጥራት ልዩነት የነበራቸውን የመኖሪያና የመሥሪያ መንደሮች በማቀራረብ ፍትሐዊ የከተማ ከባቢን የመፍጠር ዕድል አለው።

ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ በከፊል ከላይ የተዘረዘሩት ጥቅሞች ቢኖሩትም፣ አፈጻጸምን ተከትሎ በሚታዩ ጉድለቶች ምክንያት ከትችት ሊያመልጥ አይችልም። እነዚህም ትችቶች በዋነኛነት ከባለድርሻዎች ተሳትፎ ማነስ፣ ከአካባቢ ዘላቂነት፣ ከቅርስ አያያዝና ከኪነ ሕንፃ ፍልስፍና አንፃር የሚታዩ ናቸው።

ሊታረሙ የሚገባቸው ጉድለቶች

ባለድርሻዎችን በበቂ ሁኔታ አለማሳተፉ ይህንን በሚያህል ግዙፍ ፕሮጀችት ባለድርሻዎችን በተገቢው መንገድና ሚና አለማሳተፍ የፕሮጀክቱ ዋነኛው ጉድለት ነው። የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎችንና የሚመለከታቸውን በተለያዩ መድረኮች እንዳወያየ በተለያዩ ጊዜያት ቢናገርም ባለድርሻዎች ግን የተደረገው ‹‹ውይይት ሳይሆን የ‹ዕወቁልኝ› ስብሰባ ነው›› ባዮች ናቸው። አንድ ከነዋሪዎችና ከባለሙያዎች የተሰበሰበ ጥናት እንደሚያሳየው ባለድርሻዎች በተገቢው መንገድ ተሳተፈዋል ብለው የሚያምኑት ከአምስት በመቶ በታች ናቸው። ስለዚህ 95 በመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎች ተሳትፏቸው ወይ የይስሙላ አልያም ዝቅተኛ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። 30 በመቶ የሚሆኑ ፈጽሞ እንዳልተሳተፉ የሚያምኑ ናቸው።

የአትዮጵያ የከተማ ዕቅድ አዋጅ ቁጥር No. 574/2008 ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን የባለድርሻዎች ተሳትፎ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ቢደነግግም፣ ይህንን የሚያህል ግዙፍ በጀት ወጪ የሚደረግበት የከተማ ፕሮጀክት በቂና አሳማኝ የባለድርሻዎች ተሳትፎ አለማድረጉ ከአገሪቱ ሕግም አንፃር ቢመዘን ከፍ ያለ ወቀሳ የሚቀርብበት ጉድለት ነው። ከላይ ወደ ታች የሚፈስስ የውሳኔ አሰጣጥ አሠራር በሕዝቡና በአስፈጻሚው ዘንድ መተማመን እንዲላላና ይህንን የመሰለ ዘመን ተሻጋሪ ፕሮጀክት በሙሉ ልብ እንዳይደግፈው ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች ለሚያቀርቡት የፖለቲካ ሴራ ትንታኔ ጆሮውን እንዲያዘነብል ሳያደርጉት አልቀረም።

አዲስ አበባ የምትጠቀምበትና አሁን በሥራ ላይ ያለው መዋቅራዊ ዕቅድ (Addis Ababa City Structure Plan 2017-2027) ከዚህ ቀደም የተተገበሩት የከተማ ፕሮጀችቶች ዘላቂ የሕዝብ (የባለድርሻዎች) ተሳትፎ የጎደላቸው እንደነበሩ ጠቅሶ፣ ይህም በከተማ አስተዳደሩና በአልሚዎች ዘንድ መተማመን እንዳይኖር ማድረጉን ይገልጻል። ከዚህም የተነሳ የከተማ ፕሮጀክቶች በዋነኛነት ባለድርሻዎችን እንዲያሳትፉ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ በመዋቅራዊ ዕቅዱ እንደተጠቆመው ዋነኛ ባለድርሻ ከሚባሉት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ አካዴሚ፣ የሙያ ማኅበራትና አልሚዎች ጋር በቂ ጊዜ ተመድቦ ምክክር ባለመደረጉ የኮሪደር ልማቱ ለጥርጣሬና ለወቀሳ የተጋለጠ እንዲሆን አድርጎታል።

