ታንክ ከወታደሮቹ ጋር እና ላውንቸር የያዘ ወታደር

ከ 9 ሰአት በፊት

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ሦስት ዓመት ልትደፍን በተቃረበችበት በዚህ ሰዓት ብዙዎች የጦር ኃይል ውጊያዎችን ሊያሸንፍ ቢችልም፤ ሁሌም ቢሆን ጦርነትን የሚያሸንፈው ኢኮኖሚ ነው ይላሉ። ከዚህ አንጻር ዩክሬን ይህንን ጦርነት እየተዋጋች መቀጠል ትችላለች?

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ፤ ሀገራቸው ይህ ጦርነት “በፍጥነት ብቻ ሳይሆን በፍትሐዊነት” እንዲጠናቀቅ እንደምትፈልግ በቅርቡ ተናግረዋል።

ነገር ግን የዩክሬን ዋነኛ አጋር የሆነችው አሜሪካ ለዩክሬን የሚሰጥ እርዳታን ባቆመችበት እና ወደፊት ሊሰጥ የሚችል ድጋፍን ልትቀንስ እንደምትችል እየጠቆመች ባለበት በዚህ ጊዜ፣ በጦርነት የተጎዳው የዩክሬን ኢኮኖሚ ሌላ የውጊያ ዓመትን መቋቋም ይችላል?

የዩክሬን የጦርነት ጊዜ ኢኮኖሚ

ዩክሬን ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጋር ስትነጻጸር ትልቅ ብትሆንም በሕዝብ ብዛት፣ በግዛት ስፋት እና በኢኮኖሚ ከሩሲያ በእጅጉ ታንሳለች።

ወደዚህ ጦርነት ከመገባቱ አስቀድሞ የሩሲያ ኢኮኖሚ ከዩክሬን በአስር እጥፍ እንደሚበልጥ ተገምቶ ነበር። ጦርነቱ፤ በቅርብ ታሪክ ባልታየ መልኩ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ከትቷል።

የዩክሬን ኢኮኖሚ ያጋጠመው ንዝረት፤ በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ከሶቪየት ኅብረት ወድቀት በኋላ ካጋጠመው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እና ከፍተኛ የዋጋ ንረት ጋር የሚወዳደር አይደለም።

ከየካቲት 2022 ወዲህ የሀገሪቱ መንግሥት እንደ ጤና እና ትምህርት ላሉ አስፈላጊ ዘርፎች ወጪዎችን መሸፈን ቢችልም አብዛኛውን ገቢውን ያዋለው ግን ለመከላከያ ነው።

ይህም በሀገሪቱ በጀት ላይ ትልቅ ክፍተት ፈጥሯል።

ሩሲያ ጥቃት በጀመረችባቸው የመጀመሪያዎቹ ወራት ኪዬቭ የበጀት ጉድለቷን ለመሸፈን የሞከረችው የግምጃ ቤት ሰነዶችን በመሸጥ እና ገንዘብ በማተም ነበር።

በ2022 መጨረሻ የዩክሬን ኢኮኖሚ በአንድ ሦስተኛ የቀነሰ ሲሆን፣ የዋጋ ንረት በ25 በመቶ አሻቅቧል። ይህንን ማረጋጋት የተቻለው ከአጋር ሀገራት በተገኘ ድጋፍ ነበር።

በመጀመሪያ፤ አሜሪካ ዋነኛዋ ለጋሽ እንዲሁም እንደ ወታደራዊ፣ ሰብአዊ እና ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ ለማስገኘት አስተባባሪ ሀገር ነበረች።

ኋላ ላይ ግን ይህ የአሜሪካ ሚና በተለይም ለዩክሬን የፋይናንስ ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት ወደ አውሮፓ ኅብረት ዞሯል።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ፤ “አሁን ላይ 80 በመቶው የጦርነት ወጪ እየተሸፈነ ያለው በዩክሬን እና በአውሮፓ ነው። 20 በመቶው ደግሞ በአሜሪካ ነው” ሲሉ ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የፈረሰ ህንጻ

ዩክሬን ምን አይነት ድጋፍ እየተቀበለች ነው?

ግራፍ

እርዳታዎቹ እየጠቀሙ ነው?

