February 23, 2025

ሦስት ዓመታት ሊሞሉት ትንሽ የቀረው በሱዳን ብሔራዊ ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት 12 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ማፈናቀሉን፣ የአፍሪካ ኅብረትና የዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ በቅርቡ አስታውቀዋል፡፡ የጦርነቱ የአስከፊነት ሁኔታ አሁንም ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎቱ በዚያው ልክ እየጨመረ መምጣቱን የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2024 ብቻ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ለሕክምና ሆስፒታል የገቡ ሕፃናት በ44 በመቶ መጨመራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የሕክምና ዕርዳታ የተደረገላቸው ሕፃናት ከ431 ሺሕ በላይ መድረሱም ተጠቁሟል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከተጠናቀቀው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደረጉት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልማትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ምክትል ሚኒስትር ሡልጣን አልሻምሲ፣ አገራቸው በሱዳን እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት የሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊን ጨምሮ የተለያዩ መሪዎች በተገኙበት፣ የ200 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ይፋ አድርገዋል፡፡ ሲሳይ ሳህሉ ከምክትል ሚኒስትሩ ጋር ያደረገው አጭር ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡– የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በጦርነት ውስጥ ላለችው ሱዳን ድጋፍ ለሚያስፍልጋቸው ወገኖች ስላቀረበችው የ200 ሚሊዮን ዶላር ሰብዓዊ ዕርዳታ ቢያስረዱን?
አልሻምሲ፡- የሰብዓዊ ዕርዳታውን አቅርቦት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳፋቂ [የሥልጣን ዘመናቸው ተጠናቋል] ማሃማትና ሌሎችም እንግዶች በተገኙበት ይፋ አድርገናል፡፡ ከድጋፉ ባሻገር የረመዳን ፆም እየተቃረበ ባለበት በዚህ ወቅት ቅዱስ የሆነውን ወር ዜጎች በሰላም መንቀሳቀስ እንዲችሉና ማኅበራዊ ሕይወትን እንዲያጣጥሙ፣ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ግፊት የምናደርግበት በጣም ወሳኛና አስፈላጊ ወቅት ነው፡፡ በዚህ የረመዳን ወቅት የሚደረግ የተኩስ አቁም ስምምነት ካየን በኋላ፣ ጊዜያዊ ተኩስ አቁሙ ፀንቶ ተፋላሚ ወገኖች እንደገና ወደ ግጭት እንዳይመለሱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ጦርነቱ ከተከሰተ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ጦርነት እየተጎዱ ያሉት ሱዳናውያን ብቻ ሳይሆኑ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃይ ሱዳናውያንን እየተቀበሉና እያስተናገዱ ያሉት የጎረቤት አገሮች ቻድ፣ ደቡብ ሱዳንና ኡጋንዳ የመሳሰሉ አገሮች ጭምር ናቸው፡፡ እነዚህ አገሮች ይህን ሰብዓዊ የሆነ ተግባር በማድረጋቸው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ታመሠግናለች፡፡
በተለይም ይህን ትልቅ ኃላፊነት ወስደው በሮቻቸውን ከፍተው ወደ ድንበሮቻቸው አስገብተው ማስተናገድ በመቻላቸው ሊመሠገኑ ይገባል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ለሱዳን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ድጋፍ የማፈላለጊያ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ ባለፈ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በአፍሪካ ያላትን ቁርጠኛ ወዳጅነት ለመደገፍ ይህንን ገንዘብ ይፋ አድርጋለች፡፡ በርካቶች በሞቱበት የሱዳን ጦርነት ለተወሰነ ጊዜ የተኩስ አቁም ተደርጎ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው፣ በተለይም ለሴቶችና ለሕፃናት ድጋፉን ማድረስ የሚቻልበት ዕድል እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ አሁን የረመዳን ፆም ወቅት በመሆኑ እዚያ ያሉ የኤምሬትስ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኢፍጣር በችግር ውስጥ የወደቁ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ምግብ በማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ የቅዱሱን የረመዳን ወር አብሮ በማሳለፍና በተለያዩ ሁነቶች አብረናቹህ ነን በማለት አብረው ይሆናሉ፡፡
ሪፖርተር፡– ሰብዓዊ ዕርዳታውን እንዴት አድርጋችሁ ነው የምታሠራጩት?
አልሻምሲ፡- ገንዘብን በተመለከተ ሱዳን አሁን የሚያስፈልጋት ከ4.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ ይህን ገንዘብ ለተለያዩ መሬት ላይ ላሉ አስፈጻሚዎችና ሌሎች ዘርፎች ለጤና፣ ለምግብ እያልክ ስትመድብ ለማሠራጨት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ አንዳንዴ ለቀውሶች ለሚያስፈልጉ የዕለት ደራሽ ዕርዳታዎች ገንዘቡና ዕርዳታው ይውላል፡፡ ነገር ግን ለማሠራጨት አስቸጋሪ ይሆንና ለታለመለት ዓላማ እንደሚፈለገው ሳይደርስ ይቀራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለአንዳንድ ቀውሶች ድጋፍ ሳይገኝ ይቀራል፡፡ በሱዳን ጉዳይ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በጋራ መሥራት እንዳለብን እናምናለን፡፡ በተለይ የሚቀርበው ዕርዳታ ለትክክለኛው ሰው እንዲደርስ እንዲሁም ዕርዳታውን ለማቅረብ የሚያስችሉ መንገዶች ክፍት እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከአገራቸው ተፈናቅለው ወደ ጎረቤት አገር የገቡ ሱዳናውያን በርካታ በመሆናቸው፣ እነዚህን ስደተኞች ተቀብለው ከያዙት የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈጸመ የሚመጣው የሰብዓዊ ዕርዳታ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ብቻም ሳይሆን፣ ከምዕራባውያን አገሮችና ከአፍሪካ አገሮች ጭምር ይሆናል ማለት ነው፡፡ እኛ ማስተላለፍ የምንፈልገው ቁልፍ መልዕክት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በዚህ የረመዳን ወቅት ውጊያ አቁመው፣ ሱዳናውያን የሚያስፈልጋቸውን ዕርዳታ እንዲያገኙና ዘለቄታዊ ሰላም እንዲፈጠር ሁሉም ሊሠራ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡– ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ አዳጋች የሚባሉት ማነቆዎች ምንድናቸው?
አልሻምሲ፡- በእያንዳንዱ አገር የሚኖረው ማነቆ የተለያየ ነው፡፡ እንዲያው ዝም ብለህ ጠቅለል አድርገህ ችግሩ ይህ ነው ማለት አትችልም፡፡ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የሚያስፈልገው በጦርነት ውስጥ ላሉ፣ በጎርፍና በድርቅ ለተጎዱ ወይም በሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡ በዚህ ሒደት የሱዳንን የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት አዳጋች የሚያደርገው እየተካሄደ ያለው ጦርነት ነው፡፡ ለምሳሌ ጦር ሜዳ ውስጥ ገብተህ እንዴት ዕርዳታ ታቀርባለህ? ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የተለያዩ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል፡፡ ማቋረጫ መስመሮቹ አደገኛ ናቸው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ለሱዳናውያን በቂ የዕርዳታ አቅርቦት እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ በፖርት ሱዳንና በፖርት አደሬ የተራገፈው ዕርዳታ መግባት መቻል አለበት፡፡ ነገር ግን እያጋጠመ ያለው ችግር ወደ ሱዳን ድንበር ዕርዳታ ማድረሱ ብቻ ሳይሆን፣ ሱዳን ውስጥ ዕርዳታው ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች በተፈለገው መጠን ማሠራጨት አለመቻሉ ነው፡፡ አንዳንዴ የተለያዩ የተወሳሰቡ ነገሮችን እናያለን፡፡
ከጦርነት አለፍ ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ ወረርሽኝና ሌሎችም ችግሮችን እንደ አገሮቹ ባህሪ በተለያዩ ክስተቶች ልታገኝ ትችላለህ፡፡ በዚህ ወቅት ምላሽህ የሚሆነው እንደ ክስተቱ ሲሆን፣ ሊገጥምህ የሚችለው ማነቆም በዚያው ልክ ይለያያል፡፡ የተለያዩ ትልሞችን ታስቀምጣለህ፣ የተለያዩ አጋሮችን ትፈልጋለህ፡፡ የተባበሩ መንግሥታት ድርጅትና የግሉን ዘርፍ ጨምሮ ወደ ሜዳው አምጥተህ በጋራ እንዲሠሩ ማድረግ መቻል አለብህ፡፡ በአጠቃላይ ሊገጥምህ የሚችለው ችግር ከሁኔታዎች ጋር የሚለያይ ነው፡፡ አንድ ማስመር የምፈልገው ግን በጦርነት ውስጥ ለችግር ለተጋለጡ ሴቶችና ሕፃናት የሚያስፈልጋቸውን የሰብዓዊ ዕርዳታ የማቅረብ ጉዳይ ትኩረትና ጫና የሚፈልግ መሆኑን ነው፡፡ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች መርዳት የግዴታ ግዴታ ነው፡፡ ከሱዳን ከጦርነት ወጣ ስትልና በትንንሽ ደሴቶች ማለትም በካሪቢያንና በፓስፊክ ደሴቶች አካባቢዎች ያሉ አገሮችን ስትመለከት፣ በአየር ንበረት ለውጥ ሳቢያ በሚፈጠር ክስተት በተለይ የአውሎ ንፋስና ማዕበል ሊያጠፋቸው የሚችል አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡ በእነዚህ ደሴቶች ከፍተኛ አውሎ ንፋስና ማዕበል ቢፈጠር አገሮቹ ሊጠፉ ይችላሉ፡፡
በሌላ በኩል የጋዛን ጦርነት ተመልከት፣ ከአንድ ዓመት በላይ ዘልቋል፣ በርካቶች ተገድለዋል፣ ከተማ ወድሟል፡፡ ለዚህ አካባቢ ዕርዳታ የምታቀርብበት መንገድና ለካሪቢያን የምታደርገው ድጋፍ አንድ ዓይነት አይሆንም፡፡ ዕርዳታው ምን ሊሆን እንደሚችልና እንዴት እንደምታጓጉዘው፣ የትኛው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ዕርዳታ እንደሚሆንና ቅድሚያ የሚያስፈልገው የትኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ነው የሚለው መመለስ መቻል አለበት፡፡ አሁን ለሱዳንና ለጋዛ ዕርዳታ ለማቅረብ በጣም ከባድ የሚባል ሥራ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በቀውስ ውስጥ ያሉ በባንግላዴሽ እንደ ሮሂንጋ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ማንም ምንም እያለ አይደለም፣ ተረስተዋል፣ ተትተዋል። እነዚህን ወገኖች መርዳት ከማንነት ጋር የሚገናኝ አይደለም፣ በሰብዓዊነት ለመቆም ሁሉም ኃላፊነት አለበት። ስለዚህ አደጋ ውስጥ ያሉ ሕዝቦችንና አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን መለየትና መድረስ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሁሉ መሰናከል ግን የተለያየ መንገድና ዘዴ በመፈለግ እንደ ሁኔታው አስከፊነት መድረስ አለብን።
ሪፖርተር፡– የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬት ግንኙነት በምን ላይ የተመሠረተ ነው?
አልሻምሲ፡- ወዳጅነትና ወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በመንግሥታቱ መካከል ያለው ግንኙነት፣ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በጣም ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፡፡
ሪፖርተር፡– በተባበሩት የዓረብ ኤምሬትስ በተለያዩ ከተሞች በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ምን ዓይነት ሚና ይጫወታሉ? የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ማለት ነው፡፡
አልሻምሲ፡- እውነት ነው ቁጥራቸው የበዛ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በኢምሬትሰ ውስጥ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እናደንቃለን፣ እናመሠግናለንም፡፡ በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በሆቴል፣ በማርኬቲንግ፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች ትንንሽ ቢዝነሶች ባላቸው ተሳትፎ በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ ትልቅ የሚባል ሚና ይጫወታሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም በቀጣይ የግሉ ዘርፍ በሁለቱ አገሮች ግንኙነት እንዲሳተፍ እንፈልጋለን፡፡ በኤምሬትስ ቢዝነሶች ማለትም በሎጂስቲክስና በሌሎች ዘርፎች እንዲሰማሩ እንፈልጋለን፡፡
ሪፖርተር፡– የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዱባይ በዓለማችን ካሉ ከተሞች ትልቅ የንግድ፣ የቱሪዝምና የመዝናኛ ኢንዱስትሪ መዳረሻ ነች፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ምን ትምህርትና ልምድ መውሰድ ትችላለች?
አልሻምሲ፡- እንግዲህ ሁሉም አገሮች የራሳቸው የሆነ ልምድ ይኖራቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መውሰድ ወይም መማር የምትፈልገው ጉዳይ ካለ እኛ ሁልጊዜም በራችን ክፍት ነው፡፡ በየትኛውም መንገድ የትብብር መስኮች ካሉና ከኤምሬትስ ልምድ መቅስም ለሚፈልግ ከየትኛውም ወዳጅ አገር ለሚመጣ ጥያቄ እጃችንን ዘርግተን ለመቀበል ዝግጁ ነን፡፡ እንዳልከው የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ ለተለያዩ አገሮች መዳረሻና መተላለፊያ ናት፡፡ አዲስ የምንባል አገር ነን፡፡ ይህ እንግዲህ መንግሥታችን በቴክኖሎጂ፣ በወጣቶች፣ በሴቶችና በሌሎች ዘርፎች ጭምር ኢንቨስት ማድረጉ ይመስለኛል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ የልህቀት ማዕከላት ገንብተናል፡፡ የተለያዩ አገሮች ወደ ምሥራቅና ወድ ምዕራብ እንደ መተላለፊያ መስመር ይጠቀሙባታል፡፡ በዚህ ረገድ ከእኛ ልምድ መውሰድና ለመማር ለሚፈልግ ማንኛውም ወዳጅ ወደኋላ አንልም፡፡ ያን ለማድረግ ሁሌም ደስተኞች ነን፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት እንፈልጋለን፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያቀርባቸው አገራዊ ዕቅዶችና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ዕቅዶች መሠረት ከሌላው ዓለም ጋር እንደምንሠራው በሴቶች፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሥራ ፈጠራ፣ በትምህርትና በጤና ዘርፎች አብረን እንሠራለን፡፡ ኢትዮጵያ በአኅጉሩ በጣም ጥሩ የሚባል ለውጥና ተስፋ እያሳየች ያለች አገር ናት፡፡ ካለችበት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ተዳምሮ ወሳኝ መዳረሻ አገር ናት፡፡ አገሪቱ ያላት 130 ሚሊዮን ሕዝብና ወጣት ኃይል ሌላ አቅም ነው፡፡ ለሌላው ዓለም ጥሩ ምሳሌ መሆን ትችላለች፡፡
ሪፖርተር፡– የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ለኢትዮጵያ የምታቀርበው ድጋፍ ምንድነው?
አልሻምሲ፡- አሁን በኢትዮጵያ የተለያዩ የጀመርናቸው ፕሮግራሞች አሉ፡፡ ለምሳሌ በትምህርትና በጤና ዘርፎች እንሠራለን፡፡ በትምህርት ዘርፍ ባለፉት ወራት የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ክፍተናል፣ በሚቀጥሉት ወራትም ይኖሩናል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በግብርና፣ በሎጂስቲክስና በመሰል ዘርፎች ማጠናከር መቻል የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚኖረው ሚና የላቀ ስለሚሆን፣ በዚህ ረገድ አብረን እንሠራለን፡፡ በአኅጉሩ ቁልፍ አጋር አድርገን ስለምንወስዳትም ነው በትብብር መሥራት የምንፈልገው፡፡ ትምህርት፣ ጤናና ግብርና በሚገባ የምናተኩርባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡ በእርግጠኝነት ግን በጤናውና በትምህርት ዘርፎች ወደፊት ብዙ ፕሮግራሞች ይኖሩናል፡፡
ሪፖርተር፡– የተባበሩ ዓረብ ኤሚሬትስ እ.ኤ.አ. በ2023 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (COP28) አዘጋጅ ነበረች፡፡ ኮንፈረንሱን እንዳዘጋጀ አገር የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን እንዴት ይመለከቱታል?
