አስተያየት

By አንባቢ

February 23, 2025

በያሬድ በርሔ

አንዳንድ ወዳጆቼ ጥላሁን ግዛው ጓደኛህ ነበር፡፡ ‹‹ለምን ስለእሱ ትንሽ ነገር በጽሑፍ አታቀርብም›› እያሉ በየጊዜው ያሳስቡኛል፡፡ እኔም ማሳሰቢያው አግባብነት ያለው መሆኑን ተገንዝቤ ስለጥላሁን የማውቀውን፣ እንዲሁም ጥላሁን ይነግረኝ የነበረውን መሠረት አድርጌ ይህችን ትንሽ ጽሑፍ አቅርቤያለሁ፡፡

ጥላሁን ግዛው ማን ነው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር (ኡዙዋ) ፕሬዚዳንት የነበረው ጥላሁን ግዛው

ጥላሁን ትሁትና ሀቀኛ ሰው ነበር፡፡ ጥላሁን ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት የሚታገል ሰው ነበር፡፡ ጨቋኑ መስፍናዊ ሥርዓት በሕዝባዊ ሥርዓት መተካት አለበት የሚል እምነት ነበረው፡፡ ለሕዝባዊ ሥርዓት መመሥረትም ሕዝቡን የሚያነሳሳ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረ ሰው ነው፡፡ እኔና ጥላሁን የተዋወቅነውና ጓደኝነትም የመሠረትነው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት (ኮተቤ) እኔ የተማሪዎች ሄድ ቦይ፣ ጥላሁን ደግሞ ከፕሪፌክቶች አንዱ ሆኖ በተመረጥንበት ጊዜ ነው፡፡ ኮተቤ ከእነ ገርማሜ ንዋይ ጀምሮ ለሕዝቦች ነፃነት የሚታገሉ ተማሪዎች የሚፈልቁበት ትምህርት ቤት ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ኮተቤ ተቀስቅሶ በነበረው ረብሻ ምክንያት ፖሊሶች የኮተቤ ተማሪዎችን አፍሰው ወደ ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ማሠልጠኛ ወሰዱን፡፡ እዚያም ሁለት ሳምንታት ለሚሆን ጊዜ ከጥዋቱ በአሥራ አንድ ሰዓት እያስነሱ ከባድ ጅምናስቲክ ያሠሩን ነበር፡፡ ጭቃም ያለ ዕረፍት እንድናቦካ ያደርጉን ነበር፡፡ ስለረብሻውና ስለረብሻው መሪዎች ማንነትም በተናጠል እየወሰዱን ቃለ መጠይቅ ያደርጉልን ነበር፡፡ በዚህ መሀል ጥላሁን እንዲለቀቅ የሚል ትዕዛዝ ከበላይ ይመጣል፡፡ የማሠልጠኛው ኃላፊም ጥላሁንን ልብሱንና ፍራሹን ይዞ እንዲወጣ ነገሩት፡፡ ጥላሁንም እኔ ከጓደኞቼ ተለይቼ አልወጣም፣ ከለቀቃችሁን ሁላችንንም ልቀቁን በማለት ዕንቢ ብሏቸው ሳይለቀቅ ቀርቷል፡፡