ከከተማዋ መዋቅራዊ ዕቅድ ጋር አለመመሳከሩ

በኮሪደር ልማቱ ላይ የሚቀርበው ሌላኛው ቅሬታ ከከተማዋ መዋቅራዊ ዕቅድ ጋር የተመሳከረና የተጣጣመ አለመሆኑ ነው። አንድ ከተማ ይልቁኑም የአንድ አገር ዋና ከተማ የምትለማው በጥናትና ምርምር በታገዝ ጥልቅ ትንታኔና ሰፊ ጊዜ ወስዶ በበርካታ የሙያ ዘርፍ ባለቤቶች ምክክር ተዘጋጅቶ በፀደቀ መሪ ዕቅድ እንጂ፣ በባለሥልጣናት ይሁንታና የአንድ ሰሞን የፖለቲካ ሞቅታ አይደለም። በመሪዎች ፍላጎት ከተማን ለማልማት የምንነሳ ከሆነ በሒደት በጥልቀት ያልታሰበባቸው በርካታ ጉዳዮች እየተመዘዙ ይመጣሉ። በዚህም የተነሳ ከአጠቃላዩ የአገሪቱ የከተማ ፖሊሲም ሆነ በሥራ ላይ ከሚገኝ መሪ ዕቅድ የመጣረስ ዕድላቸው ሰፊ ነው።

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በሥራ ላይ ያለው መዋቅራዊ ዕቅድ በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ዜጎች ከመኖሪያና ከመሥሪያ ቦታቸው የሚነሱ ከሆነ፣ ቀድሞ ከነበሩበት ቦታ ከ500 ሜትር (ግማሽ ኪሎ ሜትር) ሳይርቁ ምትክ ቦታ እንዲዘጋጅላቸው ቢደነግግም እየሆነ ያለው ግን ነዋሪዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረታቸውን ከጣሉበት የቀድሞ መኖሪያቸው ተፈናቅለው በአዲስ አካባቢ እንዲሠፍሩ መደረጉ ነው። አስተዳደሩ ከነባር ሠፈሮቻቸው የተነሱ ዜጎች የተሻለ የጋራ መኖሪያ ማግኘታቸውን እንጂ፣ አዲሱ መኖሪያቸው ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ገመዶቻቸው ሳይበጣጠሱ መቀጠላቸውን ወይም ራሱ ካዘጋጀው የከተማዋ መዋቅራዊ ዕቅድ ሕግ ጋር የተገናዘበ አሠራር መከተሉን ተናግሮ አያውቅም። ይዞታዎች ላይ የሕንፃ ግንባታ ሲከናወን ከመንገድ መራቅ የሚገባቸውን ሥፍራ የሚደነግገው አዲሱ ውሳኔ በመሪ ዕቅዱ የሚታወቅ አይደለም። ‹‹ከ500 ካሬ ሜትር በታች ይዞታ ያላቸው ባለይዞታዎች ቦታቸውን ማልማት አይችሉም፤›› የሚለው አዲሱ ድንጋጌም እንዲሁ በከተማዋ የሕንፃ አዋጅም ሆነ በመሪ ዕቅዱ የሚታውቅ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎችን ንብረት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚያጣብብ ውሳኔ ነው።

የተዘነጉ የምህንድስና ጉዳዮች

አዳዲስ የተገነቡት የአረንጓዴ ልባስና መናፈሻዎች የውኃ እጥረትን መቋቋም የሚችሉ የዲዛይን አማራጮችን ከመከተል ይልቅ፣ ውኃን አብዝተው የሚፈልጉ የሳር ልባስ እንዲሆኑ መወሰኑ በከተማዋ የውኃ እጥረት ላይ ተጨማሪ ጫና የሚፈጥር ምርጫ ከመሆኑም በላይ የዘላቂነት ጥያቄ ይነሳበታል። የእግረኛ መንገዶቹም ቢሆኑ ቀድሞ እንደነበሩት የዝናብ ውኃን ወደ ታች ማስረግ በሚችሉ ተሰካኪ ጡቦች ከመጠቀም ይልቅ፣ በብረት የተዋቀረ ኮንክሪት ንጣፍ መቀየራቸው የጎርፍ መጠንን ከመጨመሩም በላይ የሲሚንቶ ንጣፍ የተሠራበት መንገድ አንሸራታች በመሆኑ፣ በተለይ ዝናብ ወይም እርጥበት በሚኖርበት ወቅት ለእግረኛ የማይመች ብቻ ሳይሆን ጉዳት የሚያስከትል ነው፡፡ የግድ ‹‹የሲሚንቶ ንጣፍ መሆን አለበት›› የሚል ፍላጎት ካለ ምቹ፣ ለዓይን ማራኪና የማያንሸራትት የአሠራር ዘዴን መጠቀም ይቻል ነበር። በሌላ በኩል ይህ አጋጣሚ የጎርፍ ማስወገጃ መስመሮችን ጭምር በተጠና መንገድ ለማሻሻል ስላልተጠቀምንበት፣ ጉርድ ሾላን በመሳሰሉ አንዳንድ አካባቢዎች የተስተዋለው የጎርፍ ማጥለቅለቅ፣ ፕሮጀክቱ በቂ ጥናት ተደርጎበት ነው ወደ ሥራ የተገባው? የሚለውን መከራከሪያ ብዙም አሳማኝ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

ባለሙያ ያላየው የከተማዋ የኪነ ሕንፃ መልክ

ሌላኛው አነጋጋሪ ውሳኔ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ግራጫ ቀለም እንድትለወጥ መደረጉ ነው። አዲስ አበባ ከሌሎች የአፍሪካ እህት ከተሞች የሚለያት አንደኛው ፀባይ በምዕራባውያን ባህልና በቅኝ ገዥዎች ተፅዕኖ ያልተለወጠ ቅይጥነቷ ነው። ይህ ቅይጥነት በአሠፋፈር፣ በዲዛይን፣ በቀለማትና በግንባታ ቁሳቁስ የሚገለጥ ስለሆነ ይህንን የከተማዋን የኪነ ሕንፃ መልክ ደምስሶ አንድ ወጥ ቅኝት መከተል ትክክል አይደለም። ጉድለቱ ይህም ብቻ እይደለም፡፡ ፈጽሞ ቀለም የማይቀቡና በግድ ቢቀቡ እንኳን ቀለም የማይዙ አሉሙኒየምና መስታወቶች ሳይቀሩ ግራጫ ቀለም እንዲቀቡ ማስገደድ ፕሮጀክቱ ከሙያ ይልቅ በፖለቲካ ውሳኔ እየተተገበረ ለመሆኑ ማሳያ ነው። ከፅዳትና ውበት አኳያ እንመዝነው ከተባለም ጉም የለበሰች ያስመሰላት ቀለም ፈጽሞ በግንባታ ላይ ላለች አዲስ አበባን ለመሰለች ከተማ ፈጽሞ የማይመከርና አቧራ በፍጥነት የሚያበላሸው መሆኑን ለመታዘብ አንድ የዝናብ ወቅት ማሳለፍ ብቻ በቂ ነው። የከተማዋ መሪ ዕቅድ ግን የከተማዋን ቀለም በዞኒንግ ከፋፍሎ አሳይቶ ነበር።

የኮሪደር ልማቱ ይዞት የመጣው የመብራት ዲዛይን ሌላኛው ትኩረት የሳበ አከራካሪ ጉዳይ ሆኗል። ‹‹ስማርት›› ናቸው የተባለላቸው የመንገድ ዳር መብራቶች (ባለ13 አምፖሎቹ) ከመሠረታዊ የመንገድ ዳር መብራቶች አገልግሎት ይልቅ ለውበት ታስቦ የተተከሉ አስመስሏቸዋል። ከ13 አምፖሎች ዘጠኙ ወደ ሰማይ የሚያበሩ ሲሆን አራቱ ብቻ ለመንገድ መብራትነት የሚያገለግሉ ናቸው። በተለመደው የኤሌክትሪክ ምህንድስና ለእግረኛ ታስበው የሚተከሉ መብራቶች ቁመታቸው ዝቅ ያለ እንዲሆን ቢጠበቅም፣ እነዚህ መብራቶች ግን ሩቅ በመሆናቸው ከአገልግሎታቸው ይልቅ ለውበት የታሰቡ አስመስሏቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሕንፃዎችና የመንገድ መብራቶች ላይ ሳይቀር የተጠመጠሙት የገመድ መብራቶች ተደጋጋሚና አሰልቺ ከመሆናቸውም በላይ፣ ባልተጠና መንገድ ሥራ ላይ እንዲውሉ ከተደረጉ በኋላ እንደገና እንዲነሱና በግለሰብ መኖሪያ ቤት ደረጃ የሚተከሉ የግድግዳ መብራቶች በየሕንፃዎች ላይ እንዲሰቀሉ ተደርጓል። ከተተከሉ ጥቂት ወራት ብቻ ያስቆጠሩ የግድግዳ መብራቶች ዛሬ በከፊል የማይሠሩና ለጥገናም ሆነ ለመቀየር የማያመቹ መሆናቸውን ምሽት ላይ ከተማዋን ዞር ዞር ብሎ በማየት ብቻ ማረጋገጥ ይቻላል።

