ዘጠነኛው የኢትዮ ኸልዝ ዓውደ ርዕይና ጉባዔ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደበት ወቅት

ማኅበራዊ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ያለውን የመድኃኒት ዋጋ ለማረጋጋት መንግሥት እያቀረበ መሆኑ ተገለጸ

የማነ ብርሃኑ

ቀን: February 23, 2025

የብር የመግዛት አቅም በመዳከሙ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኘውን የመድኃኒት አቅርቦት ዋጋ ለማረጋጋትና ተመጣጣኝ ለማድረግ፣ መንግሥት አስፈላጊና ውድ የሚባሉትን ጨምሮ መድኃኒቶችን በበቂ ሁኔታ እያስገባሁ ነው አለ፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ገልገሎ (ዶ/ር)፣ ዓርብ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጡት ማብራሪያ፣ በግልና በጤና ተቋማት የመድኃኒት ዋጋ በከፍተኛ መጠን በመጨመር ላይ ነው ብለዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣውን የመድኃኒት ዋጋ ለማረጋጋት አስፈላጊና ውድ የሚባሉ መድኃኒቶች አቅርቦት ያለ ምንም መቆራረጥ እንዲሠራጭ ለማድረግ፣ መንግሥት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹በተያዘው ዓመት በአገር ውስጥ ከሚገኙ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመድኃኒት ግዥ ተፈጽሟል፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከሦስት ዓመት በፊት ከአገር ውስጥ አምራቾች የሚገዙ መድኃኒቶች ዋጋቸው ከ1.4 ቢሊዮን ብር አይበልጥም ነበር ሲሉ አስረድተዋል፡፡ አሁን ግን አዳዲስ የመድኃኒት አምራች ድርጅቶች ወደ ዘርፉ በመቀላቀላቸውና በስፋትም ማምረት በመጀመራቸው የአገር ውስጥ ግዥ ማደጉን ተናግረዋል፡፡

እንደ አብዱልቃድር (ዶ/ር)፣ ለጤና ተቋማት ግብዓት የሚያገለግሉ እንደ ጓንትና ስሪንጅ የመሳሰሉ የሕክምና ግብዓቶች፣ ከሁለት ዓመት በፊት ከውጭ በግዥ ይገቡ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጓንትና ስሪንጅ የሚያመርቱ ድርጅቶች በመቋቋማቸው ግብዓቶቹ በአገር ውስጥ እየተሸፈኑ ናቸው ብለዋል፡፡

አዳዲስ የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ወደ ሥራ በመግባታቸውና ቀደም ሲል የነበሩትም ምርቶቻቸውን ማሳደግ በመቻላቸው፣ ስምንት በመቶ ብቻ የነበረው የአገር ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት ወደ 37 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ጤና ተቋማት 65 በመቶ መድኃኒት በብድር የሚወስዱት ከተቋማችን ነው፡፡ በብድር ለወሰዱት መድኃኒትም ክፍያ በወቅቱ ከመፈጸም አንፃር ችግሮች ነበሩ፤›› ያሉት አብዱልቃድር (ዶ/ር)፣ ችግሩን ለመቅረፍ የጤና ተቋማት በብድር ለወሰዱት መድኃኒት በስድስት ወራት ውስጥ ክፍያ ካልፈጸሙ ከባንክ የሒሳብ አካውንታቸው ለመውሰድ የሚያስችል ሕግ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል ሜዲካል ላቦራቶሪና ማኑፋክቸሪንግ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ዳንኤል ዋቅቶሌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ መንግሥት የጤና ዘርፉን ለማሻሻልና የኅብረተሰቡን የጤና ሥርዓት ሊያሳድጉ የሚችሉ ፖሊሲዎችንና መመርያዎችን በማውጣት ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ፋርማሲዩቲካል አቅርቦት አገልግሎት በጥራት የተረጋገጡ መድኃኒቶችን፣ የላቦራቶሪ ኤጀንቶችና የሕክምና መሣሪያዎችን በመግዛትና በማሠራጨት ከ70 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ተቋሙ የሕዝብ ጤና ተቋማት አስፈላጊ የጤና አቅርቦቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