
ከ 7 ሰአት በፊት
ፖፕ ፍራንሲስ ቅዳሜ ዕለት “የተራዘመ አስም መሰል የመተንፈሻ አካላት ችግር” ካጋጠማቸው በኋላ የጤናቸው ሁኔታ “አስጊ” ሆኖ ቀጥሏል ሲል ቫቲካን አስታውቋል።
የሮማው ሊቀ ጳጳስ “ከትናንትናው የበለጠ ታምመዋል” ያለው የቫቲካን መግለጫ፣ በዚህም የተነሳ ደም እንዲወሰዱ መደረጉ ተገልጿል።
የ88 ዓመቱ አዛውንት ንቁ የነበሩ ቢሆንም፣ ከፍተኛ “የኦክስጂን ፍሰት” ያስፈልጋቸው ስለነበር እና የተደረገላቸው ምርመራ “በክትትል ውስጥ መቆየት” እንዳለባቸው ማሳየቱን ቫቲካን በመግለጫው አስታውቋል።
የሮማው ሊቀ ጳጳስ የሳንባ ምች ሕመም (ኒሞኒያ) አጋጥሟቸው በሮም በሚገኘው በጌሜሊ ሆስፒታል እየታከሙ ይገኛሉ።
ቫቲካን እንዳስታወቀው ደም መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው ዝቅተኛ የፕላትሌት ቁጥር ስለነበራቸው ነው።
“የቅዱስ አባታችን ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ ነው” ያለው መግለጫው፣”ሊቃ ጳጳሱ አሁንም ከአደጋ ውጪ አይደሉም” ሲል አክሏል።
“ቅዱስ አባታችን ከትናንት በበለጠ የታመሙ ቢሆንም ቀኑን ሙሉ ንቁ ሆነው በወንበራቸው ላይ አሳልፈዋል” ሲል መግለጫው ያሉበትን ሁኔታ አብራርቷል።
የሮማው ሊቀ ጳጳስ ስለ ጤንነታቸው ሁኔታ በግልጽ እንዲነገር በመጠየቃቸው የተነሳ፣ ቫቲካን በየቀኑ መግለጫዎችን እየሰጠ ይገኛል።
የመግለጫዎቹ ይዘት እና ርዝማኔ የተለያየ በመሆኑ የተነሳ፣ አንዳንድ ጊዜ የጳጳሱ ደህንነት የሚከታተሉ ግለሰቦች በጥንቃቄ እያንዳንዱ መስመር