አናሳ ግምት የተሰጠው የቅርስ ጥበቃና ክብካቤ ጉዳይ

የኮሪደር ልማቱ ሌላው ጉድለት ለቅርሶች ክብካቤ የሰጠው አናሳ ግምት ብቻ ሳይሆን፣ ልክ ባልሆነ መንገድ ‹‹ለማስዋብ›› የሄደበት መንገድ ጭምር የሚያስተች ነው፡፡ ቅርስ የሚባለው አንድ ቁስ ወይም ግብረ ሕንፃ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑም ታሪካዊ ሠፈሮችና የከተማ ማዕከላት በቅርስነት ይመዘገባሉ፣ ይታወቃሉም፡፡ በሥራ ላይ ያለው የከተማዋ መሪ ዕቅድ ፒያሳንና አካባቢዋን ‹‹የአዲስ አበባ ታሪካዊ መንደር›› ሲል የሚበይን ሲሆን፣ በአካባቢው ስለሚገነቡ የሕንፃ ዲዛይኖች ወሰን አስቀምጧል፡፡ የኮሪደር ልማቱ የፒያሳን ታሪካዊ መልክ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ የደመሰሰው ሲሆን፣ አንዳንድ ግብረ ሕንፃዎችንም ሙያዊ ባልሆነ መንገድ ያልነበራቸውን መልክና ቁሳቁስ በመጠቀም በርዟቸዋል።

ግልጽነት የጎደለው የኮንትራት አስተዳደር

የኮሪደር ልማቱ የዲዛይንና የግንባታ አገልግሎት ለአማካሪዎችና ለሥራ ተቋራጮች የተሰጠበት የኮንትራት አስተዳደር መንገድም ከትችት አያመልጥም፡፡ መንግሥት የአገልግሎት ግዥ መመርያ ቢኖረውም፣ ይህንኑ መመርያ በሚንድ መልኩ ለዜጎች እኩል የመወዳደር ዕድል በማይሰጥና መሥፈርቱ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ያለ ጨረታ መስጠቱ አሠራሩን ለኢፍትሐዊነትና ለሙስና ከማጋለጡም በላይ፣ ከተማዋ የተሻለ አቅም ያላቸው ዲዛይነሮችንና ሥራ ተቋራጮችን ልምድና ዕውቀት እንዳታገኝ አድርጓታል።

ማጠቃለያ

ከተማን ማስዋብ፣ ለኑሮ፣ ለሥራና ለቱሪዝም ምቹ ማደረግ በሁሉም ዘንድ ሊታቀፍና ዕገዛ ሊደረግለት የሚገባ የወል አጀንዳ እንጂ፣ የፉክክር አጀንዳ መሆን የለበትም። ይህ እንዲሆን ደግሞ የአንድ ፓርቲ ወይም የአንድ ቡድን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ የነዋሪዎችንና የሌሎች ባለድርሻዎችን አስተያየት ከግምት ሊያስገባ ይገባው ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ሥራው በሒደት ላይ ያለ ከመሆኑ አንፃር ምክንያታዊ ትችቶችን በልኩ ማየት ቢቻል ጉድለቶችን ሞልቶ የተጣመመውን አቅንቶ ለመጓዝ ዕድል አለ እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ ሕንፃና የከተማ ዕቅድ መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