አዲሱ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ካሽ ፓቴል

ከ 3 ሰአት በፊት

ረጅም ጊዜ ጥቃት ሲያደርሱበት የቆዩትን የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) በዳይሬክተርነት እንዲመሩ በሀገሪቱ ሴኔት ሹመታቸው የጸደቀላቸው ካሽ ፓቴል፤ ህግ አስከባሪ ተቋሙን “መልሰው ለመገንባት” ቃል ገቡ።

የሀገሪቱ የላይኛው ምክር ቤት በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእጩነት የቀረቡትን አዲሱ ዳይሬክተር ሹመት ያጸደቀው 51 ለ49 በሆነ ጠባብ የድምጽ ብልጫ ነው።

ሁለት ሪፐብሊካን የምክር ቤቱ አባላት ሹመቱን ተቃውመው ድምጽ ሰጥተዋል።

ዲሞክራቶች፤ እጩው ተቋሙን ለመምራት የሚሾሙ ከሆነ በትራምፕ ጠላቶች ላይ የበቀል እርምጃ ይወስዳሉ በማለት አስጠንቅዋል። እጩው በበኩላቸው፤ ፖለቲካዊ በቀሎችን የመውሰድ እቅድ አላቸው መባሉን አስተባብለዋል።

የ44 ዓመቱ ፓቴል ሹመታቸው በጸደቀበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ “ከጀርባ ሆነው መንግስትን የሚያሾሩ (ዲፕ ስቴት)” ጠላቶች ዝርዝር አላቸው መባሉንም ውድቅ አድርገዋል። ከዚህ ቀደም ትራምፕ ላይ ምርመራ ያደረጉ የህግ አስከባሪ ባለስልጣናትን ላይ ተጠቅመት የነበረውን “ወንጀለኛ ወንበዴዎች” የሚል አከራካሪ ገለጻቸውንም አደባብሰዋል።

ፓቴል ህግ አስከባሪ ተቋሙን ለመምራት የተሾሙት ሴኔቱ አባል የሆኑ ዲሞክራቶች በሙሉ ተቃውመው ነው። ሪፐብሊካን የሆኑት የሜይን ግዛት ተወካይ ሱዛን ኮሊንስ እና የአላክሳ ግዛቷ ሪፐብሊካ ተወካይ ሊሳ ሙርኮውስኪም ተቃውመው ድምጽ ሰጥተዋል።

አዲሱ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር፤ ትራምፕ ወደ ስልጣኑ ከመጡ ወዲህ ሹመታቸው የጸደቀላቸው 18ተኛ የካቢኔ ባለስልጣን ናቸው።

ፓቴል ሹመታቸው ከጸደቀላቸው በኋላ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “የፌደራል ምርመራ ቢሮ ዘጠነኛ ዳይሬክተር ሆኞ በመሾሜ ክብር ተሰምቶኛል” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

“እንደ ዳይሬክተር ተልዕኮዬ ግልጽ ነው፤ ጥሩ ፖሊሶች፣ ፖሊሶች እንዲሆኑ እና የኤፍቢአይን እምነት መልሶ መገንባት” ብለዋል።

“የአሜሪካ ህዝብ ሊኮራበት የሚችልን ኤፍቢአይ መልሰን እንገነባለን” ሲሉም አክለዋል።

ፓቴል የተቋሙን ስልጣን የተቆናጠጡት፤ የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር የተወሰኑ ከፍተኛ አመራሮቹን ካባረረ እንዲሁም በአውሮፓውያኑ 2021 የትራምፕ ደጋፊዎች ያስነሱትን የካፒቶል ሂል አመጽ የመረመሩ ወኪሎች ስም እንዲሰጠው እየጠየቀ ባለበት ሁኔታ ነው።

በዋሽንግተን ዲሲ ለዓመታዊው የወግ አጥባቂዎች ‘የኮንዘርቫቲቭ ፖለቲካል አክሽን ኮንፈረንስ’ ተሰብስበው የነበሩት ሪፐብሊካኖች የፓቴልን የሹመት ዜና የተቀበሉት በጭብጨባ ነው።

የፍሎሪዳ ተወካይ የሆኑት ሪክ ስኮት በጉባኤ መድረክ ላይ ቆመው “ስለ ካሽ ፓቴል የምናስበው ምንድነው?” በማለት ለታዳሚዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ በሞቀ ጭብጨባ ተመልሷል።

ለብዙዎቹ ሪፐብሊካኖች ካሽ ፓቴል ማለት እስካሁን የዘገየውን የሀገሪቱን ከፍተኛ ህግ አስከባሪ ተቋም ከስሩ የመነቅነቅ ስራ የሚያከናውን ሰው ነው። ትራምፕ እና ሌሎች ሪፐብሊካኖች፤ ኤፍቢአይ ወግ አጥባቂዎችን ማጥቂያ ሆኗል በማለት ይከስሳሉ።

ዲሞክራቶች በበኩላቸው ፓቴል በህግ ማስከበር ያለው ልምድ ትንሽ የሆነ ቀኝ አክራሪ የሴራ ተንታኝ ነው ይላሉ። ተቋሙን በነጻነት ለመምራት ከገባው ቃል በላይ ለትራምፕ ያለውን ታማኝነት የሚያስቀድም መሆኑንም ይናገራሉ።

ማርቲን ሃይንሪክ የተባሉት የሴኔቱ አባል በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ “[የፓቴል] ደካማ ማመዛዘን ችሎታ እና የልምድ ማነስ፤ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ሆኖ የአሜሪካውያንን ደህንነት ለማስጠበቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ እንዳይሆን ያደርገዋል” ብለዋል።

ፓቴል ተቋሙን የመምራት ሹመት ያገኙት እ.አ.አ በ2017 በትራምፕ የተሾሙትን ክርስቶፈር ሬይን በመተካት ነው። ሬይ ባለፈው ወር ከትራምፕ ቃለ መሃላ አስቀድመው ከኃላፊነት የለቀቁት አዲሱ ፕሬዝዳንት እንደሚያባርሯቸው ከጠቆሙ በኋላ ነው።