አልሻምሲ፡- የአየር ንብረት ለውጥ ችግር የገዘፈ ነገር ግን መታየት ያልቻለ (Elephant in the Room) ነው፡፡ሁሉም አካል በተብብር መሥራት መቻል አለበት፡፡ ሳይንሳዊ የሆኑ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ሊገቱ የሚችሉና ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮችን በተመለከተ የመፍትሔ አማራጮች ለማስገኘት መሥራትና መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2023 የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ በማዘጋጀት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ውጤታማ የሚባል ዓመታዊ ጉባዔ ማካሄድ ችላ ነበር፡፡ ይህን ስኬት ደግሞ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2024 ‹‹COP29›› ላዘጋጀችው አዘርባይጃን ልምዳችንን አካፍለናል፡፡ አዘርባይጃን ደግሞ ለቀጣዩ ‹‹COP30›› አዘጋጅ ብራዚል ይህን ልምድ በማካፈል በየዓመቱ ከሚካሄደው ኮንፈረንስ የሚገኙ ጥሩ ልምዶችን፣ እንዲሁም ሊስተካከሉ የሚገባቸውን ችግሮችንና አመላካቾችን በተመለከተ ለቀጣዩ ሒደት ትምህርት እንዲወሰድ ማድረግ መቻል አለብን፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ከደቀነው አደጋ አንፃር ኤምሬትስ ከሌሎች አገሮች ጋር በትብብር በመሥራት፣ ቀጣይነት ያላቸውና አዋጭ መንገዶችን የመፍጠር ሥራ ላይ ታተኩራለች፡፡
እዚህ ላይ ቁልፍ የሚባለው ጉዳይ የግሉ ዘርፍ ነው፡፡ ወደፊት ለመግፋትና ችግሩን ለመቅረፍ የሚያግዙ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል የሚለው ላይ ከተስማማን፣ የግሉን ዘርፍ የማሳተፍ ወሳኝነት ጥያቄ የማይቀርብበት ይሆናል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ካለው ጫና በተጨማሪ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በሚታየው ግጭትና ጦርነት ውጣ ውረድ ለሚያስፈልገው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የአገሮችን፣ የመንግሥታትንና የግሉን ዘርፍ ትብብር፣ ጥምረትና አብሮ መሥራትን የሚጠይቅ ሲሆን፣ ሌላው ቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ገንዘብ የሚጠይቀን ጉዳይ ነው፡፡ አብሮ መሥራት ሲባል ቃል የተገቡ ቁርጠኝነቶችን ለመፈጸም የጎላ ተሳትፎና ሚና መጫወትን ይጠይቃል፡፡ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ በዓለም ላይ መጠነ ሰፊ ቀውሶች እያየን ነው፡፡ እነዚህ ቀውሶች በተወሰኑ አካላት ሊመለሱ ይችላሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ ክስተት የፈጠረውን ቀውስ አይተናል፡፡ አገሮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማወቅ ተስኗቸው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በጣም የተበጣጠሱ ጥረቶችን ስናይ ነበር፡፡ ሁሉም በሩንና ድንበሩን ዘግቶ ልውውጥ ማድረግ አለመቻልና መገበያየት ከባድ ሁኔታ ውስጥ የገባበት ወቅት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን መሰል የጤና ቀውስ ሲፈጠር ዓለም አቀፍ ትብብር በማድረግ፣ በአገሮች ኅብረት በሚሠሩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም አዲስ ክትባት መፈብረክና በአጭር ጊዜ ማድረስ የሚቻልበት ዕድል ይኖር ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ እዚህ ላይ በጣም አጠንክሬ መናገር የምፈልገው የጤናውን ዘርፍ መደገፍ ጥያቄ የማይቀርብበት ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ያለ ጤናና ያለ ትምህርት አንድን አገር ወይም ማኅበረሰብ መለወጥ፣ ማሳደግና ማበልፀግ የሚባል ነገር አይታሰበም፡፡ ስለዚህ ልጆችን ለማስተማር፣ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል የግሉን ዘርፍ ማሳተፍና ቀጣይነት ያለው ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ፣ እንዲሁም አገራዊ ዕድገትን ወጥና ቀጣይነት ያለው ማድረግ ይቻላል፡፡ አውቃለሁ እነዚህ ዘርፎች ትልቅ ገንዘብ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ነገር ግን አማራጭ እንደሌላቸው መረሳት የለበትም፡፡