
ከ 5 ሰአት በፊት
ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ወደ ድርድሩ ጠረጴዛ ተመልሰው አሜሪካ የዩክሬንን ወሳኝ ማዕድን በምታገኝበት ዙሪያ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የዋይት ሃውስ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልትዝ አስታወቁ።
በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ዘለንስኪ አገራቸው ብርቅዬ የሆኑትን ማዕድናትን ድርሻ አሜሪካ እንድትሰጣት ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህ የማዕድን ስምምነት ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ባደረገችው ፍልሚያ አሜሪካ ያደረገችላትን የእርዳታ መጠን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ሐሙስ ዕለት በዋይት ሐውስ የተሰጠው መግለጫ በኪዬቭ በፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በዩክሬን የአሜሪካ ዋና መልዕክተኛ ኬት ክሎግ መካከል የተደረገውን ውይይት ጥላ አጠልሽቶበታል።
አማካሪው እንዳሉት ዘለንስኪ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ላይ “ተቀባይነት የሌለው ዘለፋ ሰንዝረዋል” ሲሉ የወነጀሏቸው ሲሆን ይህም ሁኔታ ዋይት ሃውስን በእጅጉ ያበሳጨ ነው ብሎታል።
ዩክሬን ሊቲኒየም እና ቲታኒየምን ጨምሮ ወሳኝ የሆኑ ማዕድናትን እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው የድንጋይ ከሰል፣ ጋዝ፣ ዘይት እና የዩራኒየም ክምችት ባለቤት ናት።
አገሪቷ በበሊዮኖች ዶላር የሚያወጣ የማዕድኖች አቅርቦት አላት። ዋልትዝ ዩክሬን ያላትን ብርቅዬ ማዕድናት አሜሪካ ማግኘቷ ለእርዳታዋ ምላሽ ወይም ከዚህ ቀደም ለሰጠችው ድጋፍ እንደ ማካካሻ እንደሚቆጠር እንደሆነ ጠቁመዋል።
“ለዩክሬናውያን ድንቅ እና ታሪካዊ እድል አቅርበናል” ያሉት አማካሪው አክለውም “ዘላቂ እና ዩክሬን ተስፋ የምታደርገውን መልካም የደህንነት ዋስትና ይሰጣታል” ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው “አገራችንን መሸጥ አልችልም” በማለት የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል።
- ሳዑዲ አረቢያ በተደረገው የአሜሪካ እና ሩሲያ የሰላም ንግግር ልዑካኑ እነ ማን ናቸው?ከ 6 ሰአት በፊት
- ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ሰሜን ሸዋ ውስጥ የተደጋገመው የአመራሮች ግድያ20 የካቲት 2025
- ህይወት ባልጠፋበት የቶሮንቶ አውሮፕላን አደጋ ለእያንዳንዱ ተሳፋሪ 30 ሺህ ዶላር ሊሰጥ ነው20 የካቲት 2025
የዋልትዝ አስተያየት የተሰማው ዘለንስኪ ከአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ክሎግ ጋር በኪዬቭ ያደረጉትን ውይይት አጠናቀው ብዙም ሳይቆዩ የዩክሬኑ መሪ በአገራቸው ያለውን ጦርነት ለማስቆም ከአሜሪካ ጋር “የኢንቨስትመንት እና የደህንነት ስምምነት” ለማድረግ መዘጋጀታቸውን እንዳስታወቁ ነው።
ከአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ጋር ያደረጉትን ውይይት ዘለንስኪ “ፍሬያማ” ብለው አወድሰውት የነበረ ቢሆንም ከአሜሪካ ባለስልጣናት የሚሰማው አስተያየት ይህንን አያንጸባርቅም።
የዶናልድ ትራምፕ ቡድን ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሞስኮ ጋር በቀጥታ መገናኘታቸውን የቀጠሉ ሲሆን ልዩ መልዕክተኛው እና ጡረተኛው ጄነራል ወደ ኪየቭ የመጡት “ለማዳመጥ” እንደሆነ ተናግረዋል።
ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ጋር ስላደረጉት ውይይት በይፋ መግለጫ እንደማይሰጡ ታውቋል። በመጨረሻዋም ደቂቃ ሊሰጡት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰረዝ ተደርጓል።
ቢቢሲ ይህ ውሳኔ የአሜሪካ መሆኑን የተረዳ ሲሆን የዩክሬን ምንጮች በበኩላቸው ኬሎግ በዋይት ሃውስ “እንዲገለሉ” ተደርገዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
የዩክሬን ባለስልጣናት መልዕክቶቻቸውን ወደ ዋሽንግተን ለማስተላለፍ በልዩ መልዕክተኛው ላይ ተስፋ በመጣል ከኬሎግ ጋር የተደረገው ውይይት ለኪዬቭ ታላቅ ጠቀሜታ እንደነበረው ተገልጿል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ስለ ጦር ሜዳ ሁኔታ፣ የጦር እስረኞችን እንዴት እንደሚመለሱ እንዲሁም ስለ ደህንነት ዋስትናዎች መወያየታቸውን በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።