የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አይንሸት አዳነ (ዶ/ር)

ማኅበራዊ በኢትዮጵያ ሦስተኛው የጨረር ሕክምና ማዕከል በጎንደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሊከፈት መሆኑ ተገለጸ

አበበ ፍቅር

ቀን: February 19, 2025

በአገር አቀፍ ደረጃ ከጥቁር አንበሳና ከጅማ ስፔሻላይዝድ ሆስቲታሎች ቀጥሎ  ሦስተኛው የጨረር ሕክምና ማዕከል በቅርቡ አገልግሎት ሊጀምር መሆኑን፣ የጎንደር አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ፡፡

ማዕከሉ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በርካታ የካንሰር ታማሚዎችን ተደራሽ እንደሚያደርግ፣ የጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አይንሸት አዳነ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱ በክልል ደረጃ ባለመኖሩ ሕመምተኞች ወደ ጥቁር አንበሳና ወደ ጅማ በመሄድ ረጅም ወረፋ ጠብቀው ይታከሙ እንደነበር የተናገሩት አይንሸት (ዶ/ር)፣ ከብዙ ድካም በኋላ  ወደ ሥራ ለመግባት መቃረባቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከውጭ አገር የሚመጡ ባለሙያዎች ጭምር አገልግሎት በመስጠት እንደሚሳተፉ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከሁለትና ከሦስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ሥራ ለመጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አክለዋል፡፡

ሆስፒታሉ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት ኅብረተሰቡን በሕክምና ሲያገለግል መቆየቱን የጠቀሱት አይንሸት (ዶ/ር) ካለፉት ሰባ ዓመታት ወዲህ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በድኅረ ምረቃ በማስተርስና በፒኤችዲ፣ እንዲሁም በስፔሻሊቲና በሰብ ስፔሻሊቲ  ባለሙያዎችን በማብቃት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉና የጤና ሳይንስ ኮሌጁ በአንድ ላይ መሆናቸው በተግባር የተፈተኑና ብቁ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችን ለማፍራት አመች ሁኔታ መፍጠራቸውን፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የመማር ማስተማርና መሠረታዊ የሆነውን የጤና አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይሁን እንጂ ሁለቱንም ማስቀጠል የሚያስችል በቂ በጀት እየተበጀተላቸው እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ችግሩ መሠረታዊና ለብዙ ዓመታት የቆየ ነው ያሉት አይንሸት (ዶ/ር) ጥራት ያለው የሕክምናና የትምህርት አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ በጀት እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ ችግሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ካልተሠራ በጣም አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡

ከበጀት በተጨማሪ ሌሎች አካባቢያዊና አገራዊ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ገልጸው፣ የግብዓት አቅርቦት እጥረትና በወቅታዊ ችግሮች ምክንያት የመንገድ አለመኖር ለዘርፉ ተጨማሪ ተግዳሮቶች ናቸው ሲሉ አክለዋል፡፡

ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ ከኤርትራና ከሱዳን የሚመጡ ታማሚዎችን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የኀብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንደሚሰጥ የጠቀሱት አይንሸት (ዶ/ር)፣ የበጀትና የአቅርቦት አለመመጣጠን እንደሚያጋጥመው ተናግረዋል፡፡

በዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ታካሚዎችን እንደሚያስተናግዱ ጠቁመው፣ ተኝተውና በተመላላሽነት ለሚታከሙ ሰዎች የሚያገለግሉ ከ900 በላይ አልጋዎች አሉት ብለዋል፡፡

አካባቢው ተላላፊ ለሚባሉ በሽታዎች ተጋላጭ በመሆኑ ለወባ፣ ለቲቢና ለኤችአይቪ/ኤድስ ታካሚዎች በስፋት አገልግሎት እንደሚሰጥ ያብራሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የአዋቂዎችና የሕፃናት ፅኑ ሕሙማን ማከሚያ ከፌስቱላና ከፆታዊ ጥቃቶች ጋር የተገናኙ ሁሉን አቀፍ የሆኑ አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን አካቶ መያዙን ጠቁመዋል፡፡

በአገሪቱ ካለው ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ቁጥር አንፃር ያለው የጤና ባለሙያ በጣም ውስን መሆኑን የተናገሩት አይንሸት (ዶ/ር)፣ ነገር ግን እንደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እስካሁን ባሉት የጤና ባለሙያዎችና ሐኪሞች የተሻለ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በተወሰኑ ሰብ ስፔሻሊቲ አገልግሎት ላይ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩን ተናግረው፣ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ባለሙያዎች የመልቀቅ አዝማሚያ መኖሩን ጠቅሰው ችግሩ ያን ያህል አሳሳቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከተሟሉ ባለው የጤና ባለሙያና ሐኪም የተሻለና ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ የእናቶችን እርግዝና ከመከታተል ጀምሮ እንደ ቲቪ፣ ኤችአይቪ/ኤድስና ፌስቱላ፣ እንዲሁም ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዙና ሌሎች ከአሥር በላይ የሚሆኑ ነፃ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡

እነዚህን አገልግሎቶች ኅብረተሰቡ በነፃ እንዲያገኝ በሕግ ጭምር የተፈቀደ መሆኑን የጠቀሱት አይንሸት (ዶ/ር)፣ ከእነዚህ ባሻገር ለአቅመ ደካሞችንና ከፍለው መታከም ለማይችሉ ሰዎች ነፃ አገልግሎት በመስጠት ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