
ከ 6 ሰአት በፊት
በፓሪስ ኦሊምፒክ ዓለምን ካስደመሙ ጉዳዮች መካከል ግብፃዊቷ ናዳ ሐፊስ የሰባት ወር ነፍሰጡር ሆና በሻምላ ፍልሚያ (ፌንሲንግ) መወዳደሯ ነበር።
“ስለ ልጄ እያሰብኩ ነበር፣ ልጄ የኦሊምፒክ ተሳታፊ እንድትሆን ምኞች ነበረኝ” ትላለች በወቅቱ የነበረውን ስሜት ስትገልጽ።
ነፍሰጡርነቷ በኦሊምፒክ ውድድር እንድትሳተፍ የበለጠ መነሳሻ ሆኖኛል ትላለች።
በጣም ጥቂቶች ነበሩ ናዳ በውድድሩ ስትሳተፍ የሰባት ወር ነፍሰጡር መሆኗን የሚያውቁት።
16ኛ የሆነችበት የመጨረሻው ውድድር ላይ በማኅበራዊ ሚዲያዋ ላይ የሰባት ወር ነፍሰጡር መሆኗን ይፋ አደረገች።
ጉዳዩም በዓለም ባሉ ታላላቅ የመገናኛ ብዙኃንም ርዕሰ ዜና ለመሆን ቻለ።
ናዳ የዜናው እንዲህ መናኘት ያልጠበቀችው ጉዳይ ነበር።
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
“በግል አካውንቴ ላይ ነው የለጠፍኩት። ነፍሰጡር ሆኜ በውድድሩ 16ኛ ሆኜ ማጠናቀቄ ያኮራኛል የሚል ነበር” ስትል ናዳ ለቢቢሲ ስፖርት ተናግራለች።
የ27 ዓመቷ ወጣት የደረሷት መልዕክቶች አብዛኞቹ አዎንታዊ ነበሩ ትላለች።
“የለጠፍኩት ጽሁፍ የበለጠ ታዋቂ ሲሆን በርካቶችን ማነሳሳቱ ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር” ትላለች።
የላብራቶሪ ባለሙያ የሆነችው ናዳ በሻምላ ውድድር ላይ እንድትሳተፍ ከዶክተሮች ፍቃድ እንደተሰጣት እንዲሁም የሴት አካል ያለውን ብቃት ለዓለም ለማሳየት የውድድሩ ተሳታፊ መሆኗን ትናገራለች።
“ይህ ለእኔ፣ ለአንዲት ግብፃዊት እንዲሁም አረብ ሴት ትልቅ መልዕክት አለው። ለሁሉም ሴቶች ሰውነታችሁ የሚያስደንቅ ተግባራትን ማከናወን ይችላል የሚለውን ያሳያል” ትላለች።
አክላም “አንዳንድ ጊዜም አንድ ነገርን ማከናወን እንደምትችሉ ለማወቅ አርዓያ ማየት ሊያስፈልግ ይችላል” ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።
“ምክንያቱም ነፍሰ ጡር የሆነች ሴት ሁሉንም ነገር ለማከናወን ትፈራለች። ነፍሰ ጡር ሆና በኦሊምፒክ የምትወዳደር ሴት ማየቷ ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንደምትችል ያሳያታል” ብላለች።
ናዳ የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ሆና በግራንድ ፓሌይስ በተካሄደው የሴቶች የሽምላ ውድድር መሳተፏ በሁሉም ሰው ዘንድ ድጋፍ አላስገኘላትም። የተቃወሟትም አልታጡም።
ናዳ የሰባት ወር ነፍሰጡርነቷን ካወጀች ከአንድ ቀን በኋላ በኦሊምፒክ ውድድር በመሳተፍ የመጀመሪያዋ እርጉዝ ሴት እንዳልሆነች በቴሌግራም ገጿ ላይ ባወጣችው ጽሁፍ አሰፈረች።
አትሌቷም ግብፃውያን ሴቶች “ጥንካሬ እና ጽናት የተሞሉ እንዲሁም ተስፋ መቁረጥ የማይታይባቸው” መሆኑን ለማጉላት ነው የተሳተፍኩት ስትል በዚሁ ጽሁፍ ላይ አሰፈረች።
ናዳ አንዳንድ አሉታዊ አስተያየቶችን ማስተናገዷ አልቀረም።
“አንዳንድ ሰዎች ሲሳካልን ማየት አይፈልጉም” የምትለው ናዳ “አስተያየት ሰጥቶ መሮጥ ቀላል ነው” ብላለች።
“የሕክምና ዶክተር ነኝ፤ እናም ነፍሰጡር ሆኜ በውድድር መሳተፌ ከየትኛው የሕክምና ጉዳዮች ጋር የማይቃረን መሆኑን ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ” ብላለች።
“አንዳንድ ግለሰቦች የውድድሩን ቦታ ለሌላ ሰው መስጠት እንደነበረብኝ አስተያየት ሰጡኝ። ለውድድሩ ብቁ ሆኜ ነው የተሳተፍኩት ስለዚህ ለእኔ ይህ አማራጭ አልነበረም” ብላለች።
“እናቴ በምታነቢው ነገር ሁሉ ሐዘን አይሰማሽ ትለኝ ነበር። ባሳካሁት ነገር በሙሉ እኮራለሁ። ፈታኝ ነገር ማሳካት ችያለሁ” ብላለች።
የሽምላ ውድድር ሻምላ በመጠቀም የሚደረግ የውድድር ስፖርት በመሆኑ አሉታዊ አስተያየቶቹ የመጡት ከዚያ ጋር በተያያዘ ይሆን?
“ለእኔ የሽምላ ውድድር እንደሚታየው አይደለም። ዶክተሬም ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን አረጋግጦልኛል” ስትል ምላሽ ሰጥታለች።
- ታዳጊዎች ያለዕድሜያቸው የወር አበባ እንዲያዩ የአየር ብክለት እንዴት ምክንያት ይሆናል?20 የካቲት 2025
- ህሙማንን ለብዝበዛ እያጋለጠ ያለው ከ10 ሴቶች አንዷን የሚይዘው ፒሲኦኤስ ምንድን ነው?28 ጥር 2025
- ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ ክብረ ወሰን በሰበረ ዋጋ ለቼልሲ ፈረመች27 ጥር 2025

በፓሪስ የሽምላ ውድድር በመሳተፍ የተሳካው ህልም
በግብፅ መዲና ካይሮ ነዋሪ የሆነችው ናዳ ለሽምላ ውድድር ፍቅር ያደረባት በሕክምና የዲግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች በነበረበት ወቅት ነው። የግብፅ ሻምፒዮና በመሆን በአውሮፓውያኑ 2016 በሪዮ ኦሊምፒክ እንዲሁም በቀጣዩ በአውሮፓውያኑ 2020 በጃፓን ተሳትፋለች።
ለፓሪስ 2024 ኦሊምፒክስ ብቁ መሆኗ ነፍሰጡር መሆኗን ከማወቋ ጋር ከመገጣጠሙ ጋር ተያይዞ በውድድሩ ላለመሳተፍ አስባ ነበር?
“አዎ ከዓለም ዋንጫ በፊት ነው ነፍሰ ጡር መሆኔን ያወቅኩት። የመጀመሪያ እርግዝናዬ በመሆኑ ስጋት ውስጥ መግባት አልፈለግኩም ነበር” ትላለች።
“የልብ ቀዶ ሕክምና ሐኪም የሆነው ባለቤቴ ውድድሩን አቁሜ እረፍት እንድወስድ እሰኪነግረኝ እየጠበቅኩ ነበር። ነገር ግን ዶክተር ጋር ሄደን እሱ የሚልሽን እናደርጋለን አለኝ” ስትል ታስረዳለች።
“እናም ዶክተሩ በበኩሉ በሽታ የለብሽም። ነፍሰጡር ነሽ። ደህና ከሆንሽ እና ሁሉም ነገር በተለመደው መልኩ እየሄደ ከሆነ የፈለግሽውን ማድረግ ትችያለሽ አለኝ” ስትል ናዳ ለቢቢሲ አስረድታለች።
ዶክተሩ የሰጧትን ማረጋገጫን ተከትላ ናዳ በሥልጠናዋ ቀጠለች።
የእርግዝናዋ ዜና ቢሰማ አገሯ መነጋገሪያ ትሆናለች በሚል ዝምታን መረጠች።
“ለማንም መናገር አላስፈለገኝም ምክንያቱም ጉዳዩ የኦሊምፒክ ሕግን የሚጻረር አይደለም” ስትል ታስረዳለች።
“ማወቅ ለሚገባቸው ግለሰቦች ብቻ ተናገርኩ። ዋነኛው ነገር ከማንኛውም ሕግ ወይም የጤና ሁኔታ ጋር አለመጻረሩ ነው” ትላለች።
“እንደማሳካው አላውቅም ነበር። ስለዚህ የኦሊምፒክ ውድድር እስኪደርስ ቀስ በቀስ፣ ደረጃ በደረጃ ነው የሄድኩት” በማለት ናዳ ትገልጻለች።
የግብፅ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነፍሰጡር ሴቶች ከሥልጠናም ሆነ ከውድድር የሚከለክል ሕግ እንደሌለው ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ገልጿል።
“ነገር ግን ደኅንነቱ የተጠበቀ ከባቢ መኖር አለበት፤ እናም ምንም ዓይነት አደጋዎች አለመኖራቸውን ማረጋገጥ አለብን” ሲሉ አንድ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የኦሊምፒኳ ልጅ
ናዳ ልጇን ዘይና ከተገላገለች አራት ወራትን አስቆጥራለች። በአሁኑ ወቅት ነፍሰጡርነቷ ወይም ልጇ በፖሪስ ላስመዘገበችው ስኬት ያደረገችላትን ሚና እያጤነች ትገኛለች።
“ከአእምሮ አሠልጣኝ ጋር ሰርቻለሁ። ለልጄ የተለየ ነገር ማድረግ እፈልግ ነበር” ስትልም ትናገራለች።
“ላለማሸነፌ ሰበብ አለኝ የሚለውን ላለማሰብ ሞክሬያለሁ። ነፍሰጡር ነኝ እናም አሸንፋለሁ በሚል በተለየ መንገድ ማሰብ ጀመርኩ። እናም አሳካሁት” ስትል ታስረዳለች።
ናዳ አሜሪካዊቷን ኤልዛቤት ታርታኮቭስኪ 15 ለ13 በማሸነፍ የመጨረሻዎቹ አስራ ስድስቱ ውስጥ መግባቷን አረጋግጣለች።
“በግብፅ የሴት ኦሊምፒክ ተወዳዳሪዎች ምርጥ የሚባል ውጤት ነው” ትላለች።
“በደስታ እያነባሁ ነበር። ይህ ልጄ የምትኮራበት ስኬት ነው” ስትልም ደስታዋን አጋርታለች።
ከዚያም በደቡብ ኮሪያዊቷ ጂዮን ሃዮንግ 15 ለ7 ተሸንፋለች። ሁሉም ተፎካካሪ ተወዳዳሪዎቿ ናዳ የሰባት ወር ነፍሰጡር መሆኗን አላወቁም።
“ተፎካካሪዎቼ ማወቃቸው ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም። ምናልባት ለመንካት ወይም የሆነ ነገር ለማድረግ ይፈሩ ይሆናል። ስለዚህ መናገሩ አስፈላጊ አልነበረም።”
አርዓያ መሆን ልቤን በደስታ የሚሞላው ጉዳይ ነው
ናዳ አዲስ እናት ከመሆኗ በተጨማሪ የድኅረ ምረቃ ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች። ናዳ ያላትን ድምጽ እና መድረክ በመጠቀም በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ለሴቶች መብት መከበር የመታገል ዕቅድ ይዛለች።
በቀጣዩ በአውሮፓውያኑ 2028 በሎስ አንጀለስ በሚካሄደው ኦሊምፒክ ላይ ለመወዳደር እስካሁን አልወሰነችም።
ለአሁኑ በፓሪስ የተቀዳጀችውን ውጤት እያጣጣመች ነው።
“ታዳጊ ሴቶች አነሳስተሽናል ይሉኛል። የሕክምና ትምህርት ቤት ገብተው በስፖርት መቀጠል የሚፈልጉ እንዳሉ ገልጸውልኛል” የምትለው ናዳ “ይህ በጣም የሚያስደስተኝ ነገር ነው” ስትል ታክላለች።
“ማናቸውም አርዓያዬ ነሽ ብለው መልዕክት ሲልኩልኝ ልቤ በደስታ ይሞላል። መላው ሕይወቴን የሠራሁት ለዚህ ነው” ብላለች።
“ገና ወጣት ነኝ። የበለጠ ለመሥራት እንዲሁም እንደ እናት አርዓያ ለመሆን እፈልጋለሁ።”
“ልጄ አንድ ቀን በኦሊምፒክ ተወዳዳሪ እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ። እሷ ሕጻን የኦሊምፒክ ተሳታፊ ናት ምናልባትም ትልቅም ሆና ትሳተፍ ይሆናል።”