ዜና
ለዳኞች ከለላ የሚሰጥ አዋጅ እንዲፀድቅ መደረጉን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለጸ

ዮናስ አማረ

ቀን: February 19, 2025

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች ጥበቃና ከለላ ጉዳይን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች የያዘ ‹‹የፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ›› በክልሉ ምክር ቤት መፅደቁን ገለጸ፡፡ በክልሉ በተለዩ ዕርከኖች ባሉ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ የፍርድ ውሳኔዎችን ጥራት በተሻለ ለማስጠበቅም ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የስድስት ወራት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቶችን የተመለከቱ አራት አዋጆችና አንድ ደንብ ተረቀው በክልሉ ምክር ቤት በማፀደቅ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቋል፡፡

ከእነዚህ አዋጆች መካከልም ለዳኞች ጥበቃ ለማድረግ ያስችላል የተባለው ‹‹የአማራ ብሔራዊ ክልል ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ›› እንደሚገኝበት ጠቁሟል፡፡ ከዚህ አዋጅ በተጨማሪም የሕግና የፍትሕ ኢንስቲትዩትን እንደገና ለማቋቋም የተዘጋጀ አዋጅ፣ በአማራ ብሔራዊ ክልል የባህል ፍርድ ቤቶች ለማቋቋምና ዕውቅና ለመስጠት የተዘጋጀ አዋጅ፣ እንዲሁም የአማራ ብሔራዊ ክልል ተከላካይ ጠበቆች አዋጅ የተባሉ አዋጆች መፅደቃቸውን አክሏል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የዳኝነት አገልግሎት ክፍያን ለመወሰን የተዘጋጀ ደንብ ተጠናቆ ለክልሉ ምክር ቤት ተልኳል ብሏል፡፡

የክልሉ ፍርድ ቤቶች የስድስት ወራት የሥራ ክዋኔን የገመገመው ሪፖርቱ፣ ችግር ያለባቸውን ጉዳዮችም ዘርዝሯል፡፡ የበጀት እጥረት፣ የቢሮና ችሎት የማስቻያ ቦታዎች እጥረት፣ የዳኞች መኖሪያ ቤትና የተሽከርካሪ ችግር አለመቀረፋቸውን ገልጿል፡፡

የዳኞች መታሰርና የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ለመፈጸም አንዳንድ አካላት እንቢተኝነት ማሳየታቸው፣ ለክልሉ የፍትሕና የዳኝነት ሥርዓት እንቅፋት መሆኑንም በግልጽ አስቀምጧል፡፡

በወረዳ፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤትና በሰበር ሰሚ ችሎት በክልሉ የተለያዩ ምድብ ችሎቶች በስድስት ወራት የቀረቡና ታይተው ውሳኔ ያገኙ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮችን ዕድገት በአኃዝ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ ዳኞች በዕረፍት ጊዜያቸው ጭምር መዝገቦችን መመልከታቸው የፍርድ ውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱ እንዲቀላጠፍ ዕገዛ ማድጉንም ያትታል፡፡ በቴክኖሎጂ በተለይም በዲጂታል ቴክኖሎጂ አሠራሮች ላይ የማሻሻያ ሥራዎች በመሠራታቸው፣ እንዲሁም የአሥር ዓመቱን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ የተከተለ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ሥራ በመተግበሩ የተሻለ የአፈጻጸም ውጤት መገኘቱንም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት መግለጫ እንደሚጠቁመው፣ በስር ፍርድ ቤቶች ብይን ያገኙ ጉዳዮች በላይ ፍርድ ቤቶች የሚፀኑበት አኃዝ በሚፈለገው ልክ አለማደጉን በመጥቀስ፣ ይህም የፍርድ ጥራት አለመደረግ ምልክት መሆኑን ነው የገለጸው፡፡ የፍርድ ጥራት የሚያጓድሉ ችግሮችን በመለየት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ሥልጠናዎችን ማመቻቸት አስፈላጊ ስለመሆኑም ያስረዳል፡፡   

ለዳኞች ጥያቄና ከለላ መስጠት የግለሰብ ዳኛ ጉዳይ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የክልሉን የፍትሕና ዳኝነት ሥርዓት የተመለከተ ጉዳይ መሆኑንም ነው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሪፖርት ያመለከተው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በአማራ ክልል የዳኞች ያለ መከሰስ መብት የሕግ ከለላ እንዲያገኝ መደረጉን አድንቆ ነበር፡፡ ኢሰመኮ በመግለጫው የአማራ ክልል ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ክልል ፍርድ ቤቶች የማጠናከሪያ አዋጅን ማፅደቁን በጎ ዕርምጃ ሲል ገልጾታል፡፡

ከዚህ ቀደም በክልሉ ዳኞች ላይ የሚደርሰውን እስከ እስር የሚደረግ ጫና እንዲቆም ሲወተውት መቆየቱን ኢሰመኮ አመልክቷል፡፡ ይህ ውትወታ ሰሚ አግኝቶ ለዳኞች የሕግ ከለላ የሚሰጥ አዋጅ አሁን መፅደቁ ትልቅ ውጤት ሆኖ እንዳገኘው ነው የገለጸው፡፡