

February 19, 2025
ትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግ ፋርሚንግ በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ሳይንሳዊ ጥናቶችን የሚያደርግ ነው፡፡ በግብርናው ያሉ የዕውቀት ክፍተቶችን ለመሙላትም ከተለያዩ ዩኒቨርቲዎች ጋር በመቀናጀት ትምህርትና ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በተለይም በዶሮ ዕርባታ ዘርፍ፣ የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን በማቅረብ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ክትባቶችን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡ አቡኑ አንዳርጌ (ዶ/ር) የትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግና ፋርሚንግ ባለቤትና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ድርጅቱ በግብርናው መስክ ስለሚያካሂዳቸው ጥናቶች፣ በኢትዮጵያ የዶሮ ዕርባታ የሚገኝበትን ደረጃና ዘርፉ እየገጠሙት ያሉ ችግሮችን በተመለከተ የማነ ብርሃኑ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡– ድርጅታችሁ የተቋቋመበት ዓላማ ምንድነው?
አቡኑ (ዶ/ር)፡- ትረስት አግሮ ኮንሰልቲንግና ፋርሚንግ በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና ክፍተቶችን ለመሙላት በማሰብ በ2015 ዓ.ም. የተቋቋመ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ፈጽሞ ለብዙዎች በከተማ ግብርና ዙሪያ ትምህርትና ሥልጠና ሲሰጥም ቆይቷል፡፡፡ በተጨማሪም በግብርናና በእንስሳት ልማት ዘርፍ የተለያዩ ችግር ፈቺ ጥናቶችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡– ድርጅታችሁ የማማከር አገልግሎት የሚሰጠው ለማን ነው? በየትኞቹ ዘርፎች ላይስ ያማክራል?
አቡኑ (ዶ/ር)፡- እኔን ጨምሮ በድርጅታችን ውስጥ የሚገኙ 38 የሚሆኑ ባለሙያዎች በግብርናና በእንስሳት ሕክምና ዙሪያ ትምርታችንን የተከታተልንና በተለያዩ ተቋማት ስናገለግል የቆየን ነን፡፡ በመሆኑም በነበርንባቸው ተቋማት በዘርፉ ያስተዋልናቸውን የዕውቀት ክፍተቶች ለመሙላት በርካታ ጥናቶችን አካሂደናል፡፡ ጥናቶቻችንንም ለመንግሥትና ለግል ተቋማት ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የእንስሳት መድኃኒት ቤት በመክፈት ግብዓቶችን እያቀረብን እንገኛለን፡፡ በተለይም በዘመናዊ የዶሮ ዕርባታ መስክ ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ የዶሮዎች ውኃ መጠጫ ከውጭ አገር በማስመጣት ለዶሮ አርቢዎች እንዲጠቀሙበት አድርገናል፡፡ ቫይታሚን፣ መድኃኒትና ክትባት በማቅረብ ላይ እንገኛለን፡፡ በተጨማሪም በወተት ላም ዕርባታ፣ በንብና በአሳማ፣ በአሳ እንዲሁም በመኖ ማቀነባበር ዙሪያ የማማከርና የአዋጭነት ጥናት የፕሮፖዛል ሥራዎችን እንሠራለን፡፡
ሪፖርተር፡– ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ትምህርትና ሥልጠና እየሰጣችሁ እንደምትገኙ ገልጸውልኛል፡፡ እስካሁን ለምን ያህል ሰዎች ሥልጠና ሰጣችሁ?
አቡኑ (ዶ/ር)፡- እስካሁን በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ለ3,530 ሰዎች የከተማ ግብርናን በተመለከተና ስለዘመናዊ እንስሳት ዕርባታ ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ሥልጠናውንም ከዩኒቨርሲቲዎችና ከመንግሥት ጋር በመሆን በጥምረት ለመስጠት ችለናል፡፡
ሪፖርተር፡– በተለየ መልኩ በዘመናዊ የዶሮ ዕርባታ የምትሠሩት ሥራ ምንድነው?
አቡኑ (ዶ/ር)፡- ትረስት ኮንሰልቲንግና ፋርሚንግ በእንቁላልና በሚሰጡት የሥጋ ምርት የተለዩና የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን ለአርቢዎች ያቀርባል፡፡ እስካሁንም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዶሮዎችን ለማሠራጨት ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ሰቨን ኬ የተሰኘ ክትባት ይፋ አድርገናል፡፡ ይህ ክትባት ቀደም ሲል ለዶሮዎች በየሁለት ወሩ የሚሰጠውን ክትባት የሚያስቀር ነው፡፡ በየሁለት ወሩ የሚሰጠውን ክትባት አጠቃቀሙንና አያያዙን ባለማወቅ ሰዎች በብዙ ሲቸገሩ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህን ችግር የሚቀርፍና የሚያቃልል አንድ ጊዜ የሚሰጥ ሆኖ ሰባት በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል ክትባት ክትባት አስተዋውቀናል፡፡ ይህም ዶሮዎች በሕይወት ዘመናቸው ሳይታመሙ ጤነኛ እንዲሆኑ የሚረዳ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ይህን ክትባት በሰፊው ለመስጠት የሚያስችል የመድኃኒት አቅርቦት በአገር ውስጥ ይኖራል?
