
ከ 5 ሰአት በፊት
ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ዩኬ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ለመላክ እና በሰላም ስምምነቱ መሰረት የደህንነት ሁኔታውን ለማረጋገጥ ዝግጁ እና ፈቃደኛ መሆኗን ተናገሩ።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር በዩክሬን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን “ፑቲንን ወደፊት ከተጨማሪ ጥቃት መከላከል አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
ሰኞ ዕለት ፓሪስ ላይ ከአውሮፓ መሪዎች ጋር በሚደረገው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ከመሳተፋቸው በፊት አገራቸው “አስፈላጊ ከሆነ ወታደሮቿን ለመላክ” ለዩክሬን የደህንነት ዋስትና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀቷን ተናግረዋል።
በዴይሊ ቴሌግራፍ ላይ “የብሪታንያ ዜጎችን ወደ አደጋ መላክ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ኃላፊነት በጣም በጥልቀት ይሰማኛል” ሲሉ የጻፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይህን ቀለል አድርገን አንወስደውም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “ነገር ግን የዩክሬንን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚረዳ ማንኛውም ሚና የአህጉራችንን ደህንነት እና የዚህችን ሀገር ደህንነት ለማረጋገጥ ይረዳል” ብለዋል።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የጀመረችው ጦርነት ማብቃት “የሚሆን ከሆነ፣ ፑቲን እንደገና ከማጥቃቱ በፊት ለጊዜው የሚቆም መሆን የለበትም” ሲሉ ሰር ኬር ተናግረዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ወታደሮች ጋር በመሆን በዩክሬን በተያዘው እና በሩሲያ ግዛት መካከል ባለው ድንበር ላይ ሊሰማሩ ይችላሉ።
የሰር ኪር መግለጫ የተሰማው የቀድሞው የጦር ኃይሉ መሪ ሎርድ ዳናት ለቢቢሲ የዩናይትድ ኪንግደም ወታደራዊ ኃይል “ስለተጨናነቀ” በዩክሬን ወደፊት ምንም አይነት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ መምራት አይችልም ብለው ከተናገሩ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል የተኩስ ማቆም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የብሪታንያ ወታደሮች ዩክሬንን በመጠበቅ ላይ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።
በዚህ ወር መገባደጃ ላይ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በዋሽንግተን የሚገናኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “አሜሪካ የምትሰጠው የደህንነት ዋስትና ለዘላቂ ሰላም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም አሜሪካ ብቻ ናት ፑቲን ዳግም ጥቃት እንዳያደርስ ማድረግ የምትችለው” ብለዋል።
- ፕሮጀክት 2025፡ ቀኝ አክራሪዎች ለትራምፕ ያቀረቡት ጂቡቲ እና ሶማሊላንድን የሚጠቅሰው ፍኖተ ካርታ16 የካቲት 2025
- https://www.bbc.com/amharic/articles/clykmegl8yl
- የምግብ ሸቀጦችን ትንሽም ቢሆን በጅምላ እና በአንድ ላይ መሸመት ያለው ጥቅም ሲሰላከ 6 ሰአት በፊት
ሰር ኪር አሜሪካ ከሩሲያ ጋር የአህጉሪቱን መሪዎች ባገለለ ሁኔታ የሰላም ንግግር በጀመረችበት በአሁኑ ወቅት፣ ከሌሎች የአውሮፓ መሪዎች ጋር ተገናኝተው እየተወያዩ ነው።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በሚቀጥሉት ቀናት ከሩሲያ ባለስልጣናት ጋር በሳዑዲ አረቢያ ሊገናኙ ማቀዳቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ቅዳሜ ዕለት በዩክሬን የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ኪት ኬሎግ የአውሮፓ መሪዎች ሀሳባቸው እንደሚጠየቅ እና በአሜሪካ እና በሩሲያ መካከል በሚደረጉ ማናቸውም ንግግሮች ላይ ግን እንደማይሳተፉ ተናግረዋል።
አንድ ከፍተኛ የዩክሬን መንግሥት ምንጭ እሁድ እለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኪየቭ በአሜሪካ እና በሩሲያ መካከል ለሚደረገው ውይይት አልተጋበዘችም።
ትራምፕ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ረዘም ላለ ሰዓት በስልክ መወያየታቸውን አስታውቀው በዩክሬን ያለውን “አስቂኝ ጦርነት” ለማስቆም ድርድር “ወዲያውኑ” እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
ትራምፕ ይህንኑ እቅድ ለዜለንስኪ ‘አሳውቀዋል’።
እሁድ እለት ትራምፕ ዜለንስኪ በውይይቶቹ ውስጥ ይሳተፋሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የአውሮፓ አገራት ለዩክሬን የአሜሪካ የጦር መሳሪያ እንዲገዙ እንደሚፈቅድም ተናግሯል።
ጦርነቱ እንዲያበቃ የጊዜ ሰሌዳቸውን በቢቢሲ የተጠየቁት ትራምፕ “ይህን ለማድረግ እየሰራን ነው” ሲሉ ብቻ ለጦርነቱ ተጠያቂው የቀድሞው አስተዳደር በዩክሬን ላይ የነበረው ፖሊሲ ነው ብለዋል።
ሰር ኪር በቴሌግራፍ ላይ እንደጻፉት ከሆነ “ሰላም ያለምንም ዋጋ ሊመጣ አይችልም” እና “በእነዚህ ድርድሮች ውስጥ ዩክሬን መገኘት አለባት፤ ምክንያቱም ምንም ያነሰ ነገር ዩክሬን አገር አይደለችም የሚለውን የፑቲንን አቋም ያንጸባርቃል” ብለዋል።
አክለውም በትራምፕ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን ድርድሩ ተጀምሮ በባይደን አስተዳደር የተጠናቀቀውን የአፍጋኒስታን ጉዳይ በመጥቀስ “አሜሪካ ከታሊባን ጋር በቀጥታ የተነጋገረችበት እና የአፍጋኒስታንን መንግሥት ያገለለችበት ሁኔታ ዳግም ልንፈጥር አንችልም” ብለዋል።
“ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህንንም ማስወገድ አንደሚፈልጉ እርግጠኛ ነኝ” ሲሉ ሰር ኪር ተናግረዋል።
ሰር ኬር ዩክሬን የኔቶ አባል ለመሆን የምታደርገው ጉዞ “ሊቀለበስ የማይችል” ነው ሲሉ የአውሮፓ አገራት “የመከላከያ ወጪያችንን በመጨመር በኅብረቱ ውስጥ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባል” ብለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም በአሁኑ ጊዜ 2.3% የሚሆነውን የአገር ውስጥ ምርቷን ለመከላከያ የምታወጣ ሲሆን ለዚህ የሚሆን የጊዜ ገደብ ሳታስቀምጥ የመከላከያ ወጪውን ወደ 2.5% ለማሳደግ ወስናለች።
ትራምፕ የኔቶ አባላት 5% የአገር ውስጥ ምርታቸውን ለመከላከያ እንዲያወጡ ጥሪ ሲያቀርቡ፣ የኔቶ ዋና ፀሃፊ ማርክ ሩት ደግሞ ከ3% በላይ እንዲያወጡ ሀሳብ አቅርበዋል።
እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2009 የሰራዊቱ ኃላፊ የነበሩት ሎርድ ዳናት ለቢቢሲ እንደተናገሩት እስከ 40,000 የሚደርሱ የዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች በዩክሬን ለሚደረገው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በተለዋዋጭነት እንደሚያስፈልጉ ገልጸው “ይህንን ግን አላገኘንም።” ብለዋል።
በአጠቃላይ የዩክሬንን ሰላሙን ለማስጠበቅ ወደ 100,000 የሚጠጉ ወታደሮችን እንደሚያስፈልግ እና ዩናይትድ ኪንግደም ከፍ ያለ ወታደር ማዋጣት እንዳለበት፣ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ተስፋ ሰጪ ነገር አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በፓሪስ የጠሩት በዚህ ስብሰባ ሰር ኪር ከጀርመን፣ ኢጣሊያ፣ ፖላንድ፣ ስፔን፣ ኔዘርላንድስ እና ዴንማርክ መሪዎች ከአውሮጳ ምክር ቤት እና የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንቶች እና ሩት ይገኙባቸዋል።