የኢትዮጵያና የኤርትራን ጦርነት ያስቆመው የአልጀርስ ስምምነት ሲፈረም የወቅቱ የአልጄሪያ ፕሬዚዳንት አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ይታያሉ

ፖለቲካ

ዮናስ አማረ

February 23, 2025

ጉዳዩ ከመንግሥት ሚዲያዎች እንካ ሰላንቲያ ያለፈ ይመስላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኤርትራና በኢትዮጵያ የመንግሥት ሚዲያዎች ላይ አንዱ ሌላውን የመተቸትና የመወንጀል ዘገባዎች ተደጋግመው መታየት ጀምረዋል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና በተለያዩ አገሮች በአምባሳደርነት የሠሩት ዲፕሎማት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የኤርትራን መንግሥት በጠንካራ ቃላት የሚሸነቁጥ ሀተታ በአልጄዚራ የአስተያየት ገጽ ላይ አስነብበዋል፡፡ “To avoid another conflict in the Horn of Africa, now is the time to act” በሚል ርዕስ የተነበበው የሙላቱ (ዶ/ር) ጽሑፍ፣ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የአፍሪካ ቀንድ ዋናው ግጭት ጠማቂ ሰው እንደሆኑ በሰፊው ያትታል፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ትኩሳት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስመራ ሄደው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሁለቱን አገሮች ግጭት በማርገብ ሰላም በተፈጠረበት ወቅት

ኤርትራን ለ32 ዓመታት የገዙት ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራንና ኤርትራዊያንን ከዓለም አግልለው በግዞት ሥርዓት ውስጥ ማኖራቸውን በመጥቀስ የሚንደረደረው ጽሑፉ፣ ኢሳያስ ሰላማዊ ግንኙነትና ትብብር ከመፍጠር ወይም ለጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከመሥራት ይልቅ በግጭት አዙሪት ውስጥ መኖርን የሚያስቀድሙ መሪ እንደሆኑ ይበይናል፡፡ ‹‹ኤርትራ ከተመሠረተች ጊዜ ጀምሮ ልክ እሳት የመጫር አባዜ እንደተጠናወተው ሰው፣ ኢሳያስ ከጎረቤት አገሮች እስከ ታላላቅ ሐይቆች ቀጣና ኤርትራን በግጭት ውስጥ ሲከቱ ነው የኖሩት፡፡ ኢሳያስ በየቦታው የጦርነት እሳት የሚለኩሱት ደግሞ በግጭት አዙሪት የመኖር አባዜ ስለተጠናወታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከግጭት ውጪ ህልውናቸውን ለማስቀጠል የማይችሉ በመሆናቸው ነው፤›› በማለትም ጽሑፉ  ይፈርጃል፡፡     

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ ጀምሮ የሰላም እጃቸውን በመዘርጋት የኤርትራው ኢሳያስን በመጨበጣቸውና ሁለቱን አገሮች በማስታረቃቸው፣ ዓለም ተደንቆ ለኖቤል የሰላም ሽልማት እንደበቁ የሚጠቅሰው ሀተታው ይሁን እንጂ ኢሳያስ ይህን አጋጣሚ በኢኮኖሚ ትስስርም የበለጠ ለማጠናከር በራቸውን ባለመክፈታቸው የተነሳ ግንኙነቱ ወደ ተሻለ አዎንታዊ ምዕራፍ ሳይሸጋገር መቅረቱን ጽሑፉ ያትታል፡፡ የመሠረተ ልማት ትስስርም ሆነ የኢኮኖሚ ግንኙነት መጠናከር በኢሳያስ የሚፈለግ ባለመሆኑና ሰውየው ከዚህ ይልቅ በግጭትና ጦርነት ውስጥ መግባትን የሚመርጡ በመሆናቸው፣ በቀጣናው ሰላም ማስፈን አለመቻሉንም ጽሑፉ ያብራራል፡፡ ሕወሓት የኢትዮጵያ መንግሥትን ለማፍረስ ጥቃት ሲከፍትና የትግራይ ጦርነት ሲፈነዳም በሕወሓት ላይ ለረዥም ዘመናት ቂምና ቁርሾ ቋጥረው የቆዩት ኢሳያስ፣ ጦራቸውን ወደ ኢትዮጵያ አስገብተው በትግራይ ክልል ዕልቂትና ግፍ እንደፈጸሙ ሙላቱ (ዶ/ር) በጽሑፋቸው ተንትነዋል፡፡