በ2022 የዩክሬን ኢኮኖሚ ከባድ ውድቀት አጋጥሞት ነበር። ነገር ግን ከውጭ እርዳታ በተገኘ ድጋፍ በቀጣዮቹ ዓመታት ይህ ሁኔታ ተቀይሯል።

የሀገሪቱ መንግሥት መረጃ እንደሚያመለክተው በ2023 የዩክሬን ኢኮኖሚ በ5.3 በመቶ፣ በ2024 ደግሞ በ3.6 በመቶ አድጓል።

ከውጭ የሚገኝ እርዳታ ዩክሬን፤ የውጭ ምንዛሬ ክምችቷን እንድታሟላ፣ የሀገሪቱ ገንዘብ በአንጻሩ የተረጋጋ እንዲሆን እንዲሁም የበጀት ጉድለቷን እንድትሸፍን አስችሏል።

በዩክሬን የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያ ጥናቶች ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ድሜትሮ ቦያርቼክ፤ “ዩክሬን እየተዋጋች ለመቀጠል በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል” ይላሉ።

“እርዳታው ከቀረ እጅግ አሳዛኝ ታሪክ ይሆናል” ሲሉ ዩክሬን ከሌሎች ሀገራት የምታገኘው እርዳታን ወሳኝነት ገልጸውታል።

በዩክሬን ኪዬቭ ከተማ እየተራመዱ ያሉ ሰዎች

የዩክሬን የሀገር ውስጥ ፈተና

የዩክሬን የጦርነት ወቅት ኢኮኖሚ ፈተና ገንዘብ ብቻ አይደለም፤ የኃይል እና የሰው ኃይል እጥረትም ጭምር እንጂ።

ሩሲያ ዩክሬን ከጦርነቱ በፊት የነበራትን ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳወደመች ወይም እንደተቆጣጠረች ይታመናል።

የዩክሬን የኢነርጂ ሚኒስቴር እንደሚገልጸው፤ ከጥቅምት 2022 እስከ መስከረም 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ የሀገሪቱ ኢነርጂ መሠረተ ልማት ከአንድ ሺህ በላይ የሩሲያ ጥቃቶችን አስተናግዷል።

የሀገሪቱ የኃይል ፍላጎት በአብዛኛው የሚሸፈነው ከሩሲያ ከባድ ጥቃት ባልረሰባቸው የኒኩሌር የኃይል ማመንጫዎች ነው።

በዋነኛ የኃይል መጠቀሚያ ሰዓታት የሚፈጠረውን ክፍተት የሚሸፈነው ወደ ሀገር ውስጥ በሚገባ ኃይል እንዲሁም ከንፋስ፣ ከፀሐይ እንዲሁም ከተንቀሳቃሽ የጋዝ ተርባይኖች በሚገኝ ኃይል ነው።

ይህ ሁኔታ የኑሮ ውድነት ላይ ተፅዕኖ ያሳደረ ሲሆን፣ የንግድ ተቋማት እና የኢንዱስቱሪዎች ወጪ እንዲጨምር አድርጓል።

ሌላኛው የዩክሬን ኢኮኖሚ ችግር በአንድ ሦስተኛ እንደቀነሰ የሚታመነው የሰው ኃይል ነው። በጦርነቱ የተከሰቱ ሞት እና ጉዳቶች፣ ስደት እንዲሁም የነዋሪዎች እንቅስቃሴ ለተፈጠረው የሰው ኃይል እጥረት ምክንያቶች ናቸው።

በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ባለው ጦርነት 880 ሺህ ገደማ ሰዎች በሠራዊቱ ውስጥ እየተዋጉ እንደሆነ ዜሌንስኪ ተናግረው ነበር።

በተጨማሪም የሩሲያ ወረራ ከዩክሬን ሕዝብ አንድ አራተኛ የሚሆኑትን ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አድርጓል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ዩክሬናውያን ስደተኞች በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሲሆን፣ 4.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ደግሞ በሀገር ውስጥ ተፈናቅለዋል።

የዩክሬን ኢኮኖሚ ምን ያህል መቀጠል ይችላል?

