የምግብ ገበያ

ከ 6 ሰአት በፊት

በቤት ውስጥ ለዕለት ከዕለት ፍጆታ የምናውላቸውን የምግብ ሸቀጦች በጅምላ መግዛት ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው።

አንደኛ በጅምላ መግዛት ቅናሽ ስለሚኖረው ወጪ ይቆጥባል። ሁለተኛ ደግሞ ለአካባቢ ጥበቃ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

የቢቢሲ ዘጋቢ ሉሲ ሼሪፍ በየጊዜው ደጋግሞ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ መግዛት አንድ ጊዜ ከመግዛት አንጻር ያለውን ልዩነት ካወቀች በኋላ ወርሃዊ ወጪዋን እንዳስተካከለች ትናገራለች።

በየጊዜው ምግብ መግዛት አካባቢን የሚበክሉ ፕላስቲኮችን ደጋግሞ ለመጠቀም ያስገድዳል።

“የወተት ተዋጽኦን ከሱቅ ሳይሆን ከአምራቾቹ ለመግዛት ወሰንኩ። ዘይት፣ ሩዝ፣ ሻይ ቅጠል፣ ባቄላ እንዴት መግዛት እንደምችል መመራመርም ጀመርኩ” ትላለች ሉሲ።

ታማኝ እና ተፈጥሯዊ ምርት የሚያቀርቡ ደንበኞች ማፍራት ነበረባት።

የት ነው የሚያመርቱት? እንዴት ነው ለገበያ የሚያቀርቡት? ብላም መጠየቅ ነበረባት።

ሉሲ አጃ ለመግዛት እና አጃውን ለመጠቅለል ለምትገዛው ላስቲክ የምታወጣውን ገንዘብ አስልታለች።

“11.4 ኪሊ ግራም አጃ ስገዛ የማወጣው 48 ዶላር ነው። 1.18 ኪሎ ግራም በነጠላ ስገዛ ግን 8.99 ዶላር አወጣለሁ” በማለት በጅምላ ስትገዛ ከፍተኛ ቅናሽ እንዳላት ትናገራለች።

የተፈጥሮ ኮኮናት ዘይት 3.8 ሊትር የሚሸጠው 30 ዶላር ሲሆን 400 ሚሊ ሊትር 7.49 ዶላር ይሸጣል።

“በዚህ ስሌት መሠረት በእያንዳንዱ ጠርሙስ 71.15 ዶላር እያወጣሁ ነው” ትላለች።

የካርበን ልቀትን መቆጣጠር

ለምግብ የምናውላቸውን ግባቶች በጅምላ መግዛት ለአካባቢ ጥበቃም ይመከራል።

በካናዳ፣ ሞንትርያል፣ ፖሊቴክኒክ ተቋም ውስጥ የምትሠራው ቫለሪ ፓታሩ “አንድ ምርት ምን ያህል ለአካባቢ ጥበቃ ይጠቅማል የሚለውን ሸማቾች ማወቅ ይከብዳቸዋል። ምክንያቱም በቂ መረጃ የለም” ትላለች።

ምርቶች ምን ያህል ተረፈ ምርት እንዳላቸው ማወቅ ቀላል ቢሆንም፤ የካርበን ልቀትን ለመለካት በቂ መረጃ እንደሚያስፈልግ ታስረዳለች።

ሉሲ ይሄንን ከግምት በማስገባት ሩዝ፣ አጃ ፣ የሻይ ቅጠል እና ቡና ከአንድ ድርጅት ገዛች። እያንዳንዳቸውን በተናጠል ብትገዛ ኖሮ ለማጓጓዝ ሲባል የካርበን ልቀት ይጨምራል።

“ዕቃዎቹን ለማሸግ እና ለማድረስ ይወጣ የነበረውን ካርበን መቀነስ ችያለሁ” ትላለች።

በተጨማሪም በተናጠል ሸመታ ሲደረግ ለትራንስፖርት የሚውለው ወጪ፣ ጊዜ እና ድካም ሌላኛው ኪሳራ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

