ዮናስ አማረ

February 23, 2025

የጀርመኑ የኮንስትራክሽን ተቋራጮች ፌዴሬሽን ባውቨርባንድ (BAUVERBANDE.NRW)፣ ኢትዮጵያዊያን የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችን ወደ ጀርመን በመላክ ሥልጠና እያደረገ መሆኑን ገለጸ፡፡ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ካሉ የኮንስትራክሽን ተቋራጮች ማኅበራትና ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በትብብር የሚሠራ ሲሆን፣ የአቅም ግንባታና የሥልጠና ድጋፍ መስጠት ላይ እንደሚያተኩር ጠቁሟል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ 34 ኢትዮጵያዊያን የግንባታ ባለሙያዎችን ወደ ጀርመን ልኮ ትምህርት እንዲያገኙ ማመቻቸቱን ያስታወቀው ድርጅቱ፣ ይህን የትምህርት ፕሮግራምም ለቀጣይ ሁለት ዓመታት እንደሚቀጥል ነው ያስታወቀው፡፡

ድርጅቱ ባሳለፍነው ሳምንት የአማራ ክልል፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብ፣ የድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር ኮንስትራክሽን ተቋራጮች ማኅበራት፣ እንዲሁም የጀኔራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አመራሮች በተገኙበት፣ የሁለት ቀናት ወርክሾፕ በአዲስ አበባ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በቀጣይ ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የሚሠራውን ፕሮግራም በዚሁ ጊዜ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በዋናነት የውኃ አቅርቦትና ማጣራት ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን አቅም የሚያጠናክር የቴክኒክና ሥልጠና ድጋፍ እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል፡፡

በጀርመን ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት (GIZ) የሚደገፈው የዚህ ፌዴሬሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሄንዝ ሪትማን፣ እ.ኤ.አ. በ 2020 ተጀመረ ያሉት ኢትዮጵያዊያን የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችን ጀርመን ወስዶ የማስተማር ድጋፍ፣ ለቀጣዮቹ ዓመታትም እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የየክልሉ የኮንስትራክሽን ተቋራጮች ማኅበራት በሚያቀርቡት ጥቆማና ከቴክኒክና ሙያ ተማሪ ቤት የወጡ የጀርመን ኢሚግሬሽን ሕግን ማሟላትና ፈተና ማለፍ የቻሉ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉም ብለዋል፡፡ 

ሐሙስ የካቲት ቀን 2017 ዓ.ም. በማዶ ሆቴል በነበረው ዓውደ ጥናት ማጠቃለያ ላይ ‹‹እ.ኤ.አ. በ2023 ወደ 11 ሰው፣ በቀጣዩ 2024 ደግሞ ወደ 23 ሰው ወደ ጀርመን ለሥልጠና ሄዷል፡፡ ፕሮግራሙን ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከሥራና ክህሎት እንዲሁም ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ነው ያስጀመርነው፡፡ ዘንድሮ ውኃ አቅርቦትና ጥቅም ላይ የዋለ ውኃን በማጣራት ለመልሶ ጥቅም ማዋል ኮንስትራክሽን ላይ አተኩረናል፡፡ ውኃ አቅርቦት ላይ ያተኮርነው የውኃ ፍላጎት እየጨመረ የሚሄድ ሥራ በመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም አረንጓዴ ልማት በጀርመን የሚበረታታ በመሆኑም ነው›› ሲሉ ዕቅዳቸውን አብራርተዋል፡፡

ጀርመን ሄዶ አንድ የኮንስትራክሽን ባለሙያ ለመሠልጠን ሦስት ዓመታት ይፈጃል የሚሉት ሄንዝ፣ ሲጨርሱም በዚያው መቀጠርና መሥራት ይችላሉም ብለዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ያሉ የኮንስትራክሽን ተቋራጮች ማኅበራት በዋናነት አባሎቻቸውን እንድናሠለጥንና አቅም እንድንገነባላቸው ነው የሚፈልጉት፡፡ እኛም ለኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ መፍጠር እንደሚበጅ በማመን ነው ወደ ሥልጠና ድጋፉ ያጋደልነው፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ ወደ ጀርመን ሄደው በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት የተሻለ ሥልጠና ያገኛሉ፣ ቀጥሎ በኢንዱስትሪዎች ተሰማርተው እየሠሩ እንዲማሩ አመቻችተናል፡፡ በመጨረሻ ደግሞ በተለያዩ ኩባንያዎች መቀጠር ወይም ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ይችላሉ፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

የጀርመኑ የኮንስትራክሽን ተቋራጮች ፌዴሬሽን እንደሚገልጸው፣ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ተማሪ ሥልጠና በወር ከ2,500 እስከ 3000 ዩሮ ይጠይቃል፡፡ ከጂአይዜድና ከሌሎች ድርጅቶች እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ አባላት በሚገኝ ድጋፍ፣ ገንዘቡ እንደሚሸፈንም ጠቁሟል፡፡ ወደ 4,500 ተቋራጮችን በአባልነት የያዘው የጀርመኑ ፌዴሬሽን ለአገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እንዲሁም ለቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ጉልህ ሚና እንዳለው የሚገልጽ ሲሆን፣ በቴክኒክና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ጀርመን ያዳበረችውን ልምድ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ለማሻገር በማሰብ በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ መክፈቱን ጠቁሟል፡፡    

