
ከ 8 ሰአት በፊት
የዓለማችን ግዙፉ የተንቀሳቃሽ ምሥሎች ማጋሪያው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ዩቲዩብ መሥራት ከጀመረ ሁለት አስርት ዓመታት ደፈነ።
የተመሠረት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር የካቲት 14/2005 ነው። የዚህ የቪዲዮ ማጋሪያ መድረክ መሥራቾች ጃዌድ፣ ቻድ እና ስቲቭ ይባላሉ።
የመጀመሪያው ቪድዮ የተለጠፈው የካቲት 23/2005 ነበር። ይህም ቪዲዮ “ሚ አት ዘ ዙ” በሚል ርዕስ ከዩቲዩብ መሥራቾች አንዱ የሆነው ጃዌድ ከዝሆኖች ፊት ቆሞ የተቀረፀው የ19 ሰከንድ ቪድዮ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ዩቲዩብ በዓለም ዙሪያ 2.7 ቢሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይነገራል።
በዓለማችን በርካታ ሰው ዩቲዩብ የሚጠቀምባት ሀገር ሕንድ ስትሆን 476 ሚሊዮን ሰዎች የዚህ ማኅበራዊ ትስስር መድረክ ተጠቃሚዎች እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።
ዩቲዩብ ቪድዮ መጋሪያ ብቻ ሳይሆን የዜና እና ሌሎች ጉዳዮች መፈለጊያ ቋትም ሆኖ ያገለግላል። እንዲያውም ከጉግል ቀጥሎ በርካታ ሰዎች ዩቲዩብን እንደ መረጃ መፈለጊያ መረብነት ይጠቀሙታል።
ዩቲዩብ በአውሮፓውያኑ 2024 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከማስታወቂያ ብቻ 8.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢን አስገብቷል።
‘ሚስተር ቢስት’ በተባለ የዩቲዩብ ስሙ የሚታወቀው ጂሚ ዶናልድሰን በርካታ አባላት [ሰብስክራይበር] ያለው ዩቲዩበር ነው። ሚስተር ቢስት 363 ሚሊዮን የዩቲዩብ ተከታዮች በመያዝ ቀዳሚው ግለሰብ ሆኗል።
በዓለማችን ከፌስቡክ ቀጥሎ በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ዩቲዩብ ሲሆን በየቀኑ ከአንድ ቢሊዮን ሰዓታት በላይ የሚረዝሙ ቪድዮዎች በዚሁ መድረክ ላይ ይታያሉ።
የዩቲዩብ ደንበኞች ከሆኑት መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተጠቃሚዎች ሞባይል ስልካቸውን ተጠቅመው ነው ቪዲዮዎችን በዩቲዩብ በኩል የሚመለከቱት።
በየቀኑ 720 ሺህ ሰዓታት የሚሆኑ የዩቲዩብ ቪዲዮዎች እንደሚጫኑ መረጃዎች ያሳያሉ። እነዚህ ቪዲዮዎች በአማካይ በየቀኑ 5 ቢሊዮን ጊዜ ይታያሉ።
ይህ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ውስጥ የተጠቃሚው እና የሚያርበው ይዘት እየጨመረ ተመራጭ ከሆኑት የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች መካከል አንዱ የሆነውን ዩቲዩብን በአውሮፓውያኑ 2006 ነበር ጉግል በ1.65 ቢሊዮን ዶላር የገዛው።
- ኢንተርኔትን በመጠቀም ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ይቻላል? የቲክቶክ መካሪዎችስ ምን ያህል ታማኝ ናቸው?5 ታህሳስ 2024
- የስማርት ስልኮች ተፈላጊነት ሊቀንስ ይችላል?18 የካቲት 2025
- ቲክቶከሮች ለምን ያለቅሳሉ? ከምራቸው ነው? ለምንስ አሳዛኝ ይዘት የበለጠ ይመርጣሉ?25 ጥር 2025

ዩቲዩብ በኢትዮጵያ ምን ያክል ተጠቃሚዎች አሉት?