ቤልጅያውያን በቅኝ ግዛት ይዘውት በነበረው ኮንጎ ብዙ ሰዎች በግፍ ስለገደሉ ይህንን ድርጊት በመቃወም በሠልፍ ከኮተቤ ተነስተን ወደ ቤልጂየም ኤምባሲና ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ሄድን፡፡ በጊዜው የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ሚስተር ኮሪ የተባሉ በታኅሣሥ 1953 ዓ.ም. በክብር ዘበኛ ሠራዊት መሪ በጄኔራል መንግሥቱ ንዋይና በተራማጁ ወንድማቸው በአቶ ገርማሜ ንዋይ በተመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ትልቅ ሚና የተጫወቱ ሰው ወደ ኤምባሲው ቅጥር ግቢ እንድንገባ ፈቅደው ለምን ወደ ኤምባሲው እንደመጣን ጠየቁን፡፡ በዚህ ጊዜ ጥላሁን በቤልጅያን ኮንጎ የቅኝ ገዥ የሆኑት ቤልጂየሞች በቅርብ ቀናት በአሜሪካ ኢምፐርያሊዝም ተባባሪነት በኮንጎ ሕዝብ ላይ ለፈጸሙት ጭፍጫፋ ተቃውሟችንን ለመግለጽ መምጣታችንን በእንግሊዝኛ ሰፋ ያለ ንግግር በማድረግ ገለጸላቸው፡፡ አምባሳደር ኮሪም ንግግሩን በጥሞና ካዳመጡ በኋላ በተፈጸመው ድርጊት ማዘናቸውንና ጉዳዩን ሁሉ ተከታትለው አስፈላጊውን እንደሚፈጽሙ ከነገሩን በኋላ፣ ‹‹ጥላሁንን ስምህ ማነው?›› ብለው ጠየቁት፡፡ ጥላሁንም ስሙን ነገራቸው፡፡ እሳቸውም፣ ‹‹ከዚህ በፊት ያየሁህ ይመስለኛል፤›› አሉት፡፡ ጥላሁንም ‹‹አይመስለኝም›› ሲል መለሰላቸው፡፡ በወቅቱ ሁላችንም ሠልፈኞች ጥላሁን ባደረገው ጥሩ ንግግር ተደስተን ግባችንን አሳክተን ተመለስን፡፡

እኔ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቅቄ፣ በ1958 ዓ.ም. ዩኒቨርሲቲ ገባሁ፡፡ ጥላሁን ደግሞ በ1959 ዓ.ም. ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡ በ1959 ዓ.ም. እኔ፣ ጥላሁንና ሁለት ጓደኞቼ የነበሩ ኃይለ ተክሌ የተባለ ኤርትራዊ ከኮተቤ በ1957 ዓ.ም. ዩኒቨርሲቲ የገባ (በአሜሪካ አገር በፕሮፌሰርነት በዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ የሚገኝ) እና በላይ በርሄ የተባለ በ1958 ዓ.ም. ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የገባ (አሁን በሕይወት የሌለ) አራታችንም አምስት ኪሎ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሁለት ክፍል ቤት ተከራይተን አብረን እንኖር ነበር፡፡ ኃይሌና ጥላሁን በአንዱ ክፍል ይተኙ ነበር፡፡ ሁለቱ እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ እያነበቡ በመሃሉ ይከራከሩ ነበር፡፡ በሌላው ክፍል እንተኛ የነበርነው እኔና በላይ በመሃሉ በክርክራቸው ብንን እያልን ‹‹እስካሁን አልተኛችሁም?›› እንላቸው ነበር፡፡ ኃይሌ ተክሌ ከሳይንስ ፋኩልቲ በወርቅ ሜዳሊያ የተመረቀ ብልህ ተማሪ ነበር፡፡

በ1960 ዓ.ም. እኔ የሕግ ተማሪ ጥላሁን ደግሞ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ ሆኖ፣ ከእኔ ጋር ሕግ ይማሩ ከነበሩት ከተኮላ ሐጎስ (አሁን አሜሪካ አገር በፕሮፌሰርነት ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ የሚገኝ) እና ከዝናቡ (የአባቱን ስም የዘነጋሁት ትምህርቱን አቋርጦ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሕግ ክፍል ተቀጥሮ ከባንኩ የሠራተኛ ማኅበር መሪዎች አንዱ የነበረ አሁን በሕይወት የሌለ) አራታችን በስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ በእደ ማርያም ትምህርት ቤት ጀርባ በሚገኝ ሁለት ክፍል ቤት ተከራይተን እንኖር ነበር፡፡ ተኮላ ድንቅ ሥዕል ሠዓሊ ስለነበረ ከእኛ ጋር እየኖረ ሥዕል ይሥል ነበር፡፡ ይሥለው የነበረው ሥዕል ሽማግሌ ሰውዬ በገና ይዘው፣ ‹‹ተው ስማኝ አገሬ›› እያሉ እንደሚዘምሩ የሚያሳይ ሥዕል ነበር፡፡ ይህ ሥዕል ጥላሁንን በጣም ይስበውና ያስተክዘው ነበር፡፡ የተኮላ የሽማግሌውን ሰው ሥዕል የኢትዮጵያ ሼል ኩባንያ ገዝቶት በዘመን መቁጠሪያ አውጥቶት ነበር፡፡

ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥላሁን ዕለተ ሞት ድረስ እኔና ጥላሁን እንኖር የነበረው ከዩኒቨርሲቲው በስተምዕራብ በኩል ባለው ትልቅ በር መኪና መንገድ ተሻግሮ በተለምዶ አባ ሃና ወፍጮ ተብሎ ከሚጠራው ግቢ ከፍ ብሎ በሚገኝ ግቢ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ከዚሁ ግቢ ፊት ለፊታችን ፋሲካ ሲደልል የተባለ የኢኮኖሚክስ ተማሪ (በደርግ መንግሥት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር) ከጓደኛው ጋር ይኖር ነበር፡፡ በዚህ ግቢ በምንኖርበት ወቅት የጥላሁን እናት ከሁለት ልጆቻቸው ከመኰንንና ከሰብለ ጋር መጥተው አንድ ወር ያህል ቆይተው ወደ አገራቸው ወደ ቃሊም ሲመለሱ፣ መኰንንና ሰብለ ከእኛ ጋር ይኖሩ ነበር፡፡ ጥላሁን አባቱ የትግራይ ተወላጅ ሲሆኑ እናቱ ደግሞ የጎንደርና የላስታ ተወላጅ ናቸው፡፡ ጥላሁን በዩኒቨርሲቲው በሚማርበት ዘመን በዩኒቨርሲቲው ፀረ ፊውዳላዊው ሥርዓት እንቅስቃሴዎች ተፋፍመው ነበር፡፡ በመሠረቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የፀረ ፊውዳል ሥርዓት እንቅስቃሴ ማካሄድ የጀመሩት በዋናነት ከታኅሣሥ 1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ነበር፡፡ በእንቅስቃሴውም ትልቅ ሚና የነበራቸው በዩኒቨርሲቲው በህቡዕ ተደራጅተው ውስጥ ለውስጥ ይንቀሳቀሱ የነበሩት፣ ‹‹ኮሮኮዳይል ግሩፕ›› ይባሉ የነበሩት ማርክሲስት ተማሪዎች ናቸው፡፡ አባላቱም ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ ገብሩ ገብረ ወልድ፣ ዘርኡ ክህሽን፣ ተካልኝ ወልደ አማኑኤል፣ ወዘተ እንደነበሩ ይገመታል፡፡ አብዛኛዎቹ አባላት በዩኒቨርሲቲ ስምንትም ዘጠኝም ዓመት ቆይተዋል፡፡ ከግሩፑም መሃል ብርሃነ መስቀል ረዳ አንደበተ ርቱዕ፣ ቀስቃሽና አዋቂ ሰው ነበር (በደርግ የተገደለ)፡፡ ተማሪዎቹ በበለጠ አኳኋን እንቅስቃሴያቸውን ያጠናከሩት ግን ‹‹ኡዙዋ›› ተብሎ ይጠራ የነበረው የተማሪዎች ማኅበር በ1959 ዓ.ም. ከተቋቋመ በኋላ ነው፡፡ የመሬት ለአራሹ፣ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ እኩልነት፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች፣ ወዘተ ጎልተው የወጡት ከኡዙዋ መቋቋም በኋላ ነው፡፡ በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያም ሕዝቡን ለመቀስቀስ፣ ሰላማዊ ሠልፎች ይካሄዱ ነበር፡፡ በዘመኑ በኤርትራና በባሌ ይካሄዱ የነበሩ የትጥቅ ትግሎች፣ ዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት ተማሪዎች አገርን ለማገልገል (ናሽናል ሰርቪስ) በሚል ፕሮግራም ለአንድ ዓመት ጊዜ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እየተመደቡ በሚያስተምሩበት ወቅት የተገነዘቧቸው የሕዝብ ብሶቶች፣ እንዲሁም በዓለም በተለያዩ አገሮች በተራማጆች ለሕዝቦች ነፃነትና ለሶሻሊዝም ሥርዓት ግንባታ ሲካሄዱ የነበሩት ትግሎች ከፍ ብለው ለተጠቀሱት ጥያቄዎች ትግል መጉላት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የተማሪዎች የማርክስ፣ የሌኒን፣ የስታሊንና የማኦሴቱንግ የመሳሰሉ አብዮታውያን መጻሕፍት ማንበብም ንቃታቸውን አዳብረዋል፣ ትግላቸውንም አጠንክረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የተወሰኑ ተማሪዎች የብሔር ጥያቄ ማንሳት ‹‹ከባቢያዊነት›› (ሪጅናሊዝም) ነው፡፡ ‹‹ጎሰኝነት›› (ትራይባሊዝም) ነው እያሉ የሚያጣጥሉ ነበሩ፡፡ በዚህ ሁሉ የዘመኑ ድባብ ውስጥ ሆኖ ነው እንግዲህ ዋለልኝ መኰንን የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ የሚመለከት ጽሑፉ የጻፈው፡፡ ዋለልኝ የክፍሉ ልጅ የፖለቲካል ሣይንስ ተማሪ የነበረ ብልህና ተራማጅ የሆነ ነጋ አየለ የሚባል ጓደኛ ነበረው (የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ የነበረና የኢሕአፓ አባል ስለነበረ በደርግ የተገደለ)፡፡ የብሔር ጥያቄን የተመለከተ ጽሑፍ በጊዜው በዋለልኝ ይጻፍ እንጂ፣ ስለብሔር ጥያቄ ሆነ ስለሌሎች አገር አቀፍ አንገብጋቢ ጥያቄዎችና የአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ሆኖ ማኅበራዊ መዋቅራዊ ችግሮችን በተመለከተ ብዙ ሊተነተኑና ሊጻፉ የሚችሉ የኮሮኮዳይል ግሩፕ አባላትና ሌሎችም ተራማጅ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ነበሩ፡፡

