

ዘንድሮ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሆነው የተሰየሙት የአንጎላ ፕሬዚዳንት ጃኦ ሎሬንሶ የኅብረቱን ጉባዔ ሲያስጀምሩ
February 19, 2025
ከየካቲት 5 እስከ የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎችና 46ኛው የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባዔ እሑድ እኩለ ሌሊት አካባቢ ተጠናቋል፡፡
በመዲናዋ ለአምስት ቀናት ያህል በተካሄደው ዓመታዊ የአባል አገሮቹ ጉባዔ ከ35 በላይ መሪዎች እንደሚታደሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀድሞ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከጉባዔው በኋላ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳው በአጠቃላይ ለጉባዔው የተሳተፉት ፕሬዚዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ ቁጥሩ ከ38 በላይ ጉባዔውን ተካፍለዋል፡፡

በዚህ ትልቅ አኅጉራዊ ሁነት ኅብረቱ ካሰናዳው ዓመታዊ ጉባዔ ባልተናነሰ የኢትዮጵያ መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ እያካሄደው ያለውን የኮሪደር ፕሮጀክት ለሚመጡ ለእንግዶች ሁሉ ለማሳየትና ለማስጎብኘት ደፋ ቀና ሲል መቆየቱንና በርካታ ዝግጅቶችን ማድረጉን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ብርቱካን አያኖ (አምባሳደር) ከጉባዔው ጥቂት ቀናት አስቀድመው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር፡፡ በከተማዋ ጎዳናዎች እንግዶችን ለመቀበል የሚያስፈልጉ ምቹና ቅንጡ አዳዲስ ሰሌዳ ያልወጣላቸው ተሽከርካሪዎችን ጭምር ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመነጋገር፣ እንዲሁም ከውጭ የመጡ የትራፊክ ፖሊስ አጃቢ አሠልጣኞች ጭምር በማሳተፍ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ነበር፡፡
ጉባዔው በተካሄደባቸው ቀናት የእንግዶች መግቢያና መውጫ የሆኑ የአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች በአመዛኙ ለነዋሪዎቹም ክፍት የነበሩ ቢሆንም፣ በርካታ አሽከርካሪዎች ሲሰጡት በነበረው አስተያየት ከትራፊክ ፖሊሶችና ከፀጥታ አካላት መንገዶቹ ክፍት ሆነው እያለ የማመናጨቅ፣ የመሳደብና የማንገላታት ድርጊቶች እንደነበሩ፣ አሽከሪካሪዎችም በፖሊስ ውጡ ግቡ በሚል ድንገትኛ ጩኸትና ማስፈራሪያ ድምፅ የተነሳ፣ በድንጋጤ ከግጭት ለጥቂት መትረፋቸውን የደረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የዘንድሮ ዓመታዊ ጉባዔ ሰላማዊ በሚባል ሁኔታ መጠናቀቁን መንግሥት የገለጸ ሲሆን፣ ለቀናት በዘለቀው አኅጉራዊ ስብሰባ የከተማዋን የፀጥታ ድባብ ላይ አስተያየት የሰጡ ግለሰቦች በኅብረቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ጭምር ከፍተኛ የፀጥታ አካላት እንቅስቃሴ ማስተዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ለዘርዓ አፍሪካውያን›› በሚል መሪ ቃል ጉባዔውን ያደረገው ኅብረቱ የ55 አባል አገሮች ስብስብ ቢሆንም ስድስት አባል አገሮች ማለትም ኒጀር፣ ጋቦን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ፣ ሱዳንና ማሊ ባጋጠማቸው የውስጥ የፖለቲካ ቀውስና በአኅጉሩ እየተለመደ በመጣው የመፈንቅለ መንግሥት አባዜ ምክንያት ከአባልነት አግዷል፡፡