የምግብ ገበያ

በየትኛውም ቦታ ቢሆን ከአምራቾች ቀጥታ መግዛት ትመርጣለች።

‘ኢሰንሻል ኦርጋኒክስ’ የተባለው ተቋም መቀመጫው ዋሽንግተን ነው።

ምርቶቻቸው ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይመጣሉ። ለምሳሌ ሉሲ ያዘዘችውን የሻይ ቅጠል ከቻይና፣ ሩዙን ከታይላንድ፣ ኮኮናት ዘይቱን ከፊሊፒንስ ያመጡታል።

ይህ ማለት ደግሞ ለእያንዳንዳቸው የካርበን ልቀትን መለካት ከባድ ነው ማለት ነው።

“በተናጠል ብገዛቸውም የካርበን ልቀትን መለካት ያስቸግራል” ትላለች።

የኢሰንሻል ኦርጋኒክስ የድረ ገጽ ቃል አቀባይ አላናህ ላቨሪኝ እንደምትለው፣ ድርጅታቸው ሰዎች በጅምላ ምግብ እንዲገዙ ያበረታታል።

“እያንዳንዱ ምርት የሚጠቀለልበትን ወጪ ይቀንሳል። ደንበኞቻችን የሚያወጡትን ወጪም ይቀንሳል” ትላለች።

በጅምላ መግዛት እና ቀጥታ ከአምራቾች መግዛት ቀላል አይደለም።

ሆኖም ግን ሉሲ እንደምትለው ከአንድ ቦታ ብዙ ምግቦችን በአንድ ጊዜ መግዛትን መለማመድ ነበረባት።

“ምግቦቹ የሚመጡበትን የካርበን ልቀት ለመቆጣጠር ምክንያታዊ ውሳኔ ወስኛለሁ” ትላለች።

ተረፈ ምርትን መቀነስ

በአሜሪካ ብቻ 4 በመቶ የፕላስቲክ ተረፈ ምርት በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል።

በመላው ዓለም ደግሞ 9 በመቶ የፕላስቲክ ተረፈ ምርት በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል።

ምን ያህል ፕላስቲክ ጥቅም ላይ እንደሚውል ከግምት በማስገባት፣ መልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉት ውስን መሆናቸው ይገለጻል።

ሉሲ ምግብ አብዝቶ መግዛት ምን ያህል ተረፈ ምርትን እንደሚቀንስ ለማወቅም ሞክራለች።

በአውሮፓውያኑ 2023 የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው አሜሪካውያን ሸማቾች አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ መጠንን ለመቀነስ የመፍትሔ አማራጮች እየፈለጉ ነው።

ቫለሪ ፓታሩ በዚህ ጥናት ከተሳተፉ አንዷ ናት።

ቫለሪ እንደምትለው፣ እንደ አንድ አማራጭ እየተወሰ ያለው ምግብን አብዝቶ መግዛት ነው።

ሆኖም ለአካባቢ ጥበቃ ያለው አስተዋጽኦ እንደሚገዛው ምርት ይወሰናል።

“እርጎ እና ኦቾሎኒን ብንወስድ ሁለቱ ምርቶች ካለቁ በኋላ ማስወገድ የሚቻለው በተለያየ መንገድ ነው” ትላለች።

ሻምፖ እና ኮንዲሽነር በፕላስቲክ ከመግዛት በሳሙና መልክ የተዘጋጁትን መግዛት ሉሲ ትመርጣለች።

መያዣ ፕላስቲኮችን በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል አንደኛው መፍትሔ ነው።

በካርቶን፣ በፕላስቲክ ወይም በጠርሙስ የሚመጡ ምርቶች ሲወገዱ ወይም በድጋሚ ጥቅም ላይ ሲውሉ በተለያየ መንገድ ነው።

“አንድ ሰው አብዝቶ ምግብ ከገዛ እና ብዙ ያልተቀነባበሩ ምግቦችን የሚመገብ ከሆነ ጥሩ ልምድ አዳብሯል” ትላለች።

አትክልት ላይ የተመሠተ አመጋገብ ሌላው የሚመከረው አማራጭ ነው።

ከምርት አንስቶ ገበያ ላይ ስለሚቀርቡበት መንገድ እና እንዴት እንደሚወገዱ በቂ መረጃ እንደሚያስፈልግ ቫለሪ ታስረዳለች።