
ከ 3 ሰአት በፊት
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አርብ፣ የካቲት 14/ 2017 ዓ.ም ይፋ ያደረገው አዲሱ ፓስፖርት የጊዜ ገደብ ወደ 10 ዓመት ከፍ ማለቱን የአገልግሎቱ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ማስተዋል ገዳ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ዳይሬክተሯ ከዚህ በኋላ ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ የሆኑ ዜጎች የማብቂያ ጊዜው 10 ዓመት የሆነውን አዲሱን ፓስፖርት እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
ሆኖም ከ25 ዓመት በታች ላሉ “የተለመደው” የ5 ዓመት ጊዜ ቆይታ ያለው ፓስፖርት ይሰጣቸዋል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የቆየው የኢትዮጵያን ፓስፖርት የሚተካ አዲስ ፓስፖርት አርብ፣ የካቲት 14/2017 ይፋ የማድረጊያ መርኃ ግብር በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
አዲሱ ፓስፖርት የግለሰቦችን ባዮሜትሪክ መረጃ ጨምሮ የጣት አሻራዎችን፣ የፊት ለይቶ ማወቂያ እና የኤሌክትሮኒክስ ቺፕስ ያካተተ ነው።
በተጨማሪም ሀሰተኛ መረጃዎችን እና ማጭበርበርን ለመከላከል የሚያስችል የላቀ የደህንነት ባህሪያትን ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ ፓስፖርት የሚይዛቸው ገጾች የኢትዮጵያን ቅርስ እና መልክዓ ምድሮች አካቷል። ከነዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ ብርቅዬ እንስሳ የሆነው ዋልያ፣የኢትዮጵያ ካርታ፣አደይ አበባ እንዲሁም የግዕዝ ቁጥሮች ይታዩበታል።
አዲሱ የኢትዮጵያ ፓስፖርት በቀለም እና ንድፍ ከዚህ ቀደም ከነበረው እንደሚለይ የተገለጸ ሲሆን ዛሬ የሚቀየረው ፓስፖርት ከፍ ያለ የጥራት ደረጃ እንዳለውም ተዘግቧል።
አዲሱ ፓስፖርት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በቶፓን ሴኪዩሪቲ ኢትዮጵያ አክሲዮን ማህበር አማካኝነት በሀገር ውስጥ መመረቱ ይፋ በተደረገበት መርኃ ግብር ተነግሯል።፡
ባለፈው ጥቅምት ወር የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት መሥሪያ ቤታቸው የፓስፖርት የጊዜ ገደብ ወደ 10 ዓመት ከፍ እንደሚደረግ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረው ነበር።
ዋና ዳይሬክተሯ በዚህ መግለጫቸው የገንዘብን ብክነት ለመቀነስ ይህ እርምጃ መወሰዱን በወቅቱ አስረድተው ነበር።

- “ቁጥር 7 ኢትዮጵያዊነት የሚበየንበት ክፍል ነው” – ፓስፖርት ለማግኘት የሚንገላቱ የትግራይ ተወላጆች19 ነሐሴ 2024
- ፓስፖርት በ‘ኦንላይን’ እንዴት ማደስ/ማውጣት ይቻላል?28 ጥቅምት 2020
- የኢትዮጵያ ፓስፖርት ዋጋ ከሌሎች አገራት ጋር እንዴት ይነጻጸራል?7 ነሐሴ 2024
ለሌሎች ሀገራት ዜጎች የሚሰጠው የመኖሪያ ፈቃድ እና ቪዛም ከፓስፖርቱ ጋር አብሮ ይቀየራል ተብሏል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በፓስፖርት ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ቀደም ሲል 2 ሺህ ብር ይጠየቅበት የነበረው የአዲስ ፓስፖርት ክፍያ በአዲሱ የዋጋ ማሻሻያ 5 ሺህ ብር (50 የአሜሪካ ዶላር) መሆኑን አስታውቋል።
በአስቸኳይ አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ይጠየቅ የነበረው 5 ሺህ ብር ደግሞ ወደ 20 ሺህ ብር (200 ዶላር ገደማ) ከፍ ማለቱን አገልግሎቱ አስታውቋል።
እንደ አገልግሎቱ መረጃ ከሆነ ፓስፖርቱ ዕድሜ ኖሮት እርማት ለማግኘት ለፈጣን አገልግሎት 40 ሺህ 500 ብር ያስከፍላል።
በተመሳሳይ ለጠፋ ፓስፖርት በሁለት ቀን እርማት ለማድረግ የአገልግሎት እስከ 40 ሺህ 500 ብር (450 ዶላር) እንደሚያስከፍል አስታውቋል።
በውጭ አገር ሆነው መደበኛ ፓስፖርት በኤምባሲ በመደበኛ ጊዜ የሚጠይቁ ኢትዮጵያዊያን 200 ዶላር ይከፍላሉ። በአስቸኳይ (በ15 ቀናት) ለማግኘት ደግሞ 350 ዶላር ይጠየቃል።
ዛሬ ይፋ ይደረጋል የተባለው ፓስፖርት በሀገር ውስጥ የሚታተም በመሆኑ በውጪ ምንዛሬ ሲደረግ የነበረውን የህትመት ወጪ ይቀንሰዋል ተብሏል።