ለዩክሬን የሚደረግን ዓለም አቀፍ ድጋፍ የሚያስተዳድረው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) በቅርቡ እንደገለጸው፤ ምንም አንኳ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም የሀገሪቱ “ኢኮኖሚ ፅኑ ሆኖ ቀጥሏል።”

የኢኮኖሚ ባለሙያው ድሜትሮ ቦያርቼክ፤ በተራዘመ ጦርነት ውስጥ ሁሉም ሀብት ወሳኝ መሆኑ እንዲሁም የኢኮኖሚ ፅኑንነት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ይገልጻሉ።

የዩክሬን ብሔራዊ ባንክ ገዢ አንድሪ ፒሽኒያ፤ የዩክሬን በጦርነት መሸነፍ እንደ የምግብ ዋስትና፣ አዲስ የስደተኞች ማዕበል እንዲሁም ሀገራት ከአረንጓዴ ልማት ይልቅ ወታደራዊ ወጪዎችን እንዲያስቀድሙ በማደረግ ረገድ ባሉ ጉዳዮች ለመላው ዓለም የሚዳረስ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይናገራሉ።

ዩክሬን ምንም እንኳን በአብዛኛው በውጭ እርዳታ ላይ ጥገኛ ብትሆንም የጦርነት ወቅት ኢኮኖሚዋን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ተነሳሽነት አሳይታለች።

ሩሲያ፤ ወደ ሩቅ ሀገራት ምግብ ለመላክ በሚል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በቱርክ አደራዳሪነት ከተደረሰው የጥቁር ባሕር የእህል ማጓጓዝ ስምምነት ስትወጣ፤ ዩክሬን እና አጋሮቿ የሩሲያን ጥቃት የሚያመልጡበት አዲስ የጥቁር ባሕር መስመር ዘርግተዋል።

ይህም ዩክሬን ወደ ውጭ የምትልከውን የግብርና ምርት ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት ደረጃ ከማድረሱ በተጨማሪ ሌሎች ምርቶችንም እንድትልክ አስችሏል።

በ2024፤ በ15 በመቶ ያደገው የሀገሪቱ የወጪ ንግድ፤ 41.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል።

የኒኩሬል ማብላያ ጣብያ ፎቶ ከርቀት

2025 ለዩክሬን ምን ይመስላል?

የዩክሬን የፋይናንስ ሚኒስቴር በ2024 የነበረው የጦርነት ወጪ 52 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ገልጿል። ይህም በየቀኑ 142 ሚሊዮን ዶላር እንደ ማለት ነው።

በተጀመረው 2025 የዩክሬን መንግሥት ከሀገሪቱ አጠቃላይ በጀት አንድ አራተኛ የሚሆነውን 49 ቢሊዮን ዶላር ለመከላከያ እና ደኅንነት መድቧል።

የሀገሪቱ ወታደራዊ ያልሆኑ ወጪዎች በዓለም አቀፍ እርዳታ እየተሸፈነ ሲሆን፣ ከውስጥ የሚሰበሰብ ገቢ በአነስተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

የ2025ን በጀት ለመሸፈን አንዳንድ ታክሶች ጭማሪ ቢደረግባቸውም፤ ጭማሪው የሀገሪቱ ፊስካል ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው ጫና የንግዶችን እንቅስቃሴ በመጉዳት ጭራሽኑ ያነሰ ገቢ ሊያመጣ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

የዩክሬን ብሔራዊ ባንክ ገዢ አንድሪ ፒሽኒያ፤ ቃል የተገባው እርዳታ በጊዜው መምጣቱን የምንጠራጠርበት ምክንያት የለም ብለዋል።

ነገር ግን አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከዚህ ቀደም ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች እንዴት እንደሚመለከቷቸው ገና አልተገለጹም።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር፤ እነዚህ እርዳታዎች ቀጣይ በሚመጣው አስተዳደር ለዩክሬን እንደሚደርስ አረጋግጠው የነበረ ቢሆንም ሁኔታው “180 ዲግሪ ሊቀየር የሚችልበት ዕድል” እንዳለ የኢኮኖሚ ባለሙያው ድሜትሮ ቦያርቼክ ይናገራሉ።

በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሔ ለማበጀት የሚያስችሉ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች በአሜሪካ፣ በሩሲያ፣ በዩክሬን እና በአውሮፓ ሀገራት እየተከናወኑ ናቸው። ዘላቂ ሰላም የማግኘት ተስፋ ግን አሁንም ሩቅ ይመስላል።