ኅብረቱ ከመሣሪያ ድምፅ የፀዳችና የበለፀገች አፍሪካን ዕውን ማድረግ የአኅጉሪቱ የ2063 ዓብይ አጀንዳ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ቢናገርም፣ በአኅጉሩ በርካታ አካባቢዎች አሁንም በመሣሪያ የሚታመሰውና በግጭት የሚፈናቀለው የሕዝብ ቁጥር የትየለሌ እየሆነ መጥቷል፡፡ በየዓመቱ በሚያካሂደው ጉባዔ አዳዲስ መሪ ሐሳቦችንና አጀንዳዎችን ይፋ በማድረግ ውይይት አድርጎ የሚለያዩት መሪዎች፣ የዚህ ዓመት ዋነኛ አጀንዳ የሆነው ‹‹የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ አፍሪካውያን›› ከመሞከር ያለፈ ይተገብራሉ ወይ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ ኅብረቱ የተለማቸውን አጀንዳዎች ለማስፈጸምም ሆነ አጠቃላይ የኅብረቱ የሥራ እንቅስቃሴ በአባል አገሮች መዋጮ የማይሸፈንና የአባልነት ክፍያቸውንም በወቅቱ የማይከፍሉ መሆናቸው የአኅጉሩ ትልሞች በምዕራባውያን፣ እንዲሁም በአሜሪካና በቻይና ምጽዋት ላይ እንዲወድቅ ስለማድረጉ፣ በዚህም የተነሳ አኅጉሩ በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውስጥ መውደቁን በርካቶች አስተያየት ሲሰጡበት የሚደመጥ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የአሁኑ መፅዋቾች የቀድሞ ቅኝ ገዥዎች በመሆናቸው የዓመቱ መሪ ቃል የመፈጸም ዕድልን ጠባብ ያደርገዋል እየተባለ ነው፡፡
የአደጉ አገሮች ጫና በበዛበት የኅብረቱ ጉዞ፣ ምዕራባውያኑ በአመዛኙ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አብዛኞቹ አፍሪካውያኑ ነፃ እስከ ወጡባቸው የ20ኛው ከፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ በነበራቸው አስከፊ የግኝ ቅዛት ታሪክ ላደረሱት ጥፋት ይቅርታ እንዲጠይቁና ካሳ እንዲከፍሉ ጥያቄውን በመሪዎች ደረጃ በይፋ ያቀረበው ኅብረቱን ጠንካራ ሥራ የሚጠብቀው መሆኑ ማሳያ ይደረጋል፡፡
አውሮፓውያን በቅኝ ግዛት ዘመን መጠነ ሰፊ ሀብት መዝብረው ወደ አውሮፓ ማጓጓዛቸው፣ አፍሪካውያንን በባርነት ቀንበር ሥር በማድረግ የባሪያ ንግድ በመፈጸማቸው፣ ላደረሱት ሰብዓዊና ታሪካዊ ቁስል፣ ቅኝ ገዥዎች ባሰመሩት ድንበር ምክንያት በአኅጉሩ ውስጥ የሚገኙ ጥቁር አፍሪካውያን ወንድማማቾች መካከል እየተፈጠረ ላለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ማካካሻ መጠየቅ የኅብረቱ ዋነኛ አጀንዳ መሆኑ፣ የኅብረቱን ቀጣይ ጂኦ ፖለቲካዊ ሚና ሊቀይር የሚችል መሆኑንም የሚጠቅሱ አሉ፡፡
በጉባዔው የመሪዎች መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ካደረጉት መሪዎች መካካል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ዓመቱ ከቆዩ የኢፍትሐዊነት ታሪካዊ ጠባሳዎች በመዳንና ለዕድገት ማነቆ ከሆኑ ቁስሎቻችን በመፈወስ ወደ ዕድገት ለመሻገር ጥሪ የሚደረግበት ጉባዔ ነው፤›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኅብረቱ የማካካሻ ጥያቄ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በባሪያ ንግድ እንደ ሸቀጥ በቅኝ ግዛት ውስጥ ጉልበታቸውን፣ ሀብታቸውንና አማራጮቻቸውን ለተበዘበዙ፣ ከፍትሐዊነት ለተገለሉ አፍሪካውያን የሚመጥንና የደረሰባቸውን ቁስል የሚፈውስ፣ እንዲሁም ክብራቸውን የሚመልስ ሰብዓዊ ምላሽ እንጂ የገንዝብ ዕርዳታ ወይም የበጎ አድራጎት ተግባር እየተጠየቀ አይደለም ብለዋል፡፡
በጉባዔው የተገኙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒ ጉተሬስ ባደረጉት ንግግር የቅኝ ግዛትና የባርነት ትሩፋቶች የካሳ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኙ የሚሰሙ ጥሪዎች እየጨመሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አፍሪካ የሁለት ግዙፍ ኢፍትሐዊነት ሰለባ መሆኗን አለም መዘንጋት የለበትም ብለዋል፡፡ ሁለቱ ሰለባዎች ባሏቸው የአትላንቲክ የባሪያ ንግድና አፍሪካ በቅኝ ገዥዎች ሥር በነበረችበት ወቅት በተመሠረተ ባለብዙ ወገን ሥርዓት ውስጥ መኖሯ እንደሆነ ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡
የትራንስ አትላንቲክ የባሪያ ንግድ በ16ኛው እና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መካከል የተከሰተ በኢሰብዓዊና አረመኔያዊነት በተሞላበት መንገድ የተፈጸመ የሰዎች ዝውውር ሲሆን፣ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በባርነት የተገዙ አፍሪካውያንን በመያዝ፣ በማጓጓዝና በመሸጥ በአሜሪካ አኅጉር በእርሻና በማዕድን ማውጫዎች ላይ እንዲሠሩ ስለማድረጋቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አኅጉሩ ከዚህ የቅኝ ገዥዎች ቀንበር ከወጣ ግማሽ ዓመታት አልፎታል፡፡
