
February 23, 2025
https://www.ethiopianreporter.com/138630
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር የሦስተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ማስጀመርያ መርሐ ግብር
- ችግሩ ከውጭ በሚገቡ ባንኮች በዘላቂነት ይፈታል ተብሏል
በኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የፋይናንስ ፍላጎት ከባንኮች አቅርቦት በላይ መሆኑን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የዘርፉን የፋይናንስና ሌሎች ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የልማት ባንክ፣ የንግድ ባንክ፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴርን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ኃይልና አገልግሎት ተቋማት የሚሳተፉበት ካውንስል መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡
የፋይናንስ ተቋማት ለዘርፉ የሚያደርጉትን የፋይናንስ አቅርቦት በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን ካውንስሉ ማየቱን አስረድተዋል፡፡ ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማነቆ የሆነባቸው ፍላጎታቸውና የፋይናንስ ተቋማቱ አቅርቦት አለመመጣጠን እንደሆነ ገልጸው፣ ችግሩን በተጀመረው አገራዊ ሪፎርም ለመፍታት መታቀዱን አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡
በአገር ደረጃ በተጀመረው የፋይናንስ ሪፎርም አማካይነት በካፒታል ገበያ፣ እንዲሁም የውጭ ባንኮች አገር ውስጥ ሲገቡ ያሉትን ዕድሎች በመጠቀም የዘርፉ የፋይናንስ ችግር በዘላቂነት ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው አክለዋል፡፡
በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የሚነሳው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ የሁሉንም ኢንዱስትሪዎች ችግር ሙሉ በሙሉ ባይፈታም ካውንስሉ በሄደበት ርቀት ልክ ምክንያት ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ በዘርፉ ችግር ተብለው ከተነሱት መካከል የጉምሩክ አሠራርን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ፣ በቅርቡ የወጣው መመርያ የካውንስሉ ውጤት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዘርፉ ባሉ ተዋንያን የሚነሳው አንዱ ማነቆ ከውጭ ምርቶችን ሲያስገቡ በአንደር (ኦቨር ኢንቮይስ) ምክንያት ሁለቱም ወገኖች መግባባት እንደሚኖር አስታውሰዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል እስከ ታችኛው እርከን ድረስ በወረደው አቅጣጫ መሠረት፣ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ ለሚያስገቡት ዕቃ በሚያቀርቡት ኢንቮይስ እንዲቀረጡ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ካውንስሉ እየሠራቸው ያሉ ተግባራት እንዳለ ጠቁመው፣ ነገር ግን ከተቋቋመ ስድስት ወራት የዘለለ ዕድሜ ስለሌለው ሁሉንም የዘርፉ ችግሮች በአንዴ መፍታት አይችልም ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የተወከሉት አቶ ዮናስ መኩሪያ በበኩላቸው፣ ለዘርፉ የቀረበው የፋይናንስ አቅርቦት ኢትዮጵያ ታምርት ከመጀመሩ በፊት አሥር በመቶ ብቻ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም. ደግሞ ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ያቀረቡት ወደ 16.3 በመቶ መድረሱን ገልጸው፣ ለአሥር ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው ኢትዮጵያ ታምርት ሲጠናቀቅ 24 በመቶ የፋይናንስ አቅርቦት ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚያደርገውን ድጋፍ ያደነቁ የማሽነሪ አምራች መሆናቸውን የገለጹ አንድ ግለሰብ፣ ሚኒስቴሩ ድጋፍ ያድርግ እንጂ ባለድርሻ አካላት ተብለው የተገለጹት ተቋማት (ባንኮች፣ ጉምሩክ፣ ገቢዎች) የሚያደርጉትን ድጋፍ በተጨባጭ አይታይም ብለዋል፡፡
በምሳሌ ሲያስረዱ የፋይናንስ አቅርቦትን በተመለከተ በመንግሥት ለዘርፉ ተሰጠ ተብለው በሚነገሩ ቁጥሮች ላይ የግሉ ዘርፍ ተቃርኖ ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመው፣ መሬት ላይ ባለው እውነታ መሠረት በተባለው ልክ መሠራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አዲስ ምርት ገበያው ውስጥ ለማቅረብ በፋይናንስ ተቋማትና በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ለማግኘት እንደሚቸገሩ ገልጸው፣ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ መፍራትና የመቆጠብ ሁኔታዎች እንደሚታዩ ተናግረዋል፡፡
ስለኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ሐሳባቸውን የሰጡት የመድረኩ ተሳታፊ፣ በኤክስፖው ውስጥ ከሚዘጋጅ ውይይት በኋላ የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን በተባለው ልክ አብሮ ተገናኝቶ መሥራት ሁኔታ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
በኤክስፖ ወቅት የሚነገሩት እዚያው እንደሚቀሩ ገልጸው፣ በተባለው ልክ መፍትሔዎችን ወደ ትግበራ ለማስገባት የተገደበ አሠራር እንዳለ ገልጸዋል፡፡