ማኅበራዊ
ቡናን በዘመናዊ ገበታ

አበበ ፍቅር

ቀን: February 19, 2025

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ ጎልቶ ከሚጠቀስበትና ከምትታወቅባቸው ሀብቶቿ መካከል ቡና ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡ ቡና ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር ባለው የአፈላል ሥነ ሥርዓት ሰዎችን እርስ በርስ ያገናኛል ያቀራርባል፡፡

ሰዎች በሐዘናቸውም ሆነ በደስታቸው ሲገናኙ የመጀመሪያ ሥራቸው ቡና ማፍላት ሲሆን ከቡናው ጋር የማይለየው የቡና ቁርስና የእጣኑ ጭስ የሥነ ሥርዓቱ ማድመቂያዎች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓትና የሚፈላባቸው ዕቃዎች ጭምር  ከጊዜ ወደ ጊዜ ይዘታቸውን እየቀየሩ መምጣታቸው ይስተዋላል፡፡ ቡናና ጀበና አብረው የተፈጠሩ እስኪመስል ለብዙ ዘመናት ኑረዋል፣ ዛሬም ቀጥለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቡናና ጀበናን የሚያለያዩ ዘመናዊ የቡና ማፊያ ማሽኖች  መምጣት ጀምረዋል፡፡

አዲስ የሚመጡ የቡና ማፈያ ማሽኖች በአንድ በኩል የቡናውን ጣዕም ሊያሳጣው ይችላል የሚሉ አካላት ሲኖሩ በሌላ በኩል ማሽኖቹ ቡና ከዓለም ገበያ ጋር ይበልጥ ለማስተሳሰር አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ያስረዳሉ፡፡

‹‹ኢትኮፍ ቴስት ትሬዲንግ›› የተባለ የግል ድርጅት የተለያዩ የቡና ማፊያ ማሽኖችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ማሽኖቹ ቡናን በተጣራና የዓለም የቡና ገበያ ደረጃን የሚያስጠብቅ ሆኖ እንዲዘጋጅ የሚያስችሉ መሆናቸውን የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አቅሌሲያ ሰሎሞን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ማሽኖቹ የተለያየ መጠን ሲኖራቸው በአንድ ጊዜ ከአንድ ሰው እስከ መቶ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ማሽኖቹ ቡናን በቀላሉና ተጠቃሚዎች በሚፈልጉት ዓይነት አፍልቶ ለመጠቀም አመቺ መሆናቸውን የተናገሩት ሥራ አስኪያጇ ይህም ቡናን ቆልቶና በጥሬው በማሸግ በርካሽ ገበያ ለውጭ የማቅረብ ልማድን ያስቀራል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ማሽኖቹ ቡናን በማፍላት፣ በማቀዝቀዝና በማቅጠን ወይም በማወፈር እንደሰው ፍላጎት ለማቅረብ እንደሚያስችሉ ወ/ሮ አቅሌሲያ ያክላሉ፡፡

ኢትኮፍ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚያዘጋጀውን ቡና እስከ ማፊያ ማሽኑ ለአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ከማቅረብ ባሻገር፣ አገር ውስጥ ለሚገኙ ኤምባሲዎች፣ ዲፕሎማቶችና ለአየር መንገዶች ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ለባንኮችና ለሌሎች መሰል ተቋማት እንደሚያከፋፍሉ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ የቡና ምርቶችን ከጅማ፣ ከሐረር፣ ከይርጋጨፌና ከሌሎች የአገሪቱ  አካባቢዎች በማስመጣትና የተለያዩ እሴቶችን በመጨመር ለመጠጣት ዝግጁ እስኪሆኑ ድረስ በቴክኖሎጂ በመታገዝ፣ ለውጭና ለአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ማቅረብ መጀመሩን ሥራ አስኪያጇ ገልጸዋል፡፡

 ሙሉ ትኩረቱን ቡና ላይ በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ ምርትን በራሱ ፋብሪካ በማዘጋጀት ለውጭና ለአገር ቤት ተጠቃሚዎች ለማቅረብ መዘጋጀቱን ወ/ሮ አቅሌሲያ አስታውቀዋል፡፡

ቡናው ውስጥ የተለያዩ እሴቶችን በመጨመር በፋብሪካ ከተዘጋጀ በኋላ ማፊያ ማሽኖችን በመጠቀም በቀላሉ መገልገል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡  

ከመቶ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን የገለጹት ወ/ሮ አቅሌሲያ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በሚል ከገቢያቸው አሥር በመቶ የሚሆነውን ለተለያዩ  በጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ  እንደሚያደርጉ አክለዋል፡፡

ባህላዊ የቡና አቀራረብን ጨምሮ የቡና ቅምሻ ሥነ ሥርዓትን፣ እንዲሁም ሌሎች ለከተማዋ ቱሪዝም ዕድገት አስተዋጥኦ ያደርጋሉ የተባሉ የቡና ትርዒት የሚቀርብበት የቡና ማዕከል ነገ ሐሙስ የካቲት 13 ቀን ተመርቆ እንደሚከፈት ተናግረዋል፡፡