ታዲያ የተመድ ዋና ጸሐፊ በንግግራቸው የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ገዥዎች ፖለቲካ ነፃ ቢሆኑም፣ አገሮቹ አሁንም በመዋቅሮች ላይ ከተመሠረቱ ብዝበዛዎች ነፃ አለመሆናቸውንና ለበርካታ አሠርት ዓመታት ያለ ምንም ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ተቋማዊ ኢንቨስትመንት መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በኅብረቱ የመሪዎች የመክፈቻ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ባደረጉት 20 ደቂቃ የተሻገረ ንግግር፣ በአዳራሹ የሞሉትን ታዳሚዎችና መሪዎችን ጭምር ያስጨበጨበውን የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝነት ንግግር ያደረጉት የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አሞር ሞትሌ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሯ ንግግራችውን አጠናቀው ከመድረኩ እንደወረዱ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከቦታቸው ተነስተው አድናቆታቸውን ሲገልጹላቸው ታይተዋል፡፡
ከአፍሪካ አኅጉር ርቃ የምትገኘውና ሩብ ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ ያላትን በደቡብ ምሥራቅ ካሪቢያን የምትገኘውን ደሴት አገር ባርቤዶስ የሚያስተዳድሩት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፣ ከኅብረቱ ጉባዔ ጋር ከተገናኘው መሪ ቃል ላይ ጠንካራ ንግግር አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሯ በተደጋጋሚ የጥቁሮች ኩራት እያሉ እያሞካሹ የዓድዋን ድል አስታውሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሯ በቀድሞ ቅኝ ገዥዎች በተፈጸሙ በደሎች ምክንያት ካሳና ይቅርታ ሊኖር እንደሚገባ ሲገልጹ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን ታሪካዊ በደል ዕውቅና ለመስጠት መጀመሪያ እየጠየቅን ያለነው ይቅርታ እንድትጠይቁ ነው፡፡ የዓለም የወደፊት ሕልም ከአፍሪካውያን መረጋጋትና ከአፍሪካው ዳያስፖራዎች ሰላም መሆን ውጪ አይሳካም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ይሁን እንጂ ግብዝነት የተሞላው ዕሳቤ ይዘን በየትኛውም ሥፍራ መረጋጋትና ሰላምን ማምጣት አይቻልም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
‹‹ወደ የትኛውም ዓለም ለመጓዝ የሚሰጥን የትራንዚት ቪዛ ለማግኘት መለመንና ለምኖ ማግኘትም የደስታ ምንጫችን አይደለም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፣ ‹‹የአገሮች መሪዎች ማውራት አቁመን የወደፊት ዕጣ ፈንታችን መቆጣጠር የሚያስችለንን ድልድይ ለመገንባት የሚያስፈልገንን ሥራ መሥራትና መተግበር ያስፈልገናል፤›› ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከሙዚቃው፣ ከባህሉና ከምግቡ ባለፈ መሪዎች በአክራ ወይም ብሪጅታውን ተገኝተው መምከር ብቻ ሳይሆን ዜጎች ከየትኛውም አካባቢ ተነስተው በነፃ ሊገበያዩና ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