ሱዳን በጦርነት ተዘፍቃ ሳለ፣ ሶማሊያም ገና ከሽብር ኃይሎች ጥቃት ሳትላቀቅ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ሁኔታ ገና ከሥጋት ሳይወጣ የኢሳያስ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ግጭት እየጠመቀ ነው ይላሉ ጸሐፊው ሲቀጥሉ፡፡ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ኃይሎችን በመደገፍና በማስጠለል፣ እንዲሁም በትግራይ ካሉ የሕወሓት ኃይሎች ጋር አጋርነት በመፍጠር ኢሳያስ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ እያደረጉ ነው ይላሉ፡፡ የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በትግራይ ሰላም ማስፈን ቢቻልም ነገር ግን ከሰላም ይልቅ ጦርነት እንዲቀጥል ፍላጎት ያላቸው ኢሳያስ፣ አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ዋና ያለ መረጋጋትና የግጭት ምንጭ እየሆኑ ናቸው በማለት ሙላቱ (ዶ/ር) የኤርትራን መንግሥት ወንጅለዋል፡፡

ይህን መሰል ይዘት ያለው በአልጄዚራ የተነበበው የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንትና ዲፕሎማት የሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ጽሑፍ ብዙ ዓይነት ሐሳብና አስተያየት ከየአቅጣጫው እየቀረበበት ነው፡፡ በተለይም የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል የሰጡት ምላሽ አንደኛው ነው፡፡

የማነ በአስተያየታቸው የሙላቱ (ዶ/ር) ጽሑፍ የጦርነት ድግስና ጠብ ጫሪ አጀንዳን ማራመጃ ሆኖ የቀረበ እንደሆነ ገልጸውታል፡፡ ኤርትራ በዓለም አቀፍ ሕግ የምትገዛና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የሌላት አገር መሆኗን የጠቀሱት የማነ፣ የኢትዮጵያ አሁናዊ ቀውስ ከአገራቸው ጋር የሚገናኝ ነገር እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የገጠማት ውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በኤርትራ ላይ ጣት መቀሰሩ መፍትሔ አይሆንም፡፡ እኛ ሳንሆን ኢትዮጵያ በቀጣናችን ለሚፈጠሩ ቀውሶች ምንጭ እየሆነች ነው፡፡ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ቀጣናውን ለውጥረት ከዳረጉ ችግሮች አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌሎችን ከመክሰስ በፊት ለራሷ የውስጥ ችግሮች በራሷ መፍትሔ መፈለግ አለባት፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኤርትራ በትግራይ ጦርነት የገባችውና የተሳተፈችው ሕወሓት የኢትዮጵያ ሠራዊትና መንግሥት ላይ ጥቃት ማድረስ ብቻ ሳይሆን፣ ኤርትራንም ዒላማ ያደረገ ውጊያ በመክፈቱ እንደሆነ የማነ ይፋ አድርገዋል፡፡ ‹‹በሕወሓት ጥቃት የደረሰበትን የሰሜን ዕዝ ኃይል አስጠልለናል፡፡ ጦርነቱ ውስጥ የገባነውም በኢትዮጵያ መከላከያና መንግሥት ይፋዊ ግብዣ ሲሆን፣ ዛሬ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል ግጭትም እያነሳሱ ነው እያሉ ቢወነጅሉንም፣ በወቅቱ ላደረግነው ለዚህ እገዛችንም በይፋ ሲያመሠግኑን ቆይተዋል፤›› በማለት ነበር የኤርትራው ባለሥልጣን ጠንካራ ምላሽ የሰጡት፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሟቹ የመለስ ዜናዊ ሴት ልጅ ሰመሀል መለስ በበኩሏ፣ ከሰሞኑ የውዝግብ ምንጭ ስለሆነው የኢትዮጵያና ኤርትራ ባለሥልጣናት መካሰስ የሚተች ጽሑፍ አስነብባለች፡፡ ዛሬ ሲካሰሱና ለጦርነት ሲዘጋጁ ቢታዩም የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥት ግንባር ፈጥረው በትግራይ ላይ ጭፍጨፋ ሲያደርጉ ነበር በማለት የምትወነጅለው ሰመሀል፣ የትግራይ በተለይም የሕወሓት ፖለቲካ ልሂቃን በዚህ ውጥረት ተሳታፊ በመሆን የትግራይን ሕዝብ ህልውና ዳግም አደጋ ላይ እንዳይጥሉ አሳስባለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ከኤርትራ ጋር እየተወዛገበ ያለው የባህር በር ለማግኘት ብሎ በፈጠረው አጀንዳ ብቻ ሳይሆን፣ በግጭትና በቀውስ ስም ምርጫ ለማራዘም ካለው ፍላጎት ሊሆን እንደሚችልም ሰምሀል ትጠቁማለች፡፡ የትግራይ ፖለቲከኞች የውጭ ጣልቃ ገብነትን አጥብቀው እንዲከላከሉ የምታሳስብ ሲሆን፣ የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች ዋናውና አሳሳቢ ጉዳይ መሆን ያለበት የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊነት መሆኑንም ታስረዳለች፡፡

የሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ጽሑፍ ከሰሞኑ ሙግቶች ሲቀሰቅስ ነው የሰነበተው፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ ለአይቀሬ ጦርነት እየተዘጋጁ ነው የሚለው ደግሞ ከሁሉ ጎልቶ መሰማት ጀምሯል፡፡ ሁለቱ ጎረቤት አገሮች ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጁ ነው ከሚለው ጎን ለጎን ደግሞ በቀጣናው ያለውን የኃይል አሠላለፍ ለመበተን የተደረገ ጥረት ተደርጎም ሲቀርብ ሰንብቷል፡፡ የሰምሀል ጽሑፍ ይህን በተወሰነ መንገድ ለማሳየት የሞከረ ሲሆን፣ ከሙላቱ (ዶ/ር) ጽሑፍ ጎን ለጎን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ለሕወሓት 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል በትግርኛ የተላከው የመልካም ምኞት መግለጫም፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥታቸው ሕወሓትን ለማቅረብና ከጎኑ ለማሠለፍ መከጀሉን እንደሚያሳይ ጠቅሳለች፡፡

በቀድሞው የሕወሓት ከፍተኛ አመራር በአቶ ስብሐት ነጋ በኩል የትግራይ ፖለቲካ ኃይሎችን ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለማቀራረብ ጥረት መቀጠሉ ሲነገር ቆይቷል፡፡ በሌላ በኩል የሕወሓት ጽሕፈት ቤትን ይዞ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ሲወዛገብ የቆየው የእነ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ቡድን፣ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት ስለመመሥረቱ በተደጋጋሚ ሲነገር ሰንብቷል፡፡ ኤርትራ ከትግራይ ፖለቲካ ኃይሎች ጋር ፈጠረችው ከሚባለው ግንኙነት በተጨማሪም፣ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ ኃይሎች ጋር በጋራ ስትሠራ ቆይታለች ሲባልም ነበር፡፡ ኤርትራ ለፋኖ ኃይሎች መጠለያ ብቻ ሳይሆን የሎጂስቲክስና የሥልጠና ድጋፍ ምንጭም ሆናለች ሲባል ከራርሟል፡፡

በውጭ በኩል ደግሞ ኤርትራ ከግብፅና ከሶማሊያ ጋር የሦስትዮሽ የአጋርነት ስምምነት በመፈራረም የጋራ ግንባር ስትፈጥር ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር አጀንዳን ይዛ ባለፈው ዓመት ብቅ ማለቷ ከኤርትራ እስከ ጂቡቲና ሶማሊያ ድረስ ያሉ አገሮችን ሥጋት ውስጥ መጣሉ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህ ዜና በረድ ሳይል ደግሞ በዓመቱ አጋማሽ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የባህር በር ስምምነት መፈራረሟ ከዋናዋ ሶማሊያ ጋር ከባድ ውጥረት ውስጥ እንዳስገባት ይታወሳል፡፡ ይህን አጋጣሚ ተገን በማድረግ ኤርትራ የካይሮና የሞቃዲሾ መንግሥታትን አሰባስባ ፀረ ኢትዮጵያ ግንባር መፍጠሯ ባለፉት ጥቂት ወራት በሰፊው ሲዘገብ ቆይቷል፡፡

ይህን ሁሉ የኃይል አሠላለፍ ባህሪ ከብዙ በጥቂቱ የጠቃቀሰው የሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ጽሑፍም፣ ነገሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ሥጋት መሆኑን በተዘዋዋሪ እንደሚጠቁም በርካቶች እየጠቀሱ ነው፡፡ በውስጥም በውጭም የተፈጠረውን የኃይል አሠላለፍ ለውጥ ለመበተንና አዲስ የራሱን አሠላለፍ ለመፍጠር የኢትዮጵያ መንግሥት ቢሞክር የሚፈረድበት አለመሆኑን ነው አስተያየት ሰጪዎች የሚገልጹት፡፡ ይህ ደግሞ በቀጣናው የአይቀሬ ጦርነት ዝግጅት መኖሩን ጠቋሚ ተብሏል፡፡    

ስለዚህ አሥጊ ቀጣናዊ ሁኔታ አስተያየት የተጠየቁት አንጋፋው የቀድሞ የሕወሓት ፖለቲከኛና አሁን የአረና ትግራይ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ገብሩ አሥራት፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥት ግንኙነት የተቀየረው ከፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ጀምሮ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ሁለቱም በትግራይ ለተፈጠረው ጥፋት የጋራ ግንባር የፈጠሩ ኃይሎች ናቸው፡፡ ሻዕቢያዎች ጦርነቱን ለመቀጠል ቢፈልጉም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የፕሪቶሪያን ስምምነት በመፈረም አሰናክሎባቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ትግራይን አዳክሞ ኢትዮጵያን በተፅዕኖ ሥር የመክተት ፍላጎታቸው አልተሳካም፡፡ አሁንም ይህን የቆየ ፍላጎታቸውን የገፉበት ሲሆን፣ ከፕሪቶሪያ በኋላ ከፋኖ ኃይሎች ጋር አጋርነት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከሕወሓት ኃይል ጋር ለመተባበር እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ሻዕቢያዎች የመንግሥቴን ሥልጣን ለማሳጣትና ለመገልበጥ ከፋኖም ከሕወሓትም ጋር እያበሩ ነው የሚለው ሥጋት በኢትዮጵያ በኩል መፈጠር ከጀመረ ከራርሟል፡፡ ይህ እያደገ የመጣ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የባህር በር ለማግኘት ያሳየው ፍላጎትም ቢሆን በተቃራኒው ለኤርትራና ለሌሎች ጎረቤት አገሮች የሚያስፈራ ነው፡፡ የባህር በር ፍላጎቱ እኔን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን የምንጋራው ቢሆንም ነገር ግን መነሻው ማለትም ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ፖለቲካዊ መነሻችን ምንድነው የሚለው ግልጽ ባለመሆኑ፣ ጉዳዩ ከፈጠረው ቀጣናዊ የዲፕሎማሲ ውዝግብ በስተቀር ለኢትዮጵያ መንግሥት ከውስጥም ከውጭም በቂ ድጋፍ አላስገኘለትም፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ፍላጎት የሚያስፈራቸው ሻዕቢያዎች ደግሞ ኢትዮጵያን ማዳከምና ከተቻለም የማፍረስ የቆየ ፍላጎት አላቸው፡፡ በዚህ የተነሳ በውጭም በውስጥም አጋርነት በመፍጠር የኢትዮጵያን መንግሥት ተፅዕኖ ውስጥ መክተት መፈለጋቸው የሚቀር አይመስልም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሻዕቢያዎች በቅርብ ጊዜ የፈጠሩትን ተፅዕኖ ለመቋቋም ጥረት ማድረግ ከጀመረም ከራርሟል፡፡ ለምሳሌ የኤርትራ ተቃዋሚ የሆነውን ብርጌድ ንሀመዱን በኢትዮጵያ እንዲደራጅና ስብሰባ እንዲያደርግ እስከ መፍቀድ ሲሄድም አይተናል፡፡ አሁን አፍጥጦ ወጥቶ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ጭምር ሲነገር ከመታዘባችን ውጪ፣ የሁለቱ አገሮች ውጥረት ከፕሪቶሪያ ጀምሮ የቀጠለና እየተባባሰ የመጣ ነው፤›› በማለት አቶ ገብሩ አብራርተዋል፡፡

