
ከ 3 ሰአት በፊት
አሜሪካ አልሳተፍበትም ያለችው የቡድን 20 አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባዔ በደቡብ አፍሪካ ተከፈተ።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ለቡድን 20 አባል አገራት ገራት ሚኒስትሮች እንደተናገሩት በዓለማችን እየተከሰቱ ያሉ ቀውሶችን ለመፍታት አለም አቀፍ ህጎች እንዲሁም የበርካታ አገራት ትብብር መሰረታዊ ነው ብለዋል።
ራማፎሳ ይህንን ያሉት የትራምፕ አስተዳደር “ቅድሚያ ለአሜሪካ” የሚለውን ፖሊሲ ላይ ስጋቶች እየተነሱ ባሉበት ወቅት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጉባኤውን ውድቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።
ከማርኮ ሩቢዮ በተጨማሪ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት በበኩላቸው በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሔደው የቡድን 20 አባል አገራት የገንዘብ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ አልገኝም ብለዋል።
ሩቢዮ በጉባዔው ላይ ላለመገኘታቸው ምክንያት “ጸረ-አሜሪካዊነትን አልቀበልም” በማለት ሲሆን ስኮት ቤሴንት በበኩላቸው በዋሽንግተን በሌሎች ጉዳዮች እንደሚጠመዱ ገልጸዋል።
ደቡብ አፍሪካ የቡድን 20 አባል አገራት ጉባኤን በመምራት የመጀመሪያ አፍሪካዊት አገር ስትሆን በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ጥቅም ለማስጠበቅ ከአለማችን የበለጸጉ አገራት ጋር ለመነጋገር ይህ ጉባኤ እድልን እንደሚከፍት ተስፋ አድርጋለች።
- ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ሰሜን ሸዋ ውስጥ የተደጋገመው የአመራሮች ግድያ20 የካቲት 2025
- ዘለንስኪ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምላሽ ወሳኝ ማዕድን እንዲሰጡ አሜሪካ ጠየቀችከ 5 ሰአት በፊት
- በእስራኤል የሽብር ጥቃትነት የተጠረጠሩ ሶስት ፍንዳታዎች መከሰታቸውን ፖሊስ አስታወቀከ 5 ሰአት በፊት
ቡድን 20 የተሰኘው 19 አገራትን፣ የአፍሪካ ህብረትን እና የአውሮፓ ህብረትን ያቀፈ ሲሆን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የአለም የምጣኔ ኃብት እንዲሁም የዓለም ህዝብ ሁለት ሶስተኛውን የሚይዝ ነው።
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
በጆሃንስበርግ እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ላይ የቻይና፣ የፈረንሳይ እና የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተሳታፊ ናቸው። በደቡብ አፍሪካ የአሜሪካ ኤምባሲ የሚሲዮን ምክትል ኃላፊ በዚሁ ጉባኤ ላይ ይገኛሉ።
ራማፎሳ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት “ቀድሞውን ትስስሩ የላላ በሆነው አለም እየጨመረ በመጣው አለመቻቻል፣ ግጭቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጨማሪ አደጋ ሆነዋል” ብለዋል።
“ሆኖም የቡድን 20 አባል አገራትን ጨምሮ ለነዚህ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች እንዴት ምላሽ መሰጠት እንዳለበት በታላላቅ ኃያላን አገራት መካከል ስምምነት የለም” ሲሉ ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ተናግረዋል።
“የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር፣ የበርካታ አገራት ትብብር እንዲሁም አለም አቀፍ ህጎች የጥረቶቻችን ሁሉ ማዕከል ሆነው መቀጠላቸው ወሳኝነት አለው” ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ የቡድን 20 አባል አገራት ፕሬዚዳንትነት እስከ መጪው ህዳር የምትይዝ ሲሆን ከዚያም ለአሜሪካ እንደምታስረክባት ይጠበቃል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጥር ወር ስልጣን ከያዙ በኋላ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ በፕሬዚዳንት ዘመንዋ ምን ያህል ውጤት ልታመጣለች የሚለውን ጥያቄ አስነስቷል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ያጸደቀችው የመሬት ፖሊሲ በተወሰኑ “ማህበሰረሰቦች” ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ለአገሪቱ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያቋርጡ መዛታቸው ይታወሳል።
ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ የአፓርታድ ስርዓት ከ30 ዓመታት በኋላ ብትላቀቅም አሁንም አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬቶች አነስተኛ በሆኑት ነጮች እንደተያዘ ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የመሬት ባለቤትነት በአገሪቱ አከራካሪ እና አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ የቆየ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የጸደቀው የመሬት ፖሊሲ ይህንን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ያለመ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው በሚል በአለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የከሰሰቻት ሲሆን ይህም ጉዳይ በጦር መሳሪያ ጭምር እየደገፈቻት ያለችውን አሜሪካን አስቀይሟል።