‹‹የዓለማችንን 40 በመቶ ማዕድን የያዘ አኅጉር እንዴት ብሎ የራሱን ሰላምና ዕጣ ፈንታ መወሰን ያቅተዋል? አንድ ሦስተኛ የሆነውን የዓለም ሕዝብ የሚይዘው አኅጉር እንዴት የሚፈልጋትን ዓለም መገንባትና ዕጣ ፈንታውን በሚወስኑ ተቋማት ላይ ድምፃችን እንዲሰማ ማድረግ እንዴት ያቅተዋል?›› ሲሉ ለጉባዔው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ይህ የአኅጉሩ ጉባዔ በየዓመቱ እየተገናኘ በአዳራሽ ውስጥ ንግግር አድርጎ ተገባብዞ ከመለያየት ባለፈ የተለየ አኅጉራዊ ፋይዳ ያላቸውን ተግባራት አላከናወነም የሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ይቀርብበታል፡፡ ኅብረቱ እ.ኤ.አ. በ2063 ለአኅጉሩ ዕድገት በሚል ካስቀመጣቸው ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች መካከል በአመዛኙ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መመሥረት ላይ ወደፊት አንድ ዕርምጃ የተራመደበት ጉዳይ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
ይሁን እንጂ በርካታ ዕቅዶቹን ለመፈጸም ያለበት የበጀት እጥረትና ከምዕራባውያኑ አገሮች ጥገኛ አለመሆኑ፣ በአኅጉሩ የሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ተጠያቂነት አለመኖር፣ ዘገምተኛ የሆነ የለውጥ ሒደት፣ ፆታዊ ተሳትፎዎች ውስን መሆን፣ እንዲሁም የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ዕድገት በእጅጉ ዝቅተኛ መሆን ኅብረቱን የሚያስወቅሱት ጉዳዮች ናቸው፡፡
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሠረቱት የነፃነት አባቶች በምሥረታውና ከምሥረታው ማግሥት ያስቀመጧቸው ዕቅዶችን ጨምሮ በአሁነኛው የአፍሪካ ኅብረት የወጡ በርካታ ዕቅዶችን ለማስፈጸም ያልቻለው የመሪዎቹ ጉባዔ፣ አሁን ቅኝ ገዥዎች በአኅጉሩ ላይ ላደረሱት ግፍ ይቅርታ እንዲጠይቁና ካሳ እንዲከፍሉ መጠየቁ አግባብ ቢሆንም እውነት አንድ ዕርምጃ ይሄድበታል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው የሚሉ አሉ፡፡
‹‹የዕርዮተ ዓለም ቅርምት በአፍሪካ›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ያሳተሙትና በኔዘርላንድ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰሩ ፍራንክ ግሪትስ እንደሚሉት፣ አፍሪካውያን ይህን የማካካሻ ጥያቄ ሲያቀርቡ ከአውሮፓውያኑ ለሚቀርበው ጥያቄ ምን ዓይነት ምላሽ ይፈለጋል የሚለውን ጉዳይ በተብራራ መንገድ መቅረብ አለበት ሲሉ ከአልጄዚራ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ገልጸዋል፡፡
ጥያቄው ሁሉን አቀፍና የተሟላ የፖሊሲ ማዕቀፍ ይፈልጋል የሚሉት ምሁሩ፣ የቅኝ ግዛት ታሪካ ጠባሳ ማካካሻ ጥያቄ አውሮፓውያኑ ምንም እንኳ የቅኝ ግዛት በደሎችን ለመቀበል ፈቃደኛ ቢመስሉም፣ ወደ ገንዘብ ተቀይሮ የሚደረግን የማካካሻ ጥያቄ ለመቀበል ፈቃደኝነቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መከናወን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአውሮፓ ምድር ከመጣው የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች መስፋፋት ጋር ጥያቄውን ለመቀበል ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑን፣ እ.ኤ.አ. በግንቦት 2024 በፖርቹጋል የተፈጠረውን ክስተት ማንሳት ይቻላል፡፡ ፖርቹጋል እ.ኤ.አ. ከ1526 እስከ 1867 ብቻ ወደ ስድስት ሚሊዮን አፍሪካውያን በባሪያ ንግድ ወደ ብራዚልና አውሮፓ ማጓጓዟን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በዚህ ከፍተኛ የባሪያ ንግድ ላይ የተሳተፈችው ፖርቹጋል ፕሬዚዳንት እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2024፣ አገራቸው በቅኝ ግዛት ዘመን ላደረሰችው ጥፋት የመፍትሔ ምላሽ መስጠት ትፈልጋለች የሚል ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የተፎካካሪና የቀኝ ዘመም ፓርቲ አባል ሪቤሎ ዲስኮ ፕሬዚዳንቱ ያደረጉት ንግግር በአገር ክህደት ሊያስጠይቃቸው ይገባል የሚል ቅስቀሳ ሲያሰሙ ተደምጠው ነበር፡፡ ነገር ግን የተፎካካሪ ፓርቲው ውንጀላ በፖርቹጋል ፓርላሜንት ውድቅ ተደርጓል፡፡ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ አፍሪካውያንን ለአውሮፓና ለሌሎች አገሮች ያጓጓዘችው ፖርቹጋል አንጎላን፣ ሞዛምቢክንና ብራዚልን በቅኝ ግዛት አስተዳድራለች፡፡
