
ከ 5 ሰአት በፊት
በእስራኤል ዋና ከተማ ቴል አቪቭ ደቡባዊ ክፍል ባት ያም፤ ፖሊስ የሽብር ጥቃት እንደሆኑ የጠረጠራቸው ሶስት የአውቶብስ ፍንዳታዎች ማጋጠማቸው ተገለጸ።
በሁለት አውቶብሶች ላይ የተገጠሙ መሳሪያዎች ሳይፈነዱ መቅረታቸውን ያስታወቀው የሀገሪቱ ፖሊስ፤ “ትልቅ ቁጥር ያለው የፖሊስ ኃይል በቦታው ተገኝቶ ተጠርጣሪዎችን እያሰሰ” መሆኑን ተናግሯል።
የእስራኤል የትራንስፖርት ሚኒስትር ሚሪ ሪጌቭ፤ ፈንጂዎች ላይ አሰሳ ለማድረግ እንዲቻል በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም አውቶብሶች፣ ባቡር እና ቀላል ባቡሮች እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ማድረጋቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች እየተዘዋወረ ያለ አንድ ቪዲዮ በማቆሚያ ስፍራ የነበረ አንድ አውቶብስ በእሳት ተያይዞ እና ከበላዩ ጭስ ሲወጣ ያሳያል። እስካሁን ድረስ በጥቃቶቹ የደረሰ ጉዳት ሪፖርት አለመደረጉን ፖሊስ አስታውቋል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ አርየህ ዶሮን ፖሊሶች አሁንም ቴልአቪቭ ውስጥ ሌሎች ቦምቦችን ለማግኘት እየሞከሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ “ጉዳዩ አሁንም በሂደት ላይ ያለ” መሆኑን ተናግረዋል።
- ህይወት ባልጠፋበት የቶሮንቶ አውሮፕላን አደጋ ለእያንዳንዱ ተሳፋሪ 30 ሺህ ዶላር ሊሰጥ ነው20 የካቲት 2025
- ዘለንስኪ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምላሽ ወሳኝ ማዕድን እንዲሰጡ አሜሪካ ጠየቀችከ 5 ሰአት በፊት
- ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ሰሜን ሸዋ ውስጥ የተደጋገመው የአመራሮች ግድያ20 የካቲት 2025
“ኃይሎቻችን አሁንም በአካባቢው ላይ ቅኝት እያደረጉ ነው” ሲሉ ቻናል 12 ለተባው መገናኛ ብዙኃን የተናገሩት ቃል አቀባዩ፤ ህዝቡ “አጠራጣሪ የሆኑ ቦርሳዎች ወይም እቃዎችን” በንቃት እንዲከታተል መክረዋል።
“አሸባሪዎቹ [የቦምቡን መፈንጃ] ጊዜ በተሳሳተ ሰዓት ላይ አስቀምጠውት ከሆነ እድለኛ ልንሆን እንችላለን። ይህ ነው ብሎ ለመናገር ግን ጊዜው ገና ነው” ብለዋል።
የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ አምስት ኪሎግራም የሚመዝን አንድ ፈንጂ መሳሪያ “በቀል ከቱልካረም” የሚል ጽሁፍን ይዞ ነበር። በፈንጂው ላይ የተጠቀሰው “ቱልካረም” የእስራኤል ሠራዊት በቅርቡ በዌስት ባንክ ያካሄደውን የጸረ ሽብር ብሎ የጠራውን ጥቃት የሚያመለክት ነው።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ፤ በባት ያም ለተፈጠረውን ፍንዳታ በሰጡት ምላሽ ሠራዊቱ፤ በዌስት ባንክ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚያደርገውን ጥቃት “አጠናክሮ እንዲጨምር” ማዘዛቸውን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤኒያሚን ኔታንያሁ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንደተሰጣቸውም ተገልጿል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ሚሪ ሪጌቭ በዚህ ክስተት ምክንያት በሞሮኮ የነበራቸውን ጉዞ በማቋረጥ ወደ እስራኤል እንደሚመለሱ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።