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኃላፊ ሄንሪ ሆሽለር በበኩላቸው፣ ለኢትዮጵያ ተቋራጮች ቁሳቁስና ሥልጠና ከመደገፍ በዘለለ፣ የአገሪቱን የቴክኒክና ቮኬሽናል ትምህርት ዘርፍ የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቲቬት ሥርዓቱን የተሻለ ለማድረግ እንዲሁም ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን የሚያፈራ እንዲሆን እንረዳለን፡፡ ቲቬት ተቋማት ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የተማረ የሰው ኃይል እንዲያፈሩ ከማድረግ በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ የተሻለ ጥራት ያለው የግንባታ ሥራ የሚሠሩ ተቋራጮችን ለማፍራት በማሰብ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ከጄኔራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ጋርና ከሌሎችም ጋር የጀመርነው አጋርነት የዚህ አካል ነው፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ በኢትዮጵያ ይህንኑ የኮንስትራክሽን መስክን የመደገፍ ሥራ በኢትዮጵያ ሲሠራ መቆየቱን ያስታወቁት ሄንሪ፣ ከኮሌጅ የወጡ ተማሪዎችን ወደ ጀርመን ወስዶ ከማሠልጠን በተጨማሪ ታች በሥራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችንም ወስዶ ለማሠልጠን ፕሮግራም መክፈታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ግንበኛ፣ አናጺ፣ ለሳኝ፣ የፌሮ ባለሙያ ወዘተ የሚባሉ ገንቢዎችን በቀጣይ እንደሚወስዱና እንደሚያስተምሩ ጠቁመዋል፡፡

በዚሁ ወርክሾፕ ላይ የተገኙት የደቡብ ኮንስትራክሽን ተቋራጮች ማኅበር ሊቀመንበር ጉጃ ጉሊ፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የሙስና፣ የቁሳቁስ፣ የጥራት፣ ሌላም ብዙ ዓይነት ችግር እንደ አገር ያሉበት ዘርፍ ነው፡፡ ቁሳቁስን በሚመለከት እንደ አገር ሁሉንም የግብዓት ችግር ማሟላት ይቻላል እላለሁ፡፡ ይህ የጀርመን ድርጅት ለምሳሌ በኤሌክትሪክ ዝርጋታ ወቅት ትክክለኛ ሥራ መሠራቱን በአንድ ቦታ መፈተሽ የሚያስችል መሣሪያ አቅርቦልናል፡፡ ይህ የግንባታ ጥራት ላይ ትልቅ ትርጉም ያለው ውጤት ያመጣል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

የጀርመኑን ድርጅት በሚመለከት የቴክኒክና ሥልጠና ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነ የጠቀሱት የአማራ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ማኅበር የቦርድ አመራርና ፀሐፊ የሆኑት ጋሻው አቡሀይ በበኩላቸው፣ ዘርፉ በክልሉ የተደቀኑበት ችግሮች በርካታ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ‹‹ከለውጡ በፊት የነበረው የፖለቲካ ተፅዕኖ ትልልቅ ተቋራጮችን ለማፍራት አግዶናል፡፡ ከለውጡ ወዲህ ደግሞ የሰላም ዕጦት ዋነኛ ችግር ሆኖብናል፤›› ብለዋል፡፡ ከ27 በላይ ትልልቅ የልማት ድርጅቶች በክልሉ መኖራቸውና በመንግሥት በኩል የሥራ ቅድሚያ የሚሰጠው ለእነዚሁ ድርጅቶች በመሆኑ፣ በማኅበሩ ሥር ያሉ 757 አባላትን ጨምሮ በግል የሚንቀሳቀሱ ተቋራጮች የሥራ ዕድል ለማግኘት እየተቸገሩ እንደሚገኝም አክለው ገልጸዋል፡፡

የጀርመኑ ተቋም ከሚያደርገው ድጋፍ በላይ ከመንግሥት ብዙ ዓይነት ድጋፍ እንደሚጠብቁ የጠቆሙት የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ዳዲ ገዳ በበኩላቸው፣ በ2004 የተመሠረተው ማኅበራቸው ወደ 455 አባላት እንዳሉት ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ሰላም ችግር በመሆኑ ለክልላችን ኮንስትራክሽን ዘርፍ ትልቅ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ ከትልልቅ ኮንትራክተሮች ጋር መወዳደርም ከባድ ፈተና ሆኗል፡፡ ሲሚንቶና ብረት አንድ ወቅት ችግር ነበሩ፡፡ የፊኒሺንግ ዕቃዎችን ከውጪ ማምጣቱም ችግር ነው፡፡ የፋይናንስ ችግርም ለዘርፉ ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ከመንግሥት ሲደረግ የቆየ ሲሆን በቁርጥ ዋጋ ለኮንትራክተሮች ፕሮጀክቶች ሲሰጥ ነበር የቆየው፡፡ ሆኖም አሁን ላይ መንግሥት የፈጠራቸው ትልልቅ ተቋራጮች ይህን ዕድል ስለወሰዱት አቅማቸውን ገና ያላጠናከሩ አባሎቻችን ተቸግረዋል፤›› በማለት  ተናግረዋል፡፡