ሔለን ተስፋዬ

February 19, 2025

የአገልግሎቱ ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ታዬ

ደንበኞች ከሚፈልጉት የአገር ውስጥ አቅራቢ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ትራንስፎርመር በጊዜያዊነት እንዳይገዙ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡

አገልግሎቱ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሁሉም የክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽሕፈት ቤቶች በላከው ሰርኩላር፣ ደንበኞች (ተቋማት) በራሳቸው የኃይል ማከፋፈያ ትራንስፎርመርና ኮምፓክት ዲስትሪቢዩሽን ሰብስቴሽኖች በመግዛታቸው የጥራት ችግር እያጋጠመ ስለሆነ፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እስኪሰጥ ድረስ እንዳይገዙ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

የአገልግሎቱ ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ታዬ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአገር ውስጥ ተገጣጥመው የሚቀርቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ትራንስፎርመሮችን ደንበኞች በራሳቸው ስለሚገዛቸው አንዳንዴ የጥራት ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አገልግሎቱ የግብዓትና የፋይናንስ እጥረት ስለነበረበትና የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት የሚፈልጉ በርካቶች በመሆናቸው፣ ትራንስፎርመር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ግብዓቶችንም አቅም ያላቸው ደንበኞች ገዝተው ኃይል ሲያገኙ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

አገልግሎቱ እስካሁን ትራንስፎርመር ከውጭና ከአገር ውስጥ ገጣጣሚዎች (አቅራቢዎች) በብዛት ሲገዙ መቆየታቸውን፣ ነገር ግን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከፍለው ኃይል ለማግኘት የሚጠባበቁ በርካታ በመሆናቸውና አቅም ያላቸው ደንበኞች እንዲገዙ በአማራጭነት ሲተገበር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ትራንስፎርመር ዋጋው ውድና ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ ለረዥም ዓመታት አገልግሎት መስጠት ስላለበት፣ በአገልግሎቱ በወጣው የጥራት መሥፈርት መሠረት ያልቀረቡ ኃይል አስተላላፊ ትራንስፎርመሮች እንደሚታገዱ ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ የአገልግሎቱን የጥራት መሥፈርት ያላሟሉ ትራንስፎርመሮችን የአገር ውስጥ አቅራቢዎች ለደንበኞች ሸጠው ኔትወርክ ውስጥ የተገኙ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረት ደንበኞች ላልተወሰነ ጊዜ በራሳቸው እንዳይገዙ፣ ከላይ ተከሰተ የተባለው ችግር መፍትሔ እስኪሰጠው ድረስ ሙሉ በሙሉ ከአገልግሎቱ ብቻ እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡

በአገር ውስጥ ትራንስፎርመርና ሌሎች ግብዓቶችን የሚያመርቱ አቅራቢዎች ሙሉ በሙሉ የአገልግሎቱን ፍላጎት እንደማያሟሉ፣ ክፍተቱን ለመሙላት ከውጭ አገሮች ግዥ እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡

ይሁንና አገልግሎቱ አሁንም ቢሆን አቅራቢዎች የሚያመርቱትን በሙሉ እንደሚገዙ፣ ነገር ግን በጊዜያዊነት በደንበኞች ተገዝተው ኃይል በሚጠይቁት በጊዜያዊነት እንዲያቆሙ ብቻ መደረጉ ተናግረዋል፡፡

ከለውጡ በፊት በኢትዮጵያ የኃይል ማከፋፈያ ትራንስፎርመርና የኮምፓክት ዲስትሪቢዩሽን ሰብስቲሽን ብቸኛ አቅራቢ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ብቻ እንደነበረ፣ ከዚያ በኋላ ግን 12 ኩባንያዎች ከላይ የተጠቀሱትን ግብዓቶች በአገር ውስጥ በመገጣጠም ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ትራንስፎርመር ከሚገጣጥሙ ኩባንያዎች የአንዱ ኃላፊ ስለጉዳዩ ለሪፖርተር እንዳሉት፣ ለዓመታት የሚያመርቱት ትራንስፎርመር በአገልግሎቱ አማካይነት ጥራቱ ተገምግሞ ሲቀርብ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ወፍጮ ለሚተክሉና ትልልቅ ድርጅቶችን ለመክፈት ለሚፈልጉ ደንበኞች ትራንስፎርመር ሲያቀርቡ መቆየታቸውን፣ ደንበኞቹም የሚገዙትን ትራንስፎርመር በኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚያስፈትሹ ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱ በማረጋገጥ የብቃት ማረጋገጫ ከሰጠ በኋላ ደንበኞች ክፍያ እንደሚፈጽሙ አስረድተው፣ በወጣው ሰርኩላር ምክንያቱ የጥራት ችግር ሳይሆን ከአሥራ ሁለቱ ኩባንያዎች ትራንስፎርመር ገዝቶ ለመሸጥ በመፈለጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህ ማለት 12 አምራች ኩባንያዎችን ለአገልግሎቱ አቅራቢ እንጂ በቀጥታ ከደንበኞች ጋር እንዳይገናኙ እንደሚያደርጋቸው፣ አንድ ተቋም ብቻ የሚገዛቸው ከሆነ በዋጋ እንደሚጎዱና አማራጭ ገበያ እንደሚያሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡

ይህ አሠራር የኩባንያዎቹን መገንባት አላስፈላጊ እንደሚያደርግ፣ አገልግሎቱ እንደ አንድ ገዥ ደንበኛ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በምሳሌነት ሲያሳዩም ኢትዮ ቴሌኮም ኔትወርክ ዘርግቶ፣ የሞባይል ቀፎ ከሌላ አካል የገዛ ሰውን ኔትወርክ አታገኝም እንደ ማለት ነው ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞች ትራንስፎርመርና መሰል ግብዓቶችን ከአገር ውስጥ አምራቾች እንዳይገዙ የሚለው ውሳኔ ትክክል አለመሆኑን፣ ምርቱን ከውጭ የሚያስገቡ ባለሀብቶች ስላሉ የጥራት ጉዳይ እንደ ችግር ከተነሳ መጠየቅ ያለበት የሚመረቱ ትራንስፎርመሮችን ፍተሻ የሚያደርገው አገልግሎቱ መሆን እንደበረበት አስረድተዋል፡፡

በአማካይ በቀን ከ20 እስከ 25 ትራንስፎርመሮች እንደሚገጣጥሙ፣ ነገር ግን ደንበኞች የማይገዙ ከሆነ የጥገና አገልግሎት ላይ ብቻ እንደሚሰማሩ ተናግረዋል፡፡

አንድ ትራንስፎርመር የሚገጣጥም ድርጅት ለ75 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፣ ነገር ግን ለአገልግሎቱ ብቻ በማቅረብ ለደንበኞች መሸጥ የሚያቆሙ ከሆኑ የሠራተኞች ቁጥር ሊቀንስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