በ1961 ዓ.ም. ጥላሁን በዩኒቨርሲቲው የሦስተኛ ዓመት የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ኡዙዋ ተብሎ ይጠራ ለነበረው የተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትነት መኰንን ቢሻው ከሚባል ትምህርቱን ፈረንሣይ አገር አጠናቆ መጥቶ ለሌላ ዲግሪ ዩኒቨርሲቲ ይማር ከነበረ ተማሪ ጋር ተወዳደረ፡፡ በምረጡኝ ካምፓየን ስሙን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ጥላሁን እንዳይመረጥ ለማድረግ ብዙ ነገር ይወራም፣ ይደረግም ነበር፡፡ በስድስት ኪሎ ቅጥር ግቢ ባሉ ዛፎች ግንድ ላይ ‹‹ንጥላሁን ምረፁ›› (ጥላሁንን ምረጡ) የሚል በትግርኛ የተጻፈ ጽሑፉ ይለጠፍ ነበር፡፡ ውስጥ ለውስጥ የሚናፈሰው ወሬ ደግሞ የትግሬዎች ምኞች የአክሱም መንግሥትን ለመመሥረት ስለሆነ መሣሪያ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን፣ ወዘተ የሚል ነበር፡፡ በራስ መኰንን አዳራሽ በተደረገው የምረጡኝ ንግግር ጥያቄና መልስ ወቅትም ጥላሁን እንዳይመረጥ ተደራጅተው የገቡ ተማሪዎች ይጠይቁት የነበረው ‹‹አባትህ ደጃዝማች፣ እህትህ ልዕልት፣ እንዴት እናምንሃለን፣ ለጭቁኖች እታገላለሁ ስትል?›› ‹‹አባትህ ሞተዋል የወረስከውን መሬት ለድሆች ገባሮች አከፋፈልክ ወይ?›› በማለት ነበር፡፡ ጥላሁንም ጊዜ መስተዋት ነው፡፡ ለጭቁኖች አርነት የምታገል መሆኑን ጊዜ ያሳያችኋል ሲል ይመልስላቸው ነበር፡፡ በምርጫው ውድድርም መኰንን ቢሻው አሸነፈ፡፡