አቡኑ (ዶ/ር)፡- መድኃኒቱ በእኛም ፋርማሲ ሆነ በሌሎችም ቦታዎች ይገኛል፡፡ ነገር ግን መድኃኒቱ ስላለ ብቻ ማንም ሰው የሚሸጠው አይደለም፡፡ እኛም የምናደርገው ዶሮዋን ከትበን የተከተበችውን ዶሮ መሸጥ ነው፡፡ ይህም ክትባት ጤናቸው የተጠበቀና ምርትና ምርታማነታቸው ከፍ ያለ ዶሮዎች እንዲኖሩን ከማድረግ አንፃር ጉልህ ድርሻ የሚኖረው ነው፡፡
ሪፖርተር፡– በዶሮ ዕርባታ ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶች ምንድናቸው?
አቡኑ (ዶ/ር)፡- በዘርፉ ላይ ካሉ ተግዳሮቶች አንዱ የመኖ መወደድ ነው፡፡ የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎች በተፈለገው ልክ አለመገኘት ደግሞ ሌላው ችግር ነው፡፡ በተጨማሪም ሕገወጥ ደላላና ያለንግድ ፈቃድ በዶሮ ዕርባታ ላይ የሚንቀሳቀሱ ግለቦች የዘርፉ ችግሮች ናቸው፡፡ ንግድ ፈቃድ ኖሮት ግብር እየከፈለ የሚኖረው አርቢ፣ ዶሮ አርብቶ ሦስት መቶ ሲሸጥ ያለፈቃድ የሚያረባውም እኩል ሦስት መቶ ብር ሲሸጥ ይታያል፡፡ ይህ በምንም መልኩ ፍትሐዊ ስላልሆነ መስተካከል ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩት ሸሽተው ከዘርፉ እንዳይወጡ ለማድረግ ሕገወጦችን ሕጋዊ መንገድ ተከትለው እንዲሠሩ ማድረግ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡– የማኅበረሰባችን የእንቁላልና የዶሮ ሥጋ አመጋገገብ ባህል ምን ይመስላል?
አቡኑ (ዶ/ር)፡- አገራችን በዶሮ ሀብት ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ናት፡፡ 60 ሚሊዮን ዶሮዎች በኢትዮጵያ አሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ነገር ግን እንቁላልና የዶሮ ሥጋ የመብላት ባህላችን እጅግ የወረደ ነው፡፡ ለምሳሌ ኬንያ በዶሮ ሀብት ቁጥር ከእኛ ያነሰች ናት፡፡ 47 ሚሊዮን ያህል ዶሮዎች ያሏት ቢሆንም፣ እንቁላል ግን በከፍተኛ ደረጃ ታመርታለች፡፡ ዜጎቿም የዶሮ ሥጋና እንቁላል የመመገብ ልማዳቸው በዚያው ልክ ያደገ ነው፡፡ ወደ አገራችን ስንመጣ ያለው ግንዛቤ አናሳና ያለውም የዕውቀት ክፍተት የሰፋ ነው፡፡ እንዳለን የዶሮና የሕዝብ ብዛት ምርቱን እየተጠቀምን ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ በመንግሥት ‹‹የሌማት ትሩፋት›› ተብሎ ከሚሠራበት ዘርፍ አንዱ ይህ በመሆኑ ወደፊት ልማድና ባህሉ ይቀየራል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡– የእንቁላል ዋጋ ላይ በየዕለቱ ልዩነት አለ፡፡ አንዳንድ ግለሰቦችም ኢትዮጵያ ካላት የዶሮ ሀብት አንፃር እንቁላል በአነስተኛ ዋጋ መሸጥ አለበት ይላሉ፣ እዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
አቡኑ (ዶ/ር)፡- እንቁላል የሚሸጥበትን ዋጋ ሰው ሳይሆን የምርት ዋጋው ነው የሚወስነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ዶሮ እንቁላል ለመጣል ምን ያህል ገንዘብ ወጥቶባታል የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡ አንድ እንቁልል ለማምረት ከስምንት ብር በላይ ነው፡፡ የቤት ኪራይ፣ የሠራተኛ፣ የመኖ፣ የቫይታሚንና የክትባት ተብሎ ሲሰላ ወጪው ከፍ ይላል፡፡ አነኚህ ነገሮች ተደማምረው የእንቁላልን ዋጋ ሊያስወድዱት ችለዋል፡፡ በየዕለቱ ከፍና ዝቅ እያለ፣ ደላላም እጁን እያስገባበት ዋጋው ከሚዋዥቅ መንግሥት የዶሮ አርቢዎችን የምርት ዋጋና ትርፋቸውን በማስላት ወጥ የሆነ ተመን ቢቀመጥ የሚል የራሴ ምክረ ሐሳብ አለኝ፡፡ አርቢውም ክፍል እንቁላል መሸጥ አያዋጣም በማለት ከዘርፉ እንዳይወጣና ተጠቃሚው ማኅበረሰብም በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል ብዬ አምናለሁ፡፡