የጦር መሳሪያ

ከ 7 ሰአት በፊት

በሱዳን በሦስት ቀናት ውስጥ ከ200 የሚበልጡ ያልታጠቁ ሰዎች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መገደላቸውን የአገር ውስጥ የመብቶች ቡድን አስታወቀ።

የሕግ ባለሙያዎች ስብስብ የሆነው ተሟጋች ቡድኑ ጥቃቱ የተፈፀመው የሱዳን ጦር በማይንቀሳቀስበት የሰሜን ነጭ ናይል ግዛት አል-ካዳሪስ እና ካህልዋት በተባሉ ስፍራዎች ነው ብሏል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች “በግድያ፣ እገታ፣ አስገድዶ ስወራ እና በዘረፋ” ጥፋተኛ ናቸው ሲል ቡድኑ አስታውቋል።

የእርስ በእርስ ጦርነቱ ሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ከመቀስቀሱ በፊት የሱዳን ጦር አጋር የነበረው እና በጀነራል ዳጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እስካሁን ለቀረበበት ክስ ምላሽ አልሰጠም።

ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መፈንቅለ መንግሥት ፈፅመው በጋራ ወደ ስልጣን የመጡ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ድጋፍ በተሰጠው የሲቪሊያን አስተዳደር ሽግግር ላይ ባሳዩት ልዩነት ወደ ግጭት ገብተዋል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጥቂት ከፍተኛ አመራሮች በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች መንግሥት መመስረት የሚያስችላቸውን ውጥን በኬንያ ያቀርባሉ ተብለው እየተጠበቁ ነው።

ሆኖም ተንታኞች እርምጃው በሱዳን ልዩነቱን የበለጠ ሊያስፋፋ ይችላል በሚል እያሳሰቡ ነው።

የሰብዓዊ ድርጅቶች 12 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን ከቀያቸው ያፈናቀለው የሱዳን ግጭት እንደሚያሳስባቸው በተደጋጋሚ ይገልፃሉ።

በግጭቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤ ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ዘግናኝ የተባሉ ጥሰቶችን በመፈፀም ስማቸው ይጠቀሳል።

የሱዳን ጦር በቅርቡ ካርቱም የሚገኘውን ዋና መስሪያ ቤቱን እና የተወሰነውን የከተማዋን ክፍል ዳግም መያዙን ተከትሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሽንፈትን አስተናግዷል።

ከዋና ከተማው በተጨማሪም ጦሩ ግዚራ የተባለ ቁልፍ ግዛት ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል አሸናፊነት መቀናጀቱ ተነግሯል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሽንፈቶችን ተከትሎ በዋናነት በሚቆጣጠረው ዳርፉር እና በከፊል በያዘው ኮርዶፋን ግዛቶች ተፃራሪ መንግሥት ለመመስረት እቅዱን ዳግም እያጤነ ነው።

በዚህም ኃይሉ በኬንያ ናይሮቢ ከአጋሮቹ ጋር ስብሰባ የተቀመጠ ሲሆን “የፖለቲካ ቻርተር ለሰላም እና አንድነት መንግሥት” የተባለ እቅድ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አል ቡርሃን እርምጃውን ውድቅ በማድረግ ሙሉ ለሙሉ ካርቱምን ለመቆጣጠር ቃል ገብተዋል።