ጥላሁን በኢትዮጵያ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ሕዝቡን የማንቃት እንቅስቃሴ መጎልበት እንዳለበትና መድረኩም ዩኒቨርሲቲው መሆኑን ያምን ስለነበር በሚቀጥለው ዓመት 1962 ዓ.ም. ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር እንዲችል ትምህርቱን አቋረጠ፡፡ ቤትም እየዋለ የተለያዩ አገሮች አብዮቶች የሚመለከቱ መጻሕፍትን በጥልቀት ያነብ ነበር፡፡ ገብሩ ገብረ ወልድ የተባለ የኮሮኮዳይል ግሩፕ አባል (አሁን አሜሪካ አገር የሚኖር) ወዳጁ ስለነበር ስድስት ትልልቅ መጻሕፍት ማለትም ሦስት የካርል ማርክስ ሥራዎች፣ ሦስት ደግሞ የሌኒን ሥራዎችን ያጠቃለሉ መጻሕፍት አምጥቶ እንዲያነባቸው ሰጠው፡፡ ጥላሁን እንዳረፈም ስድስቱ ትልልቅ መጻሕፍት የገብሩ ገብረ ወልድ መሆናቸውን ለጥጋቡ ግዛው (በሕይወት አለ፡፡ የጥላሁን የአባት ልጅ ነው) ነግሬ ለገብሩ አሰጥቼዋለሁ፡፡ ጥላሁን አባቱ እንደሞተ ከወረሳቸው ንብረቶች መካከል ሦስት መትረየሶች፣ አንድ የጦር ሜዳ መነፀር፣ አንድ ኮልት ሽጉጥ (ሁልጊዜ የሚታጠቀው የነበረ) እና አንድ ወርቅ ሰዓት ነበሩ፡፡ መትረየሶቹንና የጦር ሜዳ መነፅሩን በልብስ ቁምሳጥን የግርጌ ክፍል፣ ገልብጠህ ካልሆነ ሊከፈት የማይችል ውስጥ አስቀምጦት ነበር፡፡ የምናውቀው እኔና እሱ ብቻ ነበርን መሣሪያዎቹን ሊያካሄደው ያስብው ለነበረው የትጥቅ ትግል ለመጠቀም ያስቀመጣቸው ነበሩ፡፡ በዕረፍት ጊዜም አባቱ አገር ማይጨው ደርሶ ይመጣ ነበር፡፡