የአውሮፓ ሙዚየሞች ከአፍሪካ አኅጉር በተለይም ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች በተጓጓዙ ቅርሶች የተሞሉ ስለመሆናቸውና የአውሮፓ ኢንዱስትሪዎቸ የሚጠቀሟቸው ማዕድናት፣ ግብዓቶችና ሌሎች ጥሬ ዕቃዎች አሁን ድረስ ከአፍሪካ እየተጫኑ የሚሄዱ መሆናቸው ሁሌም የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በርካታ የአውሮፓና የአሜሪካ ፅንፍ የያዙ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች በአፍሪካውያን ላይ ከዚህ ቀደም በቅኝ ግዛት ዘመን ለደረሰው ግፍ ካሳ ቀርቶ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ሠርተው የሚኖሩ አፍሪካውያን አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ የሚያቀርቡት ጥያቄ እየበረታ መጥቷል፡፡
በዚህ እየሰፋ በመጣ የግንኙነት መንፈስ የአፍሪካ መሪዎችና ኅብረቱ የሚያቀርቡትን የማካካሻና የፍትሕ ጥያቄ ውጤታማ ለማድረግ፣ ኅብረቱ ግልጽ የሆኑ ፖሊሲዎች በመቅረፅ የዲፕሎማቲክ ሥራ ቢያከናውን እንደሚገባ የኔዘርላንድ ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ ያብራራሉ፡፡
ለአፍሪካውያንና ዘርዓ አፍሪካውያን የማካካሻ ፍትሕ ያስፈልጋል የሚለው ዕሳቤ እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩን በተለያየ መንገድ ሲያቀርቡት ነበር፡፡ በትራንስ አትላንቲክ የባሪያ ንግድ መስመር ተፈጽሟል ለሚባለው የ30 ሚሊዮን ባሪያዎች ንግድ አገሮች በይፋ ይቅርታ እንዲያቀርቡና ማካካሻ እንዲከፍሉ ጥሪ ማድረግ ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡
የቅኝ ግዛት ዘመን የታሪክ ጠባሳ አሁን በተለያዩ የዓለም አገሮች የሚገኙ አፍሪካውያንን ለተጨማሪ የኢፍትሐዊነት ድርጊቶች፣ በጥቁር አፍሪካውያን ላይ የሚታይ ጥላቻ በዘርና በቀለም ለሚደርሱ ግፎች ተጠቂ እየዳረጋቸው መሆኑን የተመድ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በዚህ ሁሉ መሰናክል ውስጥ የቀረበው የኅብረቱ ዓመታዊ አጀንዳ ዕውን የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ በቀጣይ በመሪዎች በሚደረጉ የፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች የሚወሰን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ለአምስት ቀናት በተካሄደው ዓመታዊ ጉባዔ ለስምንት ዓመታት የአፍሪካ ኅብረትን ለሁለት የሥልጣን ዘመን ኮሚሽኑን የመሩትን ሙሳ ፋቂ ማሃማት፣ በምክትል ሊቀመንበርነት ሲያገለግሉ የነበሩትና የአራት ዓመት የሥልጣን ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን ሞንኪ ሰንዛባጋንዋ (ዶ/ር) በአዲስ ተመራጮች ተክቷል፡፡
ከወራት አስቀድሞ የኮሚሽነርነቱን ቦታ ለማግኘት ከፍተኛ ትንንቅ የተሞላበት ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩት የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህመድ ዓሊ የሱፍ፣ የኬንያ ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ፣ የማዳጋስካሩ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራንድራያ ማንድራቶናና የሞሪሽየስ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አኒል ኩማር ሲንግ ሲሆኑ በመጨረሻም የጂቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሸናፊ ሆነዋል፡፡
በተመሳሳይ የምክትልነት ቦታውን ለመያዝ ከተወዳደሩት ሁለት የአልጄሪያ፣ አንድ የሞሮኮ፣ ሁለት የግብፅ፣ አንድ የሊቢያ እጩዎች በኢትዮጵያ የአልጄሪያ አምባሳደር የነበሩት ሰሊማ ማላክ አሸንፈዋል፡፡ በዓመታዊ ጉባዔው በተጨማሪ ሌሎች የስድስት ኮሚሽነሮችን ሹመት ፀድቋል፡፡