February 20, 2025

በቤተልሔም ሠለሞን
በአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከሁለት ሳምንት በፊት የተቀሰቀሰ የእሳት አደጋ፤ እስከዛሬ ሐሙስ የካቲት 13፤ 2017 ድረስ በቁጥጥር ስር አለመዋሉን የአርሲ ዞን እና የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ለእሳት ቃጠሎው መከሰት መንስኤ ናቸው በሚል የተጠረጠሩ 30 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም የአርሲ ዞን አስታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ስድስት ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ አንዱ የሆነው የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙት የምኒልክ ድኩላ፣ የደጋ አጋዘን፣ ቀይ ቀበሮ እንዲሁም የሌሎች እንስሳት መኖሪያ ነው። በ2003 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የተመዘገበው ፓርኩ፤ 84,100 ሄክታር የሚሸፍን ቦታን የሚያካልል ነው።
በፓርኩ ይዞታ ውስጥ በሚገኝ ጢቾ በተባለ ወረዳ ከሳምንት በፊት የተከሰተው የእሳት አደጋ፤ በአሁኑ ወቅት በ11 ወረዳዎች ላይ መስፋፋቱን የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ቲፎ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በሰደድ እሳቱ “በከፍተኛ ሁኔታ” ጉዳት የደረሰበት ጭላሎ ጋለማ የተሰኘው የፓርኩ “ብሎክ” እንደሆነም ኃላፊው አስረድተዋል።

የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጭላሎ ጋለማ፣ ካካ፣ ሆንቆሎ እና ዴራ ዲልፈከር በተባሉ አራት “ብሎኮች” የተከፋፈለ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ሰፊውን ቦታ የሚይዘው ጭላሎ ጋለማ 70,486 ሄክታር ስፋት አለው። የአርሲ ዞን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እድሪስ ሆርዶፋ፤ የእሳት አደጋው ለመቀስቀሱ ምክንያት የሆኑት የአካባቢው እረኞች መሆናቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
እረኞቹ የበጋው ዝናብ ከዘነበ በኋላ “ጥሩ ሳር እንዲያበቅል” በሚል፤ በመሬት ላይ ያለውን የደረቀ ሳር በማቃጠላቸው የእሳት አደጋው መከሰቱን አቶ እድሪስ አመልክተዋል። የእሳት አደጋው በፓርኩ ውስጥ እንዲከሰት አድርገዋል የተባሉ 30 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ኃላፊው ገልጸዋል።
በአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተውን እሳት ለማጥፋት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የጸጥታ አካላት እና የመንግስት ሰራተኞች ርብርብ እያደረጉ ቢሆንም፤ ቃጠሎውን እስካሁን መቆጣጠር እንዳልተቻለ ሁለቱም ኃላፊዎች ገልጸዋል። አቶ እድሪስ በፓርኩ ያለውን ሁኔታ “አስቸጋሪ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፤ አቶ መሀመድ በበኩላቸው እሳቱን ለመቆጣጠር አዳጋች ያደረገው በአካባቢው ያለው የአየር ሁኔታ እንደሆነ አመልክተዋል።

“እሳቱ መሬት ውስጥ ገብቶ የመቆየት ባህሪ ስላለው እየቆየ ንፋሱ ያስነሳዋል” የሚሉት አቶ መሀመድ፤ የአየር ሁኔታው ሲቀዘቅዝ እንደሚዳፈን ሆኖም ቀትር ላይ መልሶ እንደሚቀጣጠል አብራርተዋል። በአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከጥር 9 እስከ ጥር 22፤ 2017 የቆየ ተመሳሳይ የእሳት ቃጠሎ ተከስቶ እንደነበር የገለጹት የፓርኩ ኃላፊ፤ በዚህ ጊዜ ተዳፍኖ የነበረ እሳት ከሳምንት በኋላ መልሶ መቀስቀሱን አክለዋል።
በመጀመሪያ ዙር ሰደድ እሳት ከ200 ሄክታር በላይ መቃጠሉንም አቶ መሀመድ ተናግረዋል። የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተለያዩ ዓመታት ተመሳሳይ የእሳት አደጋዎች ገጥሞት እንደሚያውቅ ያስታወሱት የፓርኩ ኃላፊ፤ በ2013 ዓ.ም የተከሰተው እና 4,500 ሄክታር የተቃጠለበት “ከሁሉም ከባዱ” መሆኑን ገልጸዋል።
የፓርኩ ኃላፊ የአሁኑ የእሳት ቃጠሎ ከሌሎች ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር “የከበደ” መሆኑን ቢጠቅሱም፤ በአደጋው በፓርኩ ውስጥ ያሉ እንስሳት “እስካሁን ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸውም” ብለዋል። የዱር እንስሳቱ “ስለሚሮጡ ያመልጣሉ ብለን እንገምታለን። እንዳጋጣሚ አፍኗቸው ካልሞቱ ያመልጣሉ። ሌሎች ትናንሽ የዱር እንስሳት ሊቃጠሉ ይችላሉ” ሲሉ በአነስተኛ እንስሳት ላይ ጉዳት ሊከሰት እንደሚችል ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሯ” አሚናት ሙሀመድ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጋለች]