
February 23, 2025

ሰብዓዊነት ራሱን ችሎ የቆመ አንድ ቃል ብቻ ሳይሆን በውስጡ በርካታ ጉዳዮችን አጭቆ የያዘ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ርኅራኄ፣ ደግነት፣ አዛኝነት፣ ለጋስነት፣ ፈጥኖ ደራሽነት፣ ትህትናንና መሰል መልካም ነገሮችን ማግኘት የሚቻለው ሰብዓዊነት ውስጥ ነው፡፡ ሰዎችን በዘራቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በፆታቸው፣ በቀለማቸው፣ በቋንቋቸው፣ በባህላቸው፣ በማኅበራዊ መሠረታቸው ወይም በሌሎች የማንነት መገለጫዎቻቸው እንዳይገለሉ ወይም እንዳይጠቁ ዋነኛው የመከላከያ መሣሪያ ሰብዓዊነት ነው፡፡ ሰብዓዊነት ለክፋትና ለጭካኔ ድርጊቶች ቦታ የማይሰጥ፣ ለሰብዓዊ ፍጡራን ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትና ለዕፅዋት ደኅንነት ጭምር የሚጨነቅና የሚጠበብ፣ ሁሉም ሰዎች በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚስተናገዱባቸው የትምህርት፣ የጤና፣ የሥራ፣ የመኖሪያና መሰል አገልግሎቶች ማግኛ ከባቢ እንዲኖር ይሞግታል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው በየምክንያቱ እርስ በርስ መጣላት፣ መጋጨት፣ መሳደድ፣ በጭካኔ መገዳደልና ትርምስ መፍጠር ፀረ ሰብዓዊነት ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን የመሰለች ባለብዙ ታሪክ አገር ውስጥ ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ ጭካኔዎች እያደረሱ ያሉትን ጥፋት መገንዘብ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች በልጆቿ መስዋዕትነት ተጠብቃ ኖራ እዚህ የደረሰችው፣ በየዘመናቱ የነበሩት ትውልዶች እርስ በርስ ተከባብረውና ተሳስበው አገራቸውን በጋራ በመከላከላቸው ነው፡፡ በገዥዎች የጭቆና ቀንበር ውስጥ ሆነውም በጋራ የገነቧቸው ዘመን ተሻጋራ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው፣ በተለያዩ መንገዶች መስተጋብራቸውን አስጠብቀው አዝልቀዋቸዋል፡፡ ዕድሩ፣ ዕቁቡ፣ ሐዘኑ፣ ሠርጉ፣ ደቦው፣ የሽምግልና ሥርዓቱ፣ ወዘተ በማኅበረሰቦች ውስጥ ሰብዓዊነት ጎልቶ እንዲወጣ አድርገዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ የዘመናት የጋራ እሴቶች ባይኖሩ ኖሮ፣ አርቆ ማሰብ በተሳናቸው ፖለቲከኞችና አጃቢዎቻቸው ሊደርስ ይችል የነበረው ጥፋት ተወዳዳሪ አይኖረውም ነበር፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከልዩነቶቻቸው በላይ አንድነታቸው እንደሚበልጥ ተረድተው፣ አንዱ አካባቢ የደረሰ በደል ወይም ግፍ በራሳቸው ላይ እንደተፈጸመ ቆጥረው መኖራቸው የሰብዓዊነትን ልክ አመልካች ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አኩሪ ተግባር ከማስቀጠል ውጪ ሌላ አማራጭ ሊኖር አይገባም፡፡
የዘመኑ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ ልሂቃን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ አመራሮች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ በተለያዩ ሙያዎች የተሰማሩ ዜጎችና የአገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ በሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በጭካኔ ምትክ ሰብዓዊነት እንዲቀነቀን የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዳዮች ፖሊሲዎችና ውሳኔዎች ሰብዓዊነትን ማዕከል እንዲያደርጉ ሐሳብ ማዋጣት አለባቸው፡፡ ሰብዓዊነትን መነሻ ያላደረጉ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራሞች ወይም ማኒፌስቶዎች፣ ውጤታቸው በጭካኔ የታጀበ ጥፋት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የትኛውም የፖለቲካ ዓላማ ግቡ ሰብዓዊነት ላይ ካላነጣጠረ ከዕልቂትና ከውድመት የዘለለ ውጤት እንደማይኖረው መታወቅ አለበት፡፡ ሕጎች ሲረቀቁ በሰብዓዊነት ስሜት