ማኅበራዊ
‹‹የቃል ኪዳን ልጆች›› በጎንደር ዩኒቨርሲቲ

አበበ ፍቅር

ቀን: February 23, 2025

‹‹የቃል ኪዳን›› አባት ከሆኗት ልጅ ጋር የተገናኙት ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት  ከአውሮፕላን በረራ በኋላ ወደየ ጉዳያቸው ለመሔድ ከተሳፈሩበት ታክሲ ውስጥ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ክስተቱም እንዲህ ነበር፡፡ አቶ ባዩህ በዛብህ ለጉዳይ አዲስ አበባ መጥተው ጉዳያቸውን ጨርሰው ወደ ትውልድ ከተማቸው ጎንደር በመመለስ ላይ ነበሩ፡፡ የቃል ኪዳን ልጃቸው እፁብ በዛብህ ደግሞ ከደቡብ ኦሞ ጂንካ ተነስታ ነበር ወደ ጎንደር ያቀናችው፡፡ ሁለቱ የማይተዋወቁ ሰዎች ከአዲስ አበባ አየር ማረፊያ ተነስተው ጎንደር አፄ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ይደርሳሉ፡፡

‹‹የቃል ኪዳን ልጆች›› በጎንደር ዩኒቨርሲቲ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

አቶ ባዩህ  ልጃቸው መኪና ይዞ እንዲጠብቃቸው አዘው ነበር፡፡ ነገር ግን ትዕዛዛቸው ሳይፈጸም ቀርቶ በታክሲ ለመሄድ ይወስናሉ፡፡ ይህች አጋጣሚ ነበረች አቶ ባዩህንና  የቃል ኪዳን ልቻቸውን እፁብን አገናኝታ ታላቅ ለሆነ ቤተሰባዊ ትውውቅ ያበቃቻቸው፡፡

እፁብ ወደ ጎንደር ስትሄድ የመጀመሪያዋ በመሆኑ በጣም ፈርታለች፡፡ ፊቷ ላይ ግራ የመጋባት ሁኔታ ይታይባታል፡፡ ምክንያቱም ካጠገቧ ማንም የምታውቀው ሰው የላትም፡፡ ችግሯን የምታካፍለው ዘመድ ወዳጅ ካጠገቧ የሉም፡፡ አቶ ባዩህ እንደሚሉት፣ በወቅቱ ከያዘችው የልብስ ሻንጣና ፊቷ ላይ ከሚነበበው ግራ መጋባት ተነስቶ ከሩቅ ቦታ የመጣች  ጀማሪ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እንደሆነች ለማወቅ አዳጋች አልነበረም፡፡

ወቅቱም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ ተማሪዎችን የሚቀበልበት በመሆኑ የእፁብን አዲስ ገቢ ተማሪ መሆን ለመገመት ለአቶ ባዩህ ቀላል ነበር፡፡ የእፁብን መደናገጥና ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ መሆኗን ያስተዋሉትም አብረው ከተሳፈሩበት ታክሲ ውስጥ ነበር፡፡

‹‹የቃል ኪዳን ልጆች›› በጎንደር ዩኒቨርሲቲ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

አቶ ባዩህ ብቸኝነቷን አይተው ከንፈራቸውን መጠው ማለፍ አልፈለጉም፡፡ ከየት እንደመጣችና ለምን እንደመጣች ይጠይቋታል፡፡ ተማሪ እፁብም ከጂንካ ተነስታ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ደርሷት ለመመዝገብ እንደመጣችና አብሯት የመጣ የቅርብ ቤተሰብ እንደሌላት ትመልስላቸዋለች፡፡ ከደቡብ ጫፍ እስከ ሰሜን ጫፍ ዕውቀትን ለመገብየት ያለማንም ረዳት በመምጣቷ ያዝናሉ፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ አባት እሆንሻለሁ አንቺም የእኔ ልጅ ትሆኛለሽ›› በማለት እዚያው ታክሲ ውስጥ የቃል ኪዳን አባትና ልጅነታቸውን አሰሩ፡፡ አባት ከዚያን ቀን ጀምሮ ላለፉት አምስት ዓመታት የቃል ኪዳን ልጃቸውን እንደ ልጃቸው አድርገው በመንከባከብ የት ገባሽ? የት ወጣሽ? ምን ጎደለሽ? በማለትና የጎደለውን በመሙላት አባታዊ ተግሳፅና ምክራቸውን በመለገስ የበሉትን በልታ የጠጡትን ጠጥታ ማረፊያ ክፍል ተሰጥቷት ትምህርቷን በአግባቡ እንድትከታተል እያደረጉ ነው፡፡

‹‹የቃል ኪዳን ልጆች›› በጎንደር ዩኒቨርሲቲ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ላለፉት ስድስት ዓመታት ‹‹የጎንደር ቤተሰብ›› የሚል ፕሮጀክት በማቋቋም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመደቡ ተማሪዎችን በመቀበል ከጎንደር ከተማና ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር በማስተሳሰር እንደ ወላጅና  ልጅ እንዲተያዩና እንዲተዋወቁ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በ2012 ዓ.ም. ‹‹የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት›› በሚል የጀመረው ይህ ፕሮግራም፣ በየካቲት 2017 ዓ.ም. የተመሠረተበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ‹‹የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ ትውውቅና ትስስር መርሐ ግብር›› በሚል አክብሯል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) ጨምሮ የከተማዋ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው አዲስና ነባር ተማሪዎችና የቃል ኪዳን ወላጆች ተገኝተው ነበር፡፡ በዚህም ተማሪዎች በ‹‹ጎንደር ቃል ኪዳን ፕሮጀክት›› ትስስር ተፈጥሮላቸውና የቃል ኪዳን ወላጆችን አግኝተው ትምህርታቸውን በሚገባ ሲከታተሉ መቆየታቸውን ምስክርነት የሰጡ ሲሆን፣ ወላጆችም የጎንደር ከተማ ማኅበረሰብ ለልጆቻቸው ለሚያደርገው ድጋፍና እንክብካቤ አመስግነዋል፡፡

በመድረኩ ምስክርነታቸውን ከሰጡት የቃልኪዳን ወላጆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ባዩህም ከቃል ኪዳን ልጃቸው ከተማሪ እፁብ ጋር ያላቸው ግንኙነት ከቃል ኪዳን ልጅነት አልፎ ከጎንደር እስከ ጂንካ ተዘርግቶ ከእፁብ ቤተሰብ ጋር እንደ ዘመድ ግንኙነት ለመፍጠር እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ባዩህ ‹‹ልጄ›› ሲሉ የሚጠሯት ተማሪ እፁብ፣ በትምህርቷ ጠንካራና አስተዋይ እንድትሆን ከመምከርና ስታጠፋም ከመገሰፅ ባሻገር፣ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ለማድረግ ለራሳቸው ቃል ገብተው ነበር፡፡ ይህም እንደተሳካላቸው ይገልጻሉ፡፡

እፁብ ለእረፍት ወደ ጂንካ ከሔደች እንዲሁ በባዶው አትመለስም፡፡  በአካባቢዋ ተወዳጅ የሆነውን ቆጮ ታመጣለች፡፡ ለአቶ ባዩህ ቤተሰብ እስከ አሠራሩ አስተምራ ቆጮን እንዲመገቡ አድርጋለች፡፡  

ተማሪ አፁብ በወቅቱ ከጂንካ እስከ አዲስ አበባ ከእህቷ ጋር እንደመጣች ታስታውሳለች፡፡ ከዚያም እህቷ ወደመጣችበት ስትመለስ እሷ ወደ ጎንደር ነበር ያቀናችው፡፡ እፁብ ‹‹አባቴ›› ስትል የምትጠራቸው አቶ ባዩህ፣ በሕይወቷ ብዙ ነገር እንዳስተማሯትና ጥሩ ቤተሰብ እንዳገኘች ተናግራለች።

‹‹ሰኔ እና ሰኞ›› እንደሚባለው ወቅት ተገጣጠመና የእፁብ ታናሽ ወንወድም የ12ኛ መልቀቂያ ፈተና ተፈትኖ ሲያልፍ ከጂንካ ተነስቶ ጎንደር ዩኒቨርሲቲን መዳረሻው ያደርጋል፡፡    እፁብን ተቀብለው ለቁም ነገር ያበቁት አቶ ባዩህ፣ ወንድሟን ተቀብለው እንደ ልጃቸው ተንከባክበው አስተምረው ለቁም ነገር ለማብቃት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

ፕሮጀክቱ የጎሳና የሃይማኖት ክፍፍልን በማስቀረት የኢትዮጵያን አንድነት እንደሚያጠናክር የተናገሩት አቶ ባዩህ፣ ጅማሮው ተጠናክሮና ተስፋፍቶ ይቀጥል ዘንድ ሁሉም አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩበት ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ በተለይ የሰላም ሚኒስቴር  ጉዳዩን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ የራሱ በጀት እንዲመደብለት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሃጂ አንዋር ቃሲም  ሌላኛው የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት ሲመሠረት ከመሥራች ኮሚቴዎች አንዱ ነበሩ፡፡ እስካሁን በነበራቸው ቆይታ ከጅማ፣ ከባሌና ከሻሼመኔ የመጡ 11 የቃል ኪዳን ልጆችን ተቀብለው በማስተማር አስመርቀውና ለቁም ነገር አብቅተው በሰላም ወደ ቤተሰቦቻቸው መሸኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከሱማሌ ላንድ  በስኮላርሺፕ የመጡ 11 ተማሪዎችን ተቀብለው ተመሳሳይ ድጋፍና እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ተሞክሮው በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓና በጃፓን የትምህርት ተቋማት የተለመደ አሠራር እንደሆነ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ የተናገሩት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ለፕሮጀክቱ ጅማሮ ፈር ቀዳጅና ታሪካዊ መሠረትን የጣሉት ሃይማኖታዊ ተቋማት መሆናቸውን የአብነት ተማሪዎች ቀለም ለመቅሰም ሲመጡ፣ የማኅበረሰቡ የአደራ ልጆች ይሆኑ እንደ ነበር አስራት (ዶ/ር) ያስታውሳሉ፡፡ ዘር፣ ቀለምና የትውልድ ቦታ ሳይጠይቅ የሚመገቡትን፣ የሚጠጡትንና የሚለብሱትን የሚሰጣቸው የአካባቢው ማኅበረሰብ ነውም ይላሉ፡፡

ቆሎ ተማሪዎች በየቀኑ ደጅ ሲጠኑ ለምጽዋት እጁን ይዘረጋላቸዋል፡፡ በአዘቦት ዳረጎት ሲጠይቁት ‹መጡብኝ› ብሎ በር አይዘጋባቸውም፡፡ የበዓል፣ የደስታም ይሁን የሐዘን ዝግጅት ካለ ተማሪዎቹን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ቀለምን ከየኔታ፤ ሁለገብ ድጋፍን ደግሞ ከማኅበረሰቡ እያገኙ ትምህርታቸውን ተከታትለው በየደረጃው ይመረቃሉ ሲሉ ፕሮጀክቱም ከዚህ ተሞክሮ መውሰዱን ያክላሉ፡፡

በሙስሊሙ ማኅበረሰብም በኩል ለደረሶች የሚደረገው እንክብካቤና የሰብዓዊነት መንገድ ልክ በክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ለቆሎ ተማሪ ከሚደረገው እንክብካቤ ጋር እንደሚመሳሰል ያስረዱት አስራት (ዶ/ር)፣  ‹‹ዜጎች ተምረው  አገር ተረካቢ፣ የሃይማኖት ጠባቂ  ይሆኑ ዘንድ ማኅበረሰቡ  የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል፣ ያግዛል፣ ያቀርባቸዋል፣ እንደልጆቹ ይወዳቸዋል ምክንያቱም የቃል ኪዳን ልጆቹ ናቸው፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ‹‹ቃሌ ከሚጠፋ የወለድኩት ይጥፋ›› የሚል አባት አደር ባህል አለው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህ የሚሆነው በተለይ የቀድሞ የአገራችን ሰው እምነቱን በተግባር የሚኖርና የፈጣሪውን ትዕዛዛት የሚፈጽም እንዲሁም  በጎ ሥራ በመሥራቱ  ነገ  ከፈጣሪ አገኘዋለሁ፣ ግዴታዬም ነው ብሎ ስለሚያምን የቆሎ ተማሪዎችንና ደረሶችን የቃል ኪዳን ልጁ አድርጎ ለመቀበል ይሽቀዳደማል ሲሉ አብራርተዋል።

ይህን ነባርና አገር በቀል እሴት ወደ ዘመናዊ የትምህርት ተቋም በማላመድ ‹‹የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት››ን የተገበረው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ይህ ፕሮግራም ለተማሪዎች፣ ለወላጆች፣ ለጎንደር ሕዝብ፣ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብሎም ለኢትዮጵያ ያለውን የጎላ ፋይዳ በመገንዘብ ጭምር ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሰላም አምባሳደሮችን በኢትዮጵያ መፍጠር በሚል ርዕስ በፈረንሣይ  ፈንድ ፎር ኢኖቬሽን ኢን ዴቨሎፕመንት ድርጅት ድጋፍ  የቤተሰብ ትስስር ላይ ምርምር እየተካሄደ እንደሚገኝ የተናገሩት አስራት (ዶ/ር)፣ ምርምሩ የጎንደር ዩኒቨርስቲ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ፕሮጀክት የሚፈጥረውን ቤተሰባዊ ትስስር ውጤታማነት በማጥናት፣ ከሌሎች ክልሎችና አገሮች ጎንደር መጥተው ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች የጎንደር ሕዝብ እንግዳ ተቀባይና አክባሪ ሕዝብ ስለመሆኑና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም እንዲተገበር ለማስቻል አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኜው በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በቀዳሚነት የጀመረው ይህ መርሐ ግብር ወደ ሌሎች አካባቢዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሰፋና እንደ ጥሩ ተሞክሮ እንዲታይ ጠይቀዋል።

ከዚህ ባሻገር በሰላም ሚኒስቴር በኩል ዩኒቨርሲቲው ዕውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፣ ‹‹የሰላም አንዱ መንገድ መዛመድና መተዋወቅ በመሆኑ ትስስርና ቤተሰባዊ ግንኙነት አንዳችን ለሌላችን ያለንን ትስስር ያዳብረዋል፣ ያጎለብተዋልም፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አቶ ቻላቸው፣ ‹‹ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጀመረው የቃል ኪዳን ቤተሰብ አዲስ መንገድ፣ ከነበረው የተቀዳ አገር ሊማርበትና ሊስፋፋ የሚገባው ተሞክሮ፤›› ነው፡፡

ይህ ለሰላምና ለአንድነት መሠረት ይሆናል የተባለው ‹‹የጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ ትውውቅና ትስስር›› መርሐ ግብር፣ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና አካባቢዎች እንዲስፋፋና ተደራሽ ይሆን ዘንድ በሰላም ሚኒስቴር በኩል ዕውቅና እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፣ ሚኒስቴሩ ለፕሮጀክቱ እውቅና እንደሚሰጥና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡  

በመርሐ ግብሩ፣ ስለ ‹‹ጎንደር ቃል ኪዳን ቤተሰብ›› ምስክርነት ለመስጠት ከሐዋሳ፣ ከወልቂጤ፣ ከአዳማ እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው ነበር፡፡

በዚህም ምስክርነታቸው የቃል ኪዳን ቤተሰብ ትውውቅና ትስስር መርሐ ግብር በሕዝቦች መካከል የነበረውን የተዛባ አመለካከት የቀየረና ያለውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስና አንድነት ያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ወላጅ ይሰማቸው የነበረውን ሥጋት ያቃለለ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