በዓለማችን በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት የማኅበራዊ ሚድያ መድረክ ፌስቡክ ሲሆን፣ ከዓለማችን ሕዝብ ወደ ግማሽ የሚጠጋው 3.06 ቢሊዮን ያህል ሕዝብ ፌስቡክን ይጠቀማል።
ከፌስቡክ ቀጥሎ በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ዩቲዩብ ነው። ኢንስታግራም፣ ዋትስአፕ እና ቲክቶክ በተከታይነት ይገኛሉ።
በኢትዮጵያም ቢሆን ፌስቡክ በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ማኅበራዊ ሚድያ ነው። ከፌስቡክ ቀጥሎ ዩቲዩብ በርካታ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ስታትካውንተር የተሰኘው ድረ-ገፅ ይጠቁማል።
በአውሮፓውያኑ ጥር 2024 በተሰበሰበ መረጃ በኢትዮጵያ 7 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ማኅበራዊ ሚድያ ይጠቀማሉ።
በኢትዮጵያ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ከሆኑ ሰዎች መካከል 13.5 ገደማ የሚሆኑት ዩቲዩብ እንደሚጠቀሙ ነው ይህ ድረ-ገፅ የሚገልፀው። ይህም ማለት ዩቲዩብ በኢትዮጵያ 1 ሚሊዮን አካባቢ ተጠቃሚዎች እንዳሉት መረጃው ያመለክታል።
ነገር ግን አብዛኞቹ መረጃ ሰብሳቢ ድረ-ገፆች እንደሚገልፁት ይህ ቁጥር በግምት የተሠራ ሲሆን፣ የዩቲዩብ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከዚህም የላቀ ሊሆን ይችላል።
በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የዩቲዩብ ቻናል የሚከፍቱ እንዲሁም ዩቲዩብ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን መመልከት ይችላል።
በአፍሪካ በርካታ የዩቲዩብ ተጠቃሚ ያላት ሀገር ግብፅ ስትሆን፣ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አነስተኛ የዩቲዩብ ተጠቃሚ ካላቸው ቀጣናዎች ግርጌ ላይ ይገኛሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ዩናይትድ ስቴትስ ከሕንድ ቀጥላ በ238 ሚሊዮን የዩቲዩብ ተጠቃሚዎች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ብራዚል፣ ኢንዶኔዥያ እና ሜክሲኮ ተከታትለው ከሦስት አስከ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ከዩቲዩብ ገቢ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
ከዚህ ቀደም በዩቲዩብ አማካይነት ገንዘብ ለማግኘት አንድ የቻናል ባለቤት ቢያንስ 1 ሺህ ሰብስክራይበር እንዲኖረው ይጠበቅበት ነበር።
ነገር ግን ከአውሮፓውያኑ 2023 ጀምሮ 500 ሰብስክራይበሮች እና የ3 ሺህ የዕይታ ሰዓት (ዋች አወር) ማግኘት በቂ መሆኑን ዩቲዩብ ይፋ አድርጓል።
ዩቲዩብ በወቅቱ ይህንን የፈቀደው በዩናይትድ ስቴትስ፣ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ)፣ በካናዳ፣ በታይዋን እና በደቡብ ኮሪያ ላሉ ተጠቃሚዎች ነው።
ነገር ግን በተቀረው ዓለም በዩቲዩብ ገቢ ለማግኘት አሁንም 1 ሺህ ሰብስክራይበር እና የ4 ሺህ ሰዓታት የዕይታ ጊዜ (ዋች አወር) ማግኘት ግድ ይላል።
ዩቲዩበሮች ከተንቀሳቃሽ ምሥል ማጋሪያው የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ገንዘብ ማግኘት የሚችሉት ዩቲዩብ ፓርትነር ፕሮግራም በተሰኘው መንገድ ነው።
ለዩቲዩብ የሚሆን ሐሳብ ያላቸው ሰዎች በአነስተኛ ካሜራ እና ብዙ መጠበብ በማይጠይቅ የቪድዮ ‘ኤዲቲንግ’ ሶፍትዌር በመታገዝ በሚያዘጋጇቸው ይዘቶች አማካይነት ገንዘብ ማግኘት እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ሚስተር ቢስት በአውሮፓውያኑ 2020 ከዩቲዩብ 24 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኘ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከሚስተር ቢስት ቀጥሎ በግለሰብ ደረጃ በርከታ ሰብስክራይበር ያላት ታዳጊዋ ሩሲያዊት አሜሪካዊት ናስትያ ናት። ታዳጊዋ 125 ሚሊዮን ሰብስክራይበር አላት። የታዳጊዋ ቪድዮዎች በተለይ በሕፃናት ዘንድ ተወዳጅ ናቸው።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ዩቲዩብን የተቀላቀለው ኮከቡ የእግር ኳስ ተጫዋች ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 73 ሚሊዮን ተከታዮችን አፍርቷል።