

88ኛው የሰማዕታት ቀን በአዲስ አበባ የካቲት 12 አደባባይ ሲታሰብ
ኪንና ባህል የየካቲቱ የጣሊያን ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ
ቀን: February 23, 2025
ከዘጠኝ አሠርታት ግድም በፊት በወርኃ የካቲት አዲስ አበባ በቀኑ ብርሃን ጨለማ ወርሷት፣ ሕዝቧም ፍዳውን የተጎነጨበት ሰማዕትነትን የተቀበለበት ነበር፡፡ ይህን ያስተዋለው ባለ ቅኔው ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ከዘመናት በፊት እንዲህ ስንኝ አሥሮ አስታውሷቸዋል፡፡

‹‹አገር ተቃጠለ
እሳተ ጎመራ ወረደ ከሰለ።
ጭስ አመድ አዋራ ሰማዩን ሸፈነው
ጥቁር ሰማይ ጥቁር!
የቀን ጨለማ ሞት በእናት አገር ሰማይ
በጀግናው ሕዝብ ላይ የጠላት ግፍ ቀንበር።
ፋሺስት አስተጋባ ፋስ ተሰነዘረ
ባካፋ መዶሻ ሕዝብ ተወገረ።
አባቶች ታረዱ እናቶች ታረዱ
ቤት ንብረት ፈረሰ ከብቶቹ ተነዱ።››
ከሰማንያ ስምንት ዓመታት በፊት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ነበር ፋሺስት ጣሊያን በወረራ በያዛት አዲስ አበባ ከተማ ላይ የመከራ ዝናብ ያዘነበው፡፡ ይህ የሆነው በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ በተገኘው የፋሺስቶች መሪ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ ላይ እነ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የቦንብ ጥቃት ፈጽመው ካቆሰሉት በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ በከተማዪቱ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ ከሠላሳ ሺሕ በላይ ሰዎች ሰማዕት ሆነዋል፡፡

ሰማዕታቱን ለማስታወስ በየዓመቱ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የካቲት 12 ቀን አደባባይ በልዩ ዝግጅት ይደረጋል፡፡ ዘንድሮ ለዕድሳት በታጠረው አደባባይና ሐውልቱ ዙሪያ ቀኑ የታሰበው፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ተወካይ፣ የሃይማኖት አባቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡ በሐውልቱ ግርጌ የየተቋማቱ ተወካዮች ጉንጉን አበባ አስቀምጠዋል፡፡
በተመሳሳይም በጭፍጨፋው ሰማዕት የሆኑት አፅማቸው ተሰብስቦ በጋራ ባረፈበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቆመላቸው ሐውልትም ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎላቸዋል፡፡
በልሳነ ግእዝ ‹‹ዝንቱ ውእቱ ምዕራፈ አዕጽምቲሆሙ ለብዙኃን ኢትዮጵያውያን እለ ተቀትሉ በግፍዕ በእደዊሆሙ በሕዝበ ኢጣሊያ ፋሽስታውያን አመ ፲ወ፪ ለየካቲት በ፲ወ፱፻፳ወ፱ ዓ.ም.›› (ይህ የአፅሞች ማረፊያ በጣሊያን ፋሺስታውያን እጅ በግፍ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. የተገደሉ የብዙኃን ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ነው) ይላል ሐውልቱ፡፡