ካልተቃኙ ከፋይዳቸው ይልቅ ጥፋታቸው እንደሚብስ መግባባት ተገቢ ነው፡፡ ትምህርትም ሆነ ሌሎች የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ሰብዓዊነት ላይ ያተኩሩ፡፡ አገር ወደፊት መራመድ የምትችለው በዚህ መንገድ እንደሆነ ይታመን፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ሰላም አጥታ ዙሪያ ገባው የጦርነት፣ የግድያ፣ የማፈናቀል፣ የዕገታ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የውድመት ዜናዎች ተበራክተው ሲደመጡ እንደ ዋዛ ማለፍ የማይቻልበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ በጭካኔ የሚፈጸሙ ማሰቃየቶች፣ ግድያዎችና ሌሎችም ነውረኛ ድርጊቶች በተባበረ ክንድ እንዲቆሙ ካልተደረገ ስለአገር ህልውና ለመነጋገር ጊዜ አይኖርም፡፡ አንዱ ሌላውን በጥላቻ፣ በቂም በቀል፣ በክፋት፣ በአሉባልታ፣ በስም ማጥፋትና በመረረ ስሜት ለማስወገድ የሚደረገው አደገኛ አካሄድ መቆም አለበት፡፡ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ ይዞ በበርካታ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መምከርም ሆኖ አብሮ መሥራት የሚያስችል ዓውድ መፍጠር ሲገባ፣ ኢሰብዓዊ በሆነ የደም ፍላት ውስጥ ሆነ ለመጠፋፋት ግድግዳ ሲቧጥጡ ማደር መገታት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጠን በላይ አስከፊ ጭካኔዎች በመታየታቸው አሁን ተራው የሰብዓዊነት እንዲሆን መግባባት ላይ ይደረስ፡፡
ኢትዮጵያ ከበርካታ ዓመታት በፊት ተቀብላ ያፀደቀችው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፣ ሁሉም ሰዎች ነፃና እኩል ሆነው በመወለዳቸው ክብራቸውና መብቶቻቸው መጠበቅ አለባቸው ሲል በአንቀጽ አንድ ላይ አስፍሯል፡፡ በሌሎች አንቀጾችም ሁሉም ሰዎች በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት መስተናገድ እንዳለባቸውና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና በየትም ሥፍራ የመዘዋወር መብታቸው መከበር እንዳለበት ተዘርዝሯል፡፡ ማንም ሰው ጭካኔ የተሞላበት ሥቃይና ሰብዓዊ ክብር የሚያሳጣ ቅጣት እንዳይፈጸምበትም ተደንግጓል፡፡ በሥራ ላይ ባለው የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ውስጥ ከአንድ-ሦስተኛ በላይ የሚሆነው ክፍል በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ድንጋጌዎች የታጨቀ ነው፡፡ ስለዚህ በተፈጥሮና በሕግ ዋስትና ያገኙ ነፃነትና መብቶች ተደፍጥጠው ዜጎች በጭካኔ እንዳይጎዱ ሲባል፣ ከመንግሥት ጀምሮ እስከ እያንዳንዱ ዜጋ ድረስ ለሰብዓዊነት ትልቅ ሥፍራ እንዲሰጥ ፈቃደኝነት ይኑር፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰብዓዊነት ማሳያ የሚሆኑ የበጎ አድራጎት ሥራዎች መኖራቸው ተስፋ ይሰጣል፡፡ አረጋውያንን፣ አቅመ ደካሞችን፣ የአዕምሮ ሕሙማንን፣ ሕፃናትንና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን አስጠግተው የሚደግፉ ግለሰቦችና ተቋማት የሰብዓዊነት መልካም ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህን በጎ አድራጊዎች መደገፍና ማበረታታት ተገቢ ነው፡፡ ሰሞኑን ለመቄዶኒያ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል እየተደረገ ያለው የገቢ ማሰባሰቢያ ርብርብ የሰብዓዊነትን ጥግ ማሳያ ነው፡፡ ለመቄዶኒያም ሆነ ለሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እየቀጠለ፣ ተረጂዎችም ከድጋፍ ጠባቂነት የሚያላቅቋቸው የልማት ፕሮጀክቶች እየተነደፉ ጥረቱ በባለሙያዎች ጭምር ሲታገዝ ትልቅ ውጤት ይገኝበታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ልብ የሚነኩ ሥራዎችም በሌሎች መስኮች ተጠናክረው ኢትዮጵያን ከገባችበት የጥፋት አረንቋ ውስጥ ማውጣት የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ ሰብዓዊነትም የአገር መርህ ይሁን!