የእስራኤል ወታደሮች

ከ 7 ሰአት በፊት

የእስራኤል ወታደሮች በደቡባዊ ሊባኖስ በወረራ ከያዟቸው ግዛቶች ጠቅለው አለመውጣታቸውን ተከትሎ የሊባኖስ መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነቱን የጣሰ ነው ብሎታል።

የእስራኤል ወታደሮች ከተወሰኑ ከተሞች እና ድንበሮች ላይ ቢወጡም አሁንም አምስት ስፍራዎችን ይዘው ይዘው ይገኛሉ ተብሏል።

በህዳር ወር ላይ በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት የእስራኤል ወታደሮች ከሊባኖስ ግዛቶች ጠቅለው መውጣት የነበረባቸው ቀነ ገደብ ማክሰኞ፣ የካቲት 11/ 2017 ዓ.ም ተጠናቋል።

ለ13 ወራት የዘለቀውን የእስራኤል እና የሊባኖስ ግጭትን የቋጨው ድርድርን ያሸማገሉት አሜሪካ እና ፈረንሳይ ነበሩ።

ህዳር 18/ 2017 ዓ.ም በተጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት እስራኤል በሚቀጥሉት 60 ቀናት ከወረረቻቸው የሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል ቀስ በቀስ ወታደሮቿን ታስወጣለች።

የሄዝቦላህ ወታደሮች ደግሞ ለአስርት አመታት ከተቆጣጠሯቸው የደቡባዊ ሊባኖስ ስፍራዎች ወጥተው በምትኩም የሊባኖስ መንግሥት ወታደሮች ስፍራውን የሚቆጣጠሩት ይሆናል።

ነገር ግን የእስራኤል መከላከያ የሊባኖስ ጦር ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ እስኪተገበር ድረስ የእስራኤል ወታደሮች በአምስት “ስትራቴጂክ” በሚባሉ ኮረብታዎች እንደሚቆይ አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ወታደሮቹ ለምን ያህል ጊዜ በሊባኖስ ግዛቶች እንደሚቆዩ ግልጽ አይደለም።

እስራኤል ወታደሮቼን አላስወጣም ማለቷን ተከትሎ ሊባኖስ በሰጠችው ምላሽ ሙሉ በሙሉ ወታደሮቹ መውጣት አለባቸው ብላለች። “እስራኤል በሊባኖስ ግዛት ላይ በቀጣይነት የምትቆይ ከሆነ እንደ ወረራ እንደምትቆጥረው” ገልጻለች። ማክሰኞ ዕለት የእስራኤል ወታደሮች የወጡባቸውን ስፍራዎች የሊባኖስ ጦር በመቆጣጠር የተዘጉ መንገዶችን በመክፈት እና ያልፈነፈዱ ፈንጂዎችንም ሲቆጣጠር ነበር።

በመኪኖች ተጭነው ወደቀያቸው የተመለሱ ነዋሪዎች ቢጫ የሄዝቦላህ ሰንደቅ አላማ እንዲሁም የቡድኑ መሪ ሐሰን ናስራላህ ምስል የያዙ ፖስተሮችን ይዘው ነበር። ነዋሪዎች በእስራኤል ድንበር በምትዋሰነው ክፋር ኪላ ግዛት በሚገኙ የህንጻ ፍርስራሾች ውስጥ ትተዋቸው የሄዱ የግል ንብረቶቻቸውን ቢፈልጉም በርካቶች ሊያገኙዋቸው አልቻሉም።

“ቤታችን ልክ እንደ ሌሎች መኖሪያ ቤቶች ፈርሷል” ስትል ተዋጊ ወንድሟ በጦርነቱ የተገደለባት ሳፋ ጁማ ታስረዳለች።

“ምንም ነገር ማዳን አልቻልንም። ቤታችን ሙሉ በሙሉ ወድሟል” ብላለች።

ስምምነቱ በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል በአውሮፓውያኑ 2006 የተከሰተውን ጦርነት የቋጨው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 1701 በተሰኘው ውሳኔ የተመሠረተውን ድንበር መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።

ይህም እስራኤል እና ሊባኖስ ከሚዋሰኑበት ሊታኒ ከተሰኘው ደቡባዊ ሊባኖስ ስፍራ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች እንዲርቁ ማድረግን ያካተተ ነው።

የእስራኤል ጦር በስምምነቱ መሰረት ከ60 ቀናት በኋላ፣ ጥር 18/ 2017 ዓ.ም መውጣት የነበረበት ቢሆንም ተጓትቶ ለማክሰኞ ተላልፎ ነበር።

የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር እንደተናገሩት የእስራኤል መከላከያ ኃይል “ለጊዜው በአምስት ስትራቴጂካዊ ኮረብታማ ስፍራዎች ውስጥ አለ” ሲሉ ተናግረው ይህንንም “ለደህንነታችን አስፈላጊ” ሲሉ ገልጸዋል።