ሰር ኪር ስታርመር እና ዜሌንስኪ

ከ 6 ሰአት በፊት

ሰር ኪር ስታርመር በሚቀጥለው ሳምንት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በሚያደርጉት ውይይት የዩክሬንን ሉዓላዊነት አንስተው እንደሚወያዩ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ ተናገሩ።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቅዳሜ ዕለት ከቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር ሲነጋገሩ ዩናይትድ ኪንግደም ለኪየቭ የምታደርገውን “የማያወላውል ድጋፍ” በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሩሲያ ጋር ግንኙነታቸውን እንደገና ለማደስ እና የዩክሬን ጦርነት ለማቆም መወሰናቸውን ተከትሎ ሁለቱ መሪዎች በአራት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በስልክ ተወያይተዋል።

ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን ከወረሩ ነገ ሰኞ ሦስት ዓመት የሚሞላ ሲሆን፣ ይህንንም አስመልክቶ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጥሉ አስታውቀዋል።

ቅዳሜ ዕለትም 2,000 ሰዎች በምዕራብ ለንደን ወደሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ዩክሬንን በመደገፍ በሰልፍ ተጉዘዋል።

የእንግሊዝ መንግሥት ቃል አቀባይ “ጦርነቱን ለማቆም ዩክሬን የየትኛውም ድርድር ማዕከል መሆን አለባት። . . . . . ዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያን ሕገ-ወጥ ጦርነት ለማስቆም፣ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ቁርጠኝነት አላት” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማለታቸውን ገልጸዋል።

ከሁለቱ መሪዎች የስልክ ውይይት በኋላ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሰጠው መረጃ፣ ሰር ኪር እና ዜሌንስኪ “ይህ ለወደፊቷ ዩክሬን እና በአጠቃላይ ለአውሮፓ ደህንነት ትልቅ ትርጉም ያለው ጊዜ ነው” ሲሉ መስማማታቸውን ገልጿል።

ሰር ኪር በተጨማሪም ለዜሌንስኪ “የዩክሬንን ሉዓላዊነት መጠበቅ ወደፊት ሩሲያ ልታደርግ የምትችለውን ወረራ ለመከላከል አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “በሚቀጥሉት ቀናት እና ሳምንታት ውስጥ እነዚህን ጠቃሚ ውይይቶች፣ ከትራምፕ ጋር በሚቀጥለው ሳምንት ዋሽንግተን ዲሲን ሲገናኙ ጨምሮ” እንደሚቀጥሉበት ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ ከሰር ኪር ጋር ውጤታማ ውይይት እንዳደረጉ ተናግረው “የሚኖረንን ወታደራዊ ትብብር፣ የጋራ እርምጃ እና ለሚመጣው ሳምንት ያሉብንን ጉዳዩች” በሚመለከት መወያየታቸውን ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ላይ “እንግሊዝ እና ሕዝቦቿ ከዩክሬን ትልቅ ደጋፊዎች መካከል ናቸው፤ ለዚህም ትልቅ አድናቆት አለን” ብለዋል።

ሰር ኪር ዘ ሰን ጋዜጣ ላይ በጻፉት ጽሑፍ ትራምፕ የአውሮፓ አገራት ለደህንነታቸው የበለጠ ሀላፊነት መውሰድ አለባቸው እና የመከላከያ ወጪያቸውን ማሳደግ አለባቸው ያሉት ትክክል ነው ብለዋል።

“ስለዚህ ጉዳይ ለረዥም ጊዜ ተነጋግረናል። አሁን ጊዜው የተግባር ነው። ፕሬዚዳንት ትራምፕም ይህንን ተረድተው ጥሩ የሰላም ስምምነት በጠረጴዛው ላይ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ መሞከራቸው ተጠባቂ ነው።

“ከእርሱ ጋር [ዜሌንስኪ] በተነጋገርኩ ቁጥር ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ይገርመኛል” ሲል ጽፈዋል።

ሰር ኬር በተጨማሪም ዩክሬን በድርድር ውስጥ ድምጽ ሊኖራት እንደሚገባ እና ጠንካራ የደህንነት ዋስትና እንደሚያስፈልጋት ተናግረው “አሜሪካ የዚያ ዋስትና አካል መሆን አለባት ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።

ቅዳሜ ዕለት ከአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ አውሮፓ “ለጋራ የአውሮፓ ደኅንነት ጥቅም መጎልበት መዘጋጀት አለባት” ሲሉ መስማማታቸውን ጽህፈት ቤታቸው ገልጿል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቅርቡ አገራቸው በሩሲያ ላይ የምትጥላቸው ተጨማሪ ማዕቀቦች የፕሬዚዳንት ፑቲንን “ወታደራዊ ማሽን” አቅም ይሸረሽራሉ ብለዋል።

ሰኞ ዕለት ታስቦ ከሚውለው የሩሲያ ወረራ ሦስተኛ ዓመት አስቀድሞ “በሩሲያ ላይ እስከዛሬ ከተጣሉት ሁሉ ትልቁን ማዕቀብ ለመጣል እቅድ አለ” ሲሉ ላሚ ተናግረዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም “ዘላቂ፣ ፍትሃዊ ሰላም” ለማምጣት ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ጋር መስራቷን ትቀጥላለች ብለዋል።

ሰር ኪር ሐሙስ ዕለት በዋሽንግተን ዲሲ ከትራምፕ ጋር የሚያደርጉት ስብሰባ የመጣው የአውሮፓ መሪዎች የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከሩሲያ አቻቸው ጋር የፈጠሩትን ወዳጅነት በተመለከተ አንድ አቋም ላይ ለመድረስ ስብሰባዎች እና የስልክ ውይይቶች ሲያደርጉ ከከረሙ በኋላ ነው።

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዋይት ሀውስ ከመገኘታቸው በፊት ትራምፕ የዩክሬንን ጦርነት ለማቆም “ምንም ያደረጉት ነገር የለም” ሲሉ ተችተዋቸዋል።

በተጨማሪም ዜሌንስኪ በሰላም ድርድር ውስጥ “ምንም ዕድል” እንደሌላቸው እና “በስብሰባዎች ላይ መገኘቱ በጣም አስፈላጊ ነው” ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል።

ነገር ግን የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሌይ ዘ ሰንዴይ ታይምስ ጋዜጣ ላይ በጻፉት ጽሑፍ “ስለ ዩክሬን የሚደረግ ማንኛውም ድርድር ያለ ዩክሬን ሊከናወን አይችልም። ሁላችንም ውጊያው እንዲያበቃ እንፈልጋለን፤ ነገር ግን አስተማማኝ ያልሆነ ሰላም የበለጠ የጦርነት አደጋ ላይ ይጥላል” ብለዋል።

አክለውም ” በዩክሬን ላይ ባለን አቋም በዩናይትድ ኪንግደም አመራር እና በዩናይትድ ኪንግደም አንድነት ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።

ባለፈው ሰኞ የአውሮፓ መሪዎች አሜሪካ እና ሩሲያ በሳዑዲ አረቢያ በምታደርገው ውይይት ዩክሬን እና አውሮፓ ሊገለሉ ይችላሉ የሚል ስጋት ስለተፈጠረባቸው ተሰብስበው ነበር።

ማክሰኞ ዕለት ትራምፕ ዜሌንስኪን “አምባገነን” በማለት ምንም እንኳ ሩሲያ ዩክሬንን የወረረች ቢሆንም፣ ጦርነቱን “በፍፁም መጀመር አልነበረበትም” ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

ዜለንስኪ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሩሲያ በፈጠረችው “የሃሰት መረጃ ዓለም ውስጥ እየኖሩ ነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።