ተመስገን ተጋፋው

February 23, 2025

መንግሥት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲገቡ ቢፈቅድም፣ ዘርፉን የተመለከተ የኢንሹራንሽ ዋስትናና የሰሌዳ አገልግሎት በሚፈለገው ልክ እየተሰጠ አለመሆኑን፣ ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ አስታወቀ፡፡

ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ ይህንን የገለጸው ሐሙስ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተከታታይ ዓመታት ሽልማት የወሰደበትን ‹‹IONIQ 5›› ተሸከርካሪ ለዕይታና ለሽያጭ ባቀረበበት፣ እንዲሁም በዘመናዊ መንገድ የሃንዳይ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የተደራጀውን ወርክሾፕ አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎችን ገለጻ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

የማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መልካሙ አሰፋ እንደገለጹት፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የተመለከተ ግልጽ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ፣ አስመጪዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አስገብተው ለመሸጥ ሥጋት አድሮባቸዋል፡፡

ማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አምርቶ ካጠናቀቀ በኋላ፣ ሰሌዳ ለማውጣት ሲሄድ ችግር እንደሚገጥመውና በአንድ ወቅት ተቀባይነትን ሳያገኝ የቀረበት አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበር አክለው ገልጸዋል፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዋስትና ለመስጠት ይፈሩ እንደነበር፣ ነገር ግን ማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ ለተቋማት ሥልጠና በመስጠት አሁን ችግሩ በተወሰነ መንገድም ቢሆንም ሊቀረፍ እንደቻለ አስረድተዋል፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መጀመሪያ አካባቢ በፍራቻ ምክንያት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ዓረቦን ከ150 እስከ 200 ሺሕ ይጠይቁ እንደነበር፣ ይህም ከነዳጅ መኪናዎች ጋር ሲነፃፀር ሰፊ ልዩነት እንዳለው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በዚህ የተነሳ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መግዛት እንደማይፈልግ ጠቅሰው፣ በተመሳሳይ ባንኮች ለነዳጅ ተሽከርካሪ ከአሥር እስከ 12 ዓመታት የሚቆይ ብድር እንደሚሰጡ፣ ለኤሌክትሪክ ሲሆን ግን ለአምስት ዓመታት ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባንኮች ይህንን አሠራር የተከተሉበት ምክንያት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ ዕድሜ ከአምስት ዓመት እንደማይበልጥ፣ ይህም ከተበላሸ ተሽከርካሪው አካሉ ብቻ ስለሚቀር በረዥም ጊዜ የሚመለስ ብድር መስጠት እንደማይፈልጉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ባንኮች ላይ መፍረድ እንደማይቻል የተናገሩት አቶ መልካሙ፣ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ዋስትና የሚሰጥ ተቋም ካለ ባንኮች የብድር ሁኔታውን ቢያንስ የስምንት ዓመታት ገደብ እንዲኖረው እንዲያደርጉ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡  

ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት ከመንግሥት አካላት ጋር በመሆን የመሠረተ ልማቶች እየተዘረጉ እንደሆነ ገልጸው፣ ጉዳዩን በተመለከተ በቀጣይ በክልሎች ለመሥራት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡   

ማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ የኤሌክትሪክ መኪና አምርቶ መሸጥ ከጀመረ አራት ዓመታት ሊሆነው መቃረቡን፣ በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ሞዴሎችን በማምረት ለሽያጭ እያቀረበ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ለዜጎች ከጎንዮሽ ጉዳት የፀዳ ትራንስፖርት ለመስጠት መንግሥት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ አቶ በረኦ ሐሰን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት በነዳጅ ላይ ጥገኛ ሆና መቀጠሏን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታው፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለነዳጅ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያወጣ አክለዋል፡፡

በተለይ በአፍሪካ የ‹‹አረንጓዴ ትራንስፖርት›› ኩራት ለመሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት፣ ከግሪን ኢኮኖሚ ጎን ለጎን ለማስኬድ ከፍተኛ ጉዞ መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሲገጣጠም በርካታ ውስብስብ ነገሮች ስላሉት፣ በፍጥነት ለማምረት ወደ ሥራ አለመገባቱን የማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ መሥራች ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ገልጿል፡፡