በ1962 ዓ.ም. ጥላሁን ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሶ የሦስተኛ ዓመት ትምህርቱን መከታተል ጀመረ፡፡ ለተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትነትም ዕጩ ሆኖ በመቅረብ ተወዳደረ፡፡ በራስ መኰንን አዳራሽ የምረጡኝ ንግግር በሚያደርግበትም ሰዓት አስቀድሜ ሳላሳውቀው አዘጋጅቼው የነበረውን ጉንጉን አበባ ስቴጅ ላይ ወጥቼ በአንገቱ አጠለቅኩለት፡፡ በውድድሩም ጥላሁን አሸንፎ የተማሪዎች ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ፡፡ እንደተመረጠም የተማሪዎቹን ፀረ ፊውዳል እንቅስቃሴ ለማፋፋም በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ሥነ ሐሳብ የነቁ አባላትን ለመፍጠር የተለያዩ የጥናት ቡድኖችን ያቋቁም ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ የሰከንደሪ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ማኅበራት ከዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ማኅበር ጋር ግንኙነት እንዲመሠርቱም ይጥር ነበር፡፡ በ1962 ዓ.ም. መጀመሪያ ዓመት ላይ በጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት በተማሪዎች መካከል ተነስቶ በነበረው የብሔር ግጭት ጥላሁን ከኡዙዋ አመራር አባላት ጋር ወደ ትምህርት ቤቱ ሄዶ ተማሪዎቹን በማነጋገር ዕርቅ እንዲፈጠር ጥሯል፡፡ ይህም ያደረገው የተማሪዎችን አንድነት ለማጠናከር በማሰብ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ ጥላሁን በኢትዮጵያ በየአካባቢው በሥርዓቱ በሕዝቦች ላይ ይፈጸሙ የነበሩ ጭፍጨፋዎችን ይኮንንና ያጋልጥ ነበር፡፡ መንግሥትም እንቅስቃሴውን ይከታተል ስለነበር ሥጋት ስላደረበት ጥላሁን በምስጢር ወደ ጃንሆይ እንዲቀርብ ተደረገ፡፡ ጃንሆይም፣ ‹‹የልጃችን የደጃዝማች ግዛው ልጅ ነህ፡፡ ለምንድነው የምትርቀን?›› ብለው ካነጋገሩት በኋላ፣ ምን እንድናደርግልህ ትፈልጋለህ? ሐሳብህ ምንድነው? ብለው ጠየቁት፡፡ ጥላሁንም ሐሳቤ አባቴ አገር ማይጨው ሄጄ የእርሻ ሥራ ለመሥራት ነው አላቸው፡፡ ጃንሆይም እኛ እንረዳሃለን ልዑል መንገሻም እንዲተባበርህ እንነግረዋለን ብለው አሰናበቱት፡፡ ጥላሁን በሚያውቀው አካባቢ የሚያውቃቸው ሰዎች ባሉበት ማይጨው በረሃማ ቦታ የትጥቅ ትግል ለመጀመር ያስብ ስለነበር ለወደፊቱ እዚያ እንቅስቃሴ ሲጀምር እንዳይተናኮሉት በማሰብ ይመስለኛል ማይጨው ሄጄ የእርሻ ሥራ ለመሥራት አስባለሁ ያላቸው፡፡

