ሔለን ተስፋዬ

February 19, 2025

ድጎማ የተደረገበት የ2017/18 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ዋጋው በእጥፍ መጨመሩን በአማራ ክልል የዳሞት ኅብረት ሥራ ዩኒየን አስታወቀ፡፡

የዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ አገሬ ጥጋቡ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የፌዴራል መንግሥት በአንድ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ 3‚700 ብር ድጎማ ቢያደርግም ዋጋው ግን በእጥፍ ጨምሯል፡፡

ሥራ አስኪያጁ የዋጋውን ልዩነት ከዓምናው ጋር በማነፃፀር፣ አንድ ኩንታል ዳፕ ማዳበሪያ 3‚700 ብር እንደነበር አስታውሰው፣ ዘንድሮ ግን 7‚835 ብር መግባቱን፣ አንድ ኩንታል ዩሪያ ደግሞ ዓምና 3‚650 ብር እንደነበር፣ ዘንድሮ ደግሞ 6‚113 ብር መድረሱን አስረድተዋል፡፡

ለዩኒየኑ ከቀረበው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 80 ሺሕ ኩንታል ዳፕና 72 ሺሕ ኩንታል ዩሪያ መሆኑን፣ በዕቅዱ መሠረት የሚያስፈልገው አንድ ሚሊዮን 76 ሺሕ ኩንታል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከውጭ የተገዛበትን ጨምሮ የዩኒየኑ ትርፍ ሳይጨምር ዳፕ በኩንታል 11‚000 ብር መገዛቱን ገልጸው፣ ዩሪያ ደግሞ እስከ 10‚000 ብር እንደሚደርስ ነው ያስረዱት፡፡

በክልሉ ባለው የፀጥታው ችግር ምክንያት በእጀባ እስከ ምዕራብ ጎጃም ለዳሞት ኅብረት ሥራ ዩኒየን እስካሁን የደረሰው 152‚000 ኩንታል ማዳበሪያ እንደሆነ ገልጸው፣ ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር መዘግየቱን ተናግረዋል፡፡

ከቀናት በፊት የአማራ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ የአፈር ማዳበሪያን በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

በ2017/18 የምርት ዘመን ክልሉ 8.8 ሚሊዮን ኩንታል ለማቅረብ ማቀዱን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸው፣ እስካሁን 2.1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጂቡቲ ወደብ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ከእዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮን 21 ሺሕ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለኅብረት ሥራ ዩኒየኖች መቅረቡን ገልጸው፣ የክልሉ መንግሥት የአፈር ማዳበሪያ ለማግኘት ከ79 ቢሊዮን ብር በላይ ዋስትና መግባቱን ነው ያስረዱት፡፡

ይህ ዋስትና የክልሉ ዓመታዊ ከሚሰበሰበው መደበኛ በጀት 71 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር ተቀራራቢ እንደሆነ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡

አክለውም በአገር አቀፍ ደረጃ ለአፈር ማዳበሪያ ብቻ 84 ቢሊዮን ብር ድጎማ መደረጉን፣ ይህ ከዓመታት በፊት የአገሪቱ ዓመታዊ በጀት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ድጎማው በአንድ ኩንታል አፈር ማዳበሪያ 3‚700 ብር እንደሆነ፣ ባለፈው ዓመት ከ20 እስከ 25 ቢሊዮን ብር መደጎሙን ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ 1.3 ቢሊዮን ዶላርና 156 ቢሊዮን ብር ለማዳበሪያ ግዥ በጀት የተመደበ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