የሐውልቱ ላይ ጽሑፍ የኢትዮጵያ ሰማዕታት አገዳደላቸው በድንጋይ በመወገር፣ በዱላ በመቀጥቀጥ፣ በአካፋ፣ በዶማ በመብረቀ ሐፂን/የብረት መብረቅ (መትረየስ)፣ በየቤታቸው ውስጥ በእሳት በመቃጠል፣ ወዘተ እንደሆነ ይዘረዝራል፡፡ የግፍ አገዳደሉ በተፈጸመ በአራተኛው ዓመት በ1933 ዓ.ም. ከእንግሊዝ በድል አድራጊነት የተመለሱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የነፃነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ካቆሙ በኋላ በግፍ የተገደሉትን አፅሞች ከየቦታው እንዲሰበሰቡ ሹማምንቱን በማዘዝ ለዝክረ ነገር እንዲሆንም በቅዱስ ሥፍራም መታሰቢያውን በ1934 ዓ.ም. አቆሙላቸው ሲል አመልክቷል፡፡
ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ 14ኛ ዓመት የዘውድ በዓላቸውን ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 1937 ዓ.ም. ሲያከብሩ ነበር ሐውልቱ የተመረቀውና ለአርበኞችም የተጋድሎ ሜዳሊያ ያበረከቱት፡፡
በሐውልቱ ግርጌ ላይ የተቀረፀው ግጥምም የመከራውን ዓይነት በየፈርጁ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡
ራስን ካንገት ላይ ቆራርጦ እየጣለ
በችንካር ቸንክሮ ሰው እየገደለ
ሰውን ከነቤቱ አብሮ እያቃጠለ
ማነው እንደ ፋሽስት በሰው ግፍ የዋለ?
ሥጋችንን ገድለው ሊቀብሩት ከጀሉ
በዚህ ያልነበሩ ሐሰት እንዳይሉ
እኝህ አስክሬኖች ይመሰክራሉ፡፡
ይህን ታላቅ ስቃይ መከራና ግፍ
ሲያስታውስ ይኖራል የታሪክ መጽሐፍ
አትርሱት አንርሳው ያስታውሰው ዘራችን
ኢጣሊያ መሆኗን መርዛም ጠላታችን፡፡
እናንት አእጽምቶች ዕድለኞች ናችሁ
በኃይለ ሥላሴ ትንሣኤ አገኛችሁ፡፡
ታሪክ የመዘገበው
የየካቲት 12ቱን ጥቃት በማቀነባበርና በመምራት ረገድ ተጠቃሽ የሚሆኑት በጅሮንድ ለጥይበሉ ገብሬ (በኋላ ደጃዝማች) መሆናቸው ይወሳል፡፡ ይህንንም ያቀናበሩት ጀኔቭ የነበሩት በንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በግራዚያኒ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ አማካይነት ባስተላለፉላቸው ትዕዛዝ መሠረት መሆኑ በኢትዮጵያ ጥናት ጆርናል ላይ ተመዝግቧል።
ኢያን ካምቤል በጻፈው ድርሳኑ እንደገለጸው፣ ለአብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም እነሱን ከመመልመል ጀምሮ ለተልዕኮው አስተዋፅዖ ያደረጉ ስብሐት ጥሩነህና ስምኦን አደፍርስ እንዲሁም ባሻህ ውረድ ሀብተ ወልድ ናቸው፡፡
ባህሩ ዘውዴ በጻፉት ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966›› መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ የጣሊያን ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ነው፡፡
‹‹አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት፡፡ ‹‹ጥቁር ሸሚዝ›› እየተባሉ የሚታወቁት የፋሽስት ደቀመዛሙርት መንግሥት አይዟችሁ እያላቸው አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፡፡ ቤቶች ከነነዋሪዎቻቸው ጋዩ፡፡ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፡፡
‹‹የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ፡፡ ይህ የምሁራን ጭፍጭፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመሆኑም ባገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሽር ቁስል ጥሎ አለፈ፡፡
የካቲት አርበኞቹ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በግራዚያኒ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ በተሽከርካሪው ወደ ፍቼ የወሰዳቸው ስምኦን አደፍርስ ነበር፡፡ የፋሺስቶች የግፍ ሰለባ ስለሆነው ስምዖን አደፍርስ በጴጥሮስ ጳውሎስ የካቶሊክ መካነ መቃብር በሚገኘው ሐውልቱ ላይ ገድሉን እንዲህ ጽፎታል፡፡
‹‹ወጣቱ አርበኛ ስምዖን (1905-1929) የአብርሃና የሞገስ የልብ ጓደኛ ነበር፡፡ ከአደጋውም በኋላ ከአዲስ አበባ ያሸሻቸው በታክሲ መኪናው ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ተይዞ ደጃች ውቤ ሠፈር በግራዚያኒ ወህኒ ቤት ማቅቆ አካሉ ከሰውነቱ ውጭ ሆኖ በመርዝ ተገደለ፡፡ ዘመዶቹ በድብቅ ቀበሩት፡፡››
የየካቲት 12 ቀን ሰማዕታትን ለመዘከር ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በብሔራዊ በዓልነት እስከ 1966 ዓ.ም. ለሠላሳ ሁለት ዓመታት ሲከበር ኖሯል፡፡ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ) ሥልጣን ከያዘበት ከሃምሳ ዓመት ወዲህ (1967 ዓ.ም.) ግን በመሠረዙ እስካሁን ታስቦ እየዋለ ነው፡፡