ጥላሁን ከጃንሆይ ጋር ከተገናኘ በኋላ ፀረ ሥርዓቱ እንቅስቃሴውን አላቆመም፡፡ የምዕራብ ጀርመን የአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኞች ጥላሁንን ተገናኙት፡፡ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ግራ ዘመም የተማሪዎች አንቅስቃሴ በጣም ገናና ነው፡፡ ስለእንቅስቃሴውና ዓላማችሁ ፊልም እየቀረፅን ኢንተርቪው ለማድረግ እንፈልጋለን፡፡ የምትሰጠን ኢንተርቪው ኢትዮጵያ ውስጥ ለማንም አንገልጽም ብለው ቃል ገብተው ኢንተርቪውን አደረጉ፡፡ ጥላሁን የማርክሲዝም ሌኒንዝም ሥነ ሐሳብ እንዲያጠኑ ውስጥ ለውስጥ ላቋቋማቸው ዋህዮዎች  ለጥናት የሚሆኑ ጽሑፎች ማባዣ ዱፕሊኬቲንግ ማሽንና ወረቀቶች፣ መግዣ ለማኅበሩም ሥራዎች ገንዘብ አስፈለገው፡፡ ጉዳዩንም ለማኅበሩ አመራር ኮሚቴ አቀረበው፡፡ ኮሚቴውም ለተባለው ጉዳይ ገንዘብ በቋሚነት ሊገኝ ስለሚችልበት ሁኔታ ከተወያየ በኋላ በስድስት ኪሎ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙት ሁለት ቡና ቤቶች በማኅበሩ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉና ማኅበሩ እንዲያካሄዳቸው ወሰነ፡፡ አንድ ቀን ጠዋት ሕግ ፋኩልቲ ቀጠሮ ስለነበረኝ በጥዋት ተነስቼ ለመሄድ ስነሳ ጥላሁን እኔም ከአንተ ጋር እሄዳለሁ ብሎ ስለቡና ቤቶቹ የወሰኑትን ነግሮኝ ከእኔ ጋር ሄደ፡፡ ሕግ ፋኩልቲ እንደደረስንም ፊት ለፊት ሕግ ፋኩልቲ የነበረውን ቡና ቤት (ተቆልፎ የነበረ) ይዞት ከነበረው ሁለት ቁልፍ በአንዱ እኔ ፊት ቆለፈው፡፡ ከዚያም እግር ኳስ ሜዳ አጠገብ የነበረውን ቡና ቤት ለመቆለፍ ብቻውን ሄደ፡፡ ከዚያ በኋላ ምን እንደሆነ ጥላሁን የነገረኝ ነገር የለም፡፡ ከሌላ ሰውም የሰማሁት ነገር የለም፡፡ አንድ ቀን ግን እህቱ ልዕልት ሳራ ግዛው ወደ ቤታቸው አስጠርተው አንተ ልጅ እረፍ ጃንሆይ በመንግሥታቸው የሚመጣባቸው ከሆነ ልጃቸውንም አይምሩም ብለው መክረውታል፡፡ እህቱ ጠርተው ከመከሩት በላይ ብዙም ሳይቆይ መኖሪያ ቤታችን ስትጫወት የቆየችውን ሴት ጓደኛውን ከወንድሙ ከመኰንን ጋር ሆነው ሲሸኟት አፍንጮ በር ተብሎ በሚጠራው ከአባ ሃና ወፍጮ ዝቅ ብሎ በሚገኝ መስቀለኛ መንገድ ላይ የመንግሥት ወታደሮች ደጋግመው በመተኮስ ገደሉት፡፡ በዕለቱ እኔ እንደ አጋጣሚ አዲሱ ቄራ ወንድሜ ቤት ሄጄ ነበር፡፡ ከጥዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት አካባቢ ማን እንደሆነ ያላወቅኩት ሰው ጥላሁን ተገደለ ብሎ እያለቀሰ በስልክ ነገረኝ፡፡ ወዲያው ወደ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ሄድኩኝ፡፡ ግቢው በዩኒቨርሲቲና በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ተጠለቅልቆ ነበር፡፡ መንግሥት ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ የክብር ዘበኛ ወታደሮችን አስገብቶ ሬሳው ማይጨው ሄዶ እንዲቀበር ወደ ማይጨው እወስዳለሁ ሲል ተማሪዎቹም ሬሳውን አትወስዱም ሲሉ ግቢው በተኮስ ተናደ፡፡ በተኩሱም ሦስት ተማሪዎች ተገደሉ፣ ብዙዎቹ ቆሰሉ፡፡ በዕለቱ ዋለልኝ መኰንን በአርትስ ፋኩልቲ ሕንፃ ሦስተኛ ፎቅ ላይ ሆኖ በመስኮት ድምፅ ማጉያ ይዞ ጥላሁንን መንግሥት እንደገደለው፣ ሬሳው በወታደሮች መወሰድ እንደሌለበት፣ ጥላሁን ቢሞት የቆመለት ዓላማ እንደማይሞት፣ ወዘተ  በመግለጽ በዚያ ተኩስ መሃል ለትግል የሚያነሳሳ ንግግር ያደርግ ነበር፡፡ በተኩሱም መሃል የጥላሁን ሬሳ በቤተሰቦቹና በወታደሮች ታጅቦ ወደ ማይጨው ተወስዶ እዚያ ተቀበረ፡፡ የጥላሁን ረዥም ህልም በአጭር ተቀጨ፡፡ የቆመለት ሕዝባዊ ዓላማ ግን ተቀጣጠለ፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