

አዲሱ ፓስፖርትና የተለያዩ የጉዞ ሰነዶች ይፋ ሲሆኑ
ዜና የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በአገሪቱ ታሪክ አምስተኛውን ፓስፖርት ይፋ አደረገ
ቀን: February 23, 2025
- በሥራ ላይ ያለው ፓስፖርት የአገልግሎት ዘመኑ እስኪያልቅ ያገለገላል ተብሏል
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለኢትዮጵያ አምስተኛ ነው የተባለው አዲሱን ፓስፖርትና የተለያዩ የጉዞ ሰነዶችን ይፋ አደረገ፡፡ አገልግሎቱ አዲሱን ፓስፖርት ጨምሮ ከአሥር በላይ የጉዞ ሰነዶችን ይፋ ያደረገው የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረትና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ በእጅ ጹሑፍ የሚዘጋጀው፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ የደርግ መንግሥት የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ፓሰፖርት፣ የሽግግር መንግሥት ፓስፖርት፣ እንዲሁም በኢሕአዴግ ዘመን ተዘጋጅቶ እስካሁን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ባለኮከቡ አራተኛው ፓሰፖርት ሲሆን፣ እንዲሁም አሁን ይፋ የተደረገው አዲሱ ፓስፖርት ለአገሪቱ አምስተኛ ፓስፖርት ሆኗል፡፡
ከየካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በይፋ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ የተባሉት ሰነዶቹ በርካታ የደኅንነት መጠበቂያ ይዘቶች ያሏቸው መሆኑን፣ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ ስለአዲሱ ኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ሲገልጹ፣ ‹‹አትዮጵያ እስካሁን ከነበሯት ፓስፖርቶች በዓይነቱና በደረጃው እጅግ በጣም ከፍ ያለና የተለየ የጉዞ ሰነድ ሆኖ ተዘጋጅቷል፤›› ብለዋል፡፡
የአዲሱ ፓስፖርት ዲዛይን ባለቤትነት በኢትዮጵያ የተመዘገበ በመሆኑ፣ ተመሳስሎ በመታተምና ከደኅንነቱ ጋር ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በማብራሪያቸው፣ ነባሩን ፓስፖርት እየተጠቀመ ያለ ማንኛውም ሰው የአገልግሎት ዘመኑ እስኪያልቅ ድረስ መገልገል እንደሚችል ገልጸው፣ የአገልግሎት ጊዜው ሲያልቅ በአዲሱ ፓስፖርት ይቀየራል ብለዋል፡፡
ይህ ከነባር ፓስፖርት ወደ አዲስ ፓስፖርት የሚደረገው የሽግግር ጊዜ በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ሕግ መሠረት በተቀመጠው የፓስፖርት የሽግግር ጊዜ መሠረት፣ አዲስ ፓሰፖርት ሲቀየር፣ ነባሩ ፓስፖርት ጊዜው እስኪያልቅ እየተጠቀመ የመቆየት መብቱ የተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡ ታትሞ የመጣው አዲሱ ፓስፖርት ለነባሩ ፓሰፖርት ከሚከፈለው የተለየ አዲስ የዋጋ ለውጥ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
በሥራ ላይ ያለው የፓስፖርት ኅትመት መሣሪያ ሃያ ዓመት ያለፈው ቴክኖሎጂ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፣ መሣሪያውን በቀላሉ ገበያ ውስጥ ለማግኘት ባለመቻሉ በአገሪቱ የሚታየውን ከፍተኛ የፓስፖርት ፍላጎት ማሟላት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
አገልግሎቱ 14 ቅርንጫፎችን በመክፈት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ተገዝተው የገቡ አዳዲስ መሣሪያዎችን ወደ ቅርንጫፍ በመላክ ሰዎች ከአካባቢያቸው ሳይርቁ አገልግሎት ያገኛሉ ብለዋል፡፡
አዲሱ ፓስፖርት እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2025 መታተም ይጀምራል የተባለ ሲሆን፣ ይሁን እንጂ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የታተሙ ፓስፖርቶች በመኖራቸው አሁን ላለው ፍላጎት የሚያሠጋ ችግር አለመኖሩ ተገልጿል፡፡
በጃፓኑ ኩባንያ ቶፓን የደኅንነት ኩባንያና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ትብብር ይመረታል የተባለው አዲስ ፓስፖርት፣ አሥር ዓመታት እንዲያገለግል ተደርጎ እንደሚዘጋጅ ተነግሯል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በማብራሪያቸው፣ አዲሱ ፓስፖርት ከዚህ ቀደም ያጋጥሙ የነበሩ የፓስፖርት እጥረትና የመዘግየት ችግርን የሚያስቀር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ፓስፖርትን አለማዘመን ተዓሚነትን ያሳጣል፣ መናኛ የደርጋል፣ ጉዞን ያዘገያል፣ የአገር ዕድገትንም ያሳንሳል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ፓስፖርቶች የጉዞ ሰነዶችና ቪዛዎች ዘመኑን የተላበሱ መሆንና የተራቀቁ የደኅንነት ይዘት እንዲኖራቸው መደረጉ ትልቅ ዕመርታ ብቻ ሳይሆን፣ ከአገሮች ጋር ያለውን የመዘመን ሠልፍ ያስተካክላል ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አክለውም የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት መጠቀም መጀመር የአገርን ገጽታና ለዜጎች የሚሰጠው ዋጋና ፋይዳ ከፍ የሚያደርግ፣ ብሎም በፓስፖርት የሚፈጸም ውስልትናን ለመቅረፍ ያስችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የሚል ፓስፖርት አገልግሎት ይሰጥ በነበረበት ወቅት የዘመኑን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የተላበሰና የተሻሸ ይመስል ነበር ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ወጣት ሆነን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ አገር ስንሄድ በእጅ የተጻፈ ፓስፖርት በመሆኑ፣ ወደ ምዕራብ አውሮፓ አገሮች ይህን ፓስፖርት ይዘን በምንሄድበት ጊዜ በመገረም ነበር የሚያዩት፡፡ ያን በመሰለ ቀይ የጉዞ ሰነድ በእጅ በተጻፈ፣ በስቴፕለር በተያያዘ ፓስፖርት መጓዝ በመቻላችን የሚመለከቱን በመገረምና በአርምሞ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ላቅ ያለ ፓስፖርት በሚያዝበት ጊዜ ግን የአገርን ክብርም ከፍ ያደርጋል፡፡ ተማሪዎች ሆነን ከሌሎች አገር ተማሪዎች ጋር ፓስፖርት እናወዳድር ነበርና አንዳንዶቻችን ፓስፖርቴን አልያዝኩም የሚል ምላሽ እንመርጥ ነበር፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