በቅርብ ወራት ሁለቱ አገሮች የአቪዬሽን ግንኙነት ሲያቋርጡ መታየቱም የዚሁ የግንኙነት መሻከር ውጤት ሲባል ነበር፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ በኢትዮጵያ ኤርትራዊያን ስደተኞችን የማፈስ ዕርምጃ መጀመሩን በተፈናቃዮች ጉዳይ የሚሠሩ አንድ የመረጃ ምንጭ ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡ ብርጌድ ንሀመዱን እንዲደራጅ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቀደ ቢባልም፣ ነገር ግን ልክ እንደ ቀደመው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዘመን ሁሉ ኤርትራዊያንን እያፈሱ መላክ መጀመሩን ነው የመረጃ ምንጩ የተናገሩት፡፡   

ሰኞ ግንቦት 16 ቀን 1995 ዓ.ም. ነበር ኤርትራ ነፃ አገር ተብላ ከኢትዮጵያ ጋር በይፋ ፍቺ ፈጽማ ሉዓላዊ አገር ሆና የተመሠረተችው፡፡ ኤርትራ ለዚህ ቀን የበቃችው ደግሞ ብዙ አሥርታት ያስቆጠረ የግጭትና ጦርነት ውጣ ውረድ በሁለቱ አገሮች ውስጥ ከታለፈ በኋላ ነበር፡፡ የኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል ይህን የግጭት ታሪክ ለመዝጋት ወሳኝ ምዕራፍ እንደሚሆን በወቅቱ ታምኖበት ነበር፡፡ ሁለቱ በአንድነት መኖር ያቃታቸው አገሮች፣ መለያየታቸው ቢያንስ ጥሩ ጉርብትና መሥርተው ተከባብረው ለመኖር ያስችላቸዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበትም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የኤርትራ መገንጠልና ነፃ አገር መሆን በታሰበው ልክ ለሁለቱም አገሮች ሰላም የሰፈነበት ጉርብትናን አልፈጠረም፡፡   

ሚያዝያ 28 ቀን 1990 ዓ.ም. ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ስትፈጽም ሁለቱ አገሮች ወዳለፉበት የቀደመ የጦርነት ታሪክ ዞረው መመለሳቸው ዕውን ሆኗል፡፡ ይህ አጋጣሚ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት፣ እንዲሁም ከቬትናም ጦርነት ወዲህ ታላቁን የምሽግ ጦርነት በሁለቱ አገሮች መካከል አዋልዷል፡፡ በመቶ ሺዎች ሞተውና በርካታ ንብረት ወድሞ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውትወታ ሰኔ 11 ቀን 1992 ዓ.ም. የተኩስ አቁም ስምምነት ተደረገ፡፡ በዚህ ግጭት የማቆም ስምምነት መንገድ ጠራጊነትም ታኅሳስ 3 ቀን 1993 ዓ.ም. የአልጄርስ ሰላም ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል ተፈረመ፡፡

ሁለቱን አገሮች ወደ ግጭት ባስገባው የባድመና ሌሎች አወዛጋቢ ድንበር አካባቢዎች የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሰማራ፡፡ በስተመጨረሻ ሚያዝያ 5 ቀን 1994 ዓ.ም. የተመድ የድንበር ኮሚሽን የመጨረሻ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ የሁለቱ አገሮች ድንበር ይገባኛል የወለደው ግጭት ይግባኝ በሌለው የሄጉ ዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት ውሳኔ ዕልባት ማግኘቱም ተነገረ፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ በኋላም ኢትዮጵያና ኤርትራ ቀጥተኛ ጦርነት ባያደርጉም፣ በውጥረት የተሞላ ግንኙነት በመካከላቸው ሰፍኖ ነው የኖሩት፡፡ በድንበሮቻቸው መካከል ፈንጂ ቀብረውና መሣሪያ ወድረው ነው ዓመታት የተቆጠሩት፡፡ ከሶማሊያ እስከ ደቡብ ሱዳን በአፍሪካ ቀንድ ሲካሄዱ በቆዩ ግጭቶች ውስጥ የእጅ አዙር ግጭት በማድረግ ተጠምደውም ነው ለቀጣዮቹ 20 ዓመታት ያሳለፉት፡፡

ለዚህ ሁሉ የአስመራ ባለሥልጣናትን ዋና ተጠያቂ የሚያደርጉት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ገብሩ፣ ሻዕቢያዎች ከአቅማቸው በላይ ፍላጎት እንዳላቸው ነው የሚናገሩት፡፡ ይህ ደግሞ አሁንም ቢሆን መቀጠሉና ከኢትዮጵያ ጋር ለገቡበት ሽኩቻም መነሻ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡

‹‹ሻዕቢያዎች ከአፍሪካ ቀንድ ተሻግረው የመንና መካከለኛው ምሥራቅ ድረስ ተፅዕኖ ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይቷል፡፡ ለዚህ ፍላጎታቸው መሳካት ደግሞ በጂቡቲ፣ በሱዳን፣ በየመን፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳንም ሆነ በሌሎች አገሮች በቀጥታና በውክልና ጦርነት ማድረግን ቋሚ ሥራቸው አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት ጦርነትም ቢሆን የዚሁ ባህሪያቸው ውጤት ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን (ዶ/ር) መንግሥት ወደ ሥልጣን እንደመጣ መደገፍ የፈለጉት ለዚሁ ዕቅዳቸው ሲሉ ነው፡፡ በቀጣናው ተገዳዳሪያችን ነው የሚሉት ሕወሓትን ለማዳከምና ያለ ተቀናቃኝ በቀጣናው ተፅዕኖ ለመፍጠር ሲሉ እንጂ፣ ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ጉርብትናና ወዳጅነት ለመገንባት በሚል አልነበረም የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት አጋር ሆነው ብቅ ያሉት፡፡ የተቀደሰና ዘላቂ ግንኙነት ፈልገው ሳይሆን አካባቢውን እያተራመሱ በተፅዕኗቸው ሥር ማሳደርና ጥቅም ማስጠበቅ የሻዕቢያዎች ቋሚ ፍላጎት ነው፡፡ እንደ ማንም አገር የኢትዮጵያ መንግሥትም የራሱን ጥቅም ማስጠበቅ ይፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ በአገር ውስጥም በቀጣናውም ይህን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ እየገጠመው አይደለም፡፡ በትግራይ ገና የተረጋጋ ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልሎች ገና ግጭት አልበረደም፡፡ በውስጥ ከገባበት ጦርነትና የሰላም ዕጦት በተጨማሪ በውጭም ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ገጥመውታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኤርትራን ዋና ተጠያቂ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ ሻዕቢያንና በዙሪያው የተሠለፉ ኃይሎችን ለመቋቋም ትግል ማድረጉ ይጠበቃል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የአሁነኛው የሁለቱ መንግሥታት ውጥረት ደግሞ ቀጣናውን ለብዙ ችግር የሚዳርግ ጦርነት ሊያዋልድ እንደሚችል ነው አቶ ገብሩ የሚገምቱት፡፡ ‹‹ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያን ለሻዕቢያ ተፅዕኖና ለቀጣናዊ ውጥረት እየዳረጋት ያለው ውስጣዊ የሰላም ሁኔታዋ ነው፡፡ በኦሮሚያ ያለው ግጭት፣ በአማራ የሚካሄደው ጦርነትም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች በሰላም አለመፈታታቸው አገሪቱን ለውጭ ተፅዕኖ ተጋላጭ አድርጎታል፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አለመሆኑም ሌላው ያለመረጋጋት ምንጭ ነው፡፡ መንግሥት በውስጥ ችግሮቹን ሳይፈታ፣ የአገሪቱን አንድነትና ህልውና ሳያጠናክር፣ የቀይ ባህር ወይም የባህር በር ፖለቲካ ላይ በውጭ ልጠመድ ማለቱ ሌላ ውጥረት ከመፍጠሩ በቀር የሚሳካ አይመስልም፡፡ በእኔ ዕይታ ኢትዮጵያ የፖሊሲ ችግር ገጥሟታል፡፡ ይህ ደግሞ ለብዙ ጫናዎች ዳርጓታል፡፡ አካባቢውን እያተራመሰ ጥቅሙን ማስጠበቅ ለሚፈልገው የሻዕቢያ መንግሥት ይህ የኢትዮጵያ ተጋላጭነት ምቹ ሆኖለታል፤›› በማለት የሁለቱን አገሮች ወቅታዊ ውጥረት የሚገፉ ምክንያቶችን አብራርተዋል፡፡        

ኢትዮጵያና ኤርትራ ለ20 ዓመታት ውጥረት ከሰፈነበት ቆይታ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ነገሮች ተቀየሩ፡፡ የአዲስ አበባና የአስመራ ዕርቅ በሁለቱ አገሮች መሪዎች በለውጡ ሰሞን ዕውን ሲሆን ታየ፡፡ የሁለቱ አገሮች አወዛጋቢ ድንበሮች ዳግም ክፍት ሆኑ፡፡ ኢትዮጵያ በሄጉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የተወሰነውን ውሳኔ ያለቅድመ ሁኔታ እቀበላለሁ የሚል አቋም መያዟ፣ የአገሮቹን ግንኙነት እንደገና የቀየረ የመጀመሪያው አጋጣሚ ነበር፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) ወደ አስመራ በረው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ለመገናኘት የወሰዱት ዕርምጃ ደግሞ ደፋርና የዕርቁን በር ወለል አርጎ የከፈተ ነበር፡፡

የየብስ ትራንስፖርት በሁለቱ አገሮች ድንበር መካከል ከመጀመር ባለፈ የአየር በረራና የቴሌኮም ግንኙነትም ክፍት ሆኑ፡፡ በኤርትራ ወደብ መቀሌ የተባለችው የኢትዮጵያ መርከብ መልህቋን በጣለች ጊዜ ምፅዋ ላይ ዓብይ (ዶ/ር) ባሰሙት ንግግር፣ ‹‹ድህነትና የኢኮኖሚ ችግር ከቀጣናችን እስካልጠፋ ድረስ ኤርትራና ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ድንበር ተጋሪ አገሮች መካከል ግጭት ማገርሸቱ ይቀጥላል፡፡ ስለሆነም በሁለቱ አገሮች መካከል የተጀመረውን ዕርቅ በኢኮኖሚ ትስስርና በልማት ትብብር ማሳደግ ቀጣዩ የቤት ሥራችን መሆን አለበት፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ይህን ሲሉ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነቱ ተሠርቶ የተጠናቀቀና የቀረው ሥራ የኢኮኖሚ ትስስርን የማሳደግ ምዕራፍ ላይ የተደረሰ ይመስል ነበር፡፡

በአንድ ወቅት፣ ‹‹በኢትዮጵያ የመመዝገብ ልማድ ስለሌለን እንጂ በባድመ ጦርነት የሞተው ሕዝባችን ቀላል አይደለም›› ሲሉ የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ የሰላምን አስፈላጊነት በትልቁ አውስተው ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረገውን ጦርነት ወንድም ከወንድሙ የተደረገ መተላለቅ አድርገው ያስቀመጡት ሲሆን፣ ይህን መሰሉ ዕልቂት እንደማይደገም ተስፋቸውን ገልጸው ነበር፡፡

በጊዜው የሁለቱ አገሮች ዕርቅና ዳግም ወዳጅነት ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ መርህ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ይመሥረት የሚለው የአንዳንድ ወገኖች ውትወታ የጎላ የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን ከዚያ ይልቅ ሌሎች ነገሮች ሲቀድሙ ነበር የታየው፡፡ ሁለቱ አገሮች የሚወዛገቡበትን የድንበር መሬት ጉዳይ ሳያሰምሩና ችካል ሳይቸክሉ የሶማሊያ መሪ መሐመድ ፋርማጆን ያቀፈ የአፍሪካ ቀንድ አጋርነት ወደ መፍጠር አመሩ፡፡ በሁለቱ አገሮች ውስጥ የተጠለሉ ስደተኞችም ሆነ የታጠቁ ኃይሎች ጉዳይ ዕልባት ሳያገኝ በኤሌክትሪክና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ስለመተሳሰር ነበር ይወራ የነበረው፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ በሁለቱ አገሮች መሪዎች የተፈረመው ስምምነት ውስንና ጥቅል ጉዳዮችን የያዘ ነበር፡፡ የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በቀጣይ በሚደረጉ ድርድሮችና ስምምነቶች የተሻለ መስመር እንዲይዝም ይህ መሠረት ይጥላል ተብሎ ነበር፡፡ የተፈጠረውን መልካም የዕርቅ አጋጣሚ በመጠቀም እንደገና ግጭት ለመፍጠር ቀዳዳ የማይተው መልክ ያለው ጉርብትናና ወዳጅነት፣ አገሮቹ ለመመሥረት የሚያስችል ዝርዝር ዕቅድና ገቢር እንደሚፈጠር ብዙ ተጠብቆ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በብዙዎች እምነት ይህ ባለመደረጉ የተነሳ፣ አጋጣሚው በታሰበው ልክ የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ሳይሆን ቀርቷል፡፡

ይህ ሳይሆን ደግሞ የትግራይ ጦርነት ፈነዳ፡፡ የኤርትራ ወደ ጦርነቱ መግባት ብዙ ውዝግብ አስነሳ፡፡ ጦርነቱን ለማስቆም የተደረገው የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ደግሞ ኤርትራንና ሌሎች የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎችን ያላካተተ ነበር ይባላል፡፡ በዚህ የተነሳ ዛሬም ድረስ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በውጥረት የተሞላ እንዲሆን መንገድ መፍጠሩ ይጠቀሳል፡፡ ይህ ደግሞ ቀጣናውን ጭምር ለውጥረት መዳረጉ ነው የሚነገረው፡፡

ትንሽም ቢሆን ውጊያ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል የሚሉት አቶ ገብሩ፣ መገዳደልና ሕይወት ማጥፋት ካለ የሚያመጣው አሉታዊ ውጤት ቀላል አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ጦርነት ደጋፊ አይደለሁም ሁሉም ነገር በሰላም፣ በዲፕሎማሲና በድርድር ነው መፈታት ያለበት እላለሁ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የትግራይ ጦር መካከለኛ የጦር መኮንኖች አንድ የፖለቲካ ቡድንን ወግነው አቋም ከያዙ ወዲህ በትግራይ ከፍተኛ ሥጋት ተፈጥሯል፡፡ እንደገና ጦርነት ሊቀሰቀስ ነው የሚል ሥጋት በመፈጠሩ የተነቃቃው ንግድና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ መልሶ እንዲቀዘቅዝ አድርጎታል፡፡ ሰዎች መሰደድ ጀምረዋል፣ ገበያው ቀዝቅዟል፣ ግንባታውና ኢንቨስትመንቱም ቆሟል፡፡ እንኳን ጦርነት ተቀስቅሶ አይደለም የጦርነት ሥጋትም መፈጠሩ ራሱ ብዙ ጉዳት ነው የሚያመጣው፡፡ በጦርነት ቀጣና ደግሞ ንግድና ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን እንቅስቃሴና ሕይወት አይኖርም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የቀጣናው የኃይል አሠላለፍ ተለውጧል፡፡ ከውጭ ብዙ ያሰፈሰፉ ኃይሎች አሉ፡፡ ከውስጥም የሰከነ ሁኔታ የለም፡፡ በመሆኑንም በየትኛውም አካባቢ አዲስ ጦርነት የሚጀመር ከሆነ ለሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚተርፍ ውጤት ነው የሚኖረው፡፡ አፍሪካ ቀንድ በችግር ላይ ነው፡፡ ከዚህ የባሰ ችግር እንዳይከሰት ጦርነቱን ማስቆም ነው የሚበጀው፡፡ ደግሞም ይህ ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ጦርነት ገና ለገና መከሰቱ አይቀርምና ብሎ ወደ ጦርነት የሚገፋፋ ዕርምጃ ማድረግ ለኤርትራም፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሁሉም ወገን አይበጅም፡፡ እንኳን ጦርነት ውስጥ ተገብቶ አሁን ያለንበት ሁኔታም ቢሆን ብዙ ተፅዕኖና ችግር ያለው ነው፤›› በማለት ነው ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት፡፡