
ከ 5 ሰአት በፊት
ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነታቸውን በማወጅ የመጀመሪያ የሚባሉት ኢማም በደቡብ አፍሪካ በተተኮሳባቸው ጥይት ተገደሉ።
የ57ቱ የእስልምና ሃይማኖት አባት ሙሽን ሄንድሪክት የተገደሉት ቅዳሜ፣ የካቲት 8/ 2017 ዓ.ም ነው።
ኢማሙ በደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን ለተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የተገለሉ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ጨምሮ ሁሉን አቃፊ መስጊድን ይመሩ ነበር። የሃይማኖት አባቱ ግኬብርሃ በተባለች ከተማ በመኪናቸው ሲጓዙ በሽምቅ ጥቃት መገደላቸው ተገልጿል።
“ጭምብል ያጠለቁ ሁለት ማንነታቸው ያልታወቁ ተጠርጣሪዎች ከተሽከርካሪያቸው ወርደው በኢማሙ መኪና ላይ ጥይት ማርከፍከፍ ጀመሩ” ሲል ፖሊስ በመግለጫው አስታውቋል።
የኢማሙ ሞት ዜና በመላው ዓለም ባሉ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ማህበረሰብ እና ደጋፊዎቻቸው እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል።
በርካቶች በሃይማኖት አባቱ ግድያ የተሰማቸውን ሃዘን እና ልብ መሰበር መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ቀጥለዋል። ኢማሙ የተገደሉት የሁለት ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ የሆኑ ሴቶችን ሰርግ ሲመሩ ቆይተው ሲመለሱ እንደሆነ ያልተረጋገጡ ዘገባዎች ይፋ አድርገዋል።
ጥቃቱን የሚያሳዩ የደህንነት ቪዲዮዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተጋሩ የሚገኙ ሲሆን አንድ ተሽከርካሪ ኢማሙ የሚጓዙበትን መኪና መንገድ በመዝጋት መተላላፊያ ሲያሳጣቸው ያሳያል። እንደ ፖሊስ መረጃ ከሆነ ኢማሙ የተቀመጡት ከኋላ ወንበር ነበር።
ከአንደኛው መንገድ በኩል የተከናወነው ነገር በሚያሳየው የሲሲቲቪ ቀረጻ መሰረት አንደኛው ጥቃት ፈጻሚ ከመኪናው ዘሎ በመውረድ መንገድ ወደ ተዘጋበት ተሽካርካሪ ሮጦ በኋለኛው ተሳፋሪ መስኮት በኩል በተደጋጋሚ ጥይት ሲተኩስ ያሳያል።
በኬፕታውኗ ዊንበርግ ከተማ የሚገኘውን ማስስጂዱል ጉርባህ የተሰኘውን መስጊድ የሚያስተዳድረው የሄንድሪክስ አል ጉርባህ ፋውንዴሽን ኢማሙ ቅዳሜ ማለዳ ላይ በደረሰ ጥቃት መገደላቸውን አረጋግጧል።
የፋውንዴሽን የቦርድ ሰብሳቢ አብዱልሙጌት ፒተርሰን ተከታዮቻቸው እና ምዕመናን ሁኔታውን በትዕግስት እንዲጠባበቁ በዋትስአፕ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ተማጽነዋል።
- የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆን ቅጣት የሚያስከትልባቸው የአፍሪካ ሀገራት1 ጥር 2025
- በቲክቶክ ከወንድ ጋር ሲደንስ መታየቱ ሕይወቱን ሊያሳጣው የነበረው ኢትዮጵያዊ7 ታህሳስ 2023
- ፖፕ ፍራንሲስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች ቡራኬ ልትሰጥ እንደምትችል ጠቆሙ3 ጥቅምት 2023
ኢማሙ የእስልምናን ትውፊታዊ ትርጓሜዎች በመቃወም በቸርነት፣ በደግነት እና ሁሉን ያካተተ እምነትን አስፈላጊነትን በመስበክ ይታወቃሉ።
ጨቋኙን የአፓርታይድ ስርዓት መገርሰስ ተከትሎ የወጣው የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት ዜጎች በጾታዊ ዝንባሌዎች ምክንያት የሚደርስባቸውን መድልዎ የሚታደግ እንደሆነ ይጠቀሳል።
በአውሮፓውያኑ 2006 የወጣው ይህ ህገ መንግሥት የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ህጋዊ በማድረግ ከአፍሪካ የመጀመሪያው አድርጎታል። ምንም እንኳን የተመሳሰይ ጾታ ጋብቻ ህጋዊ እንዲሁም ማኅበረሰቡም ተሰሚነት ያለው ቢሆን መድልዎ እና ጥቃቱ እንደቀጠለ ነው።
ደቡብ አፍሪካ በዓለማችን ላይ በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ከፍተኛ ግድያ ከሚፈጸምባቸው አገሮች አንዷ ናት።
ሄንድሪክስ በአውሮፓውያኑ 1996 የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪነታቸውን ማወጃቸውን ተከትሎ በኬፕታውን እንዲሁም በሌሎች ስፍራዎች ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ያስደነገጠ ሆኗል።
ሁሉን አቃፊ የሆነውን መስጊድ ከማቋቋማቸው በፊት እምነታቸውን እና ጾታዊ ዝንባሌያቸውን ለማስታረቅ ለሚፈልጉ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ ድጋፍ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ስፍራ የሆነውን ‘ዘ ኢነር ሰርክል’ የተሰኘውን ድርጅት መሰረቱ።
በአውሮፓውያኑ 2022 በእሳቸው ሕይወት ላይ የሚያጠነጥን ‘ዘ ራዲካል’ የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ተሰርቶላቸው ነበር። በዚህም ፊልም ላይ የሚደርሷቸውን ማስፈራሪያዎች አስመልክቶ “እውነተኛ ወይም ራስን መሆን ከመሞት ፍርሃት በላይ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።
ኢማሙ በሃይማኖቶች ውስጥ ውይይትን የመፍጠር አስፈላጊነት እንዲሁም የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች የሚያጋጥሟቸውን የአዕምሮ ጤና ጉዳዮች እንዲሁም ሌሎች ችግሮች ላይ በተደጋጋሚ በመናገር ይታወቃሉ።
ባለፈው ዓመት በኬፕታውን በተካሄደ አንድ አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ “ሃይማኖትን እንደ ጠላት መመልከት መቆም አለበት” ብለው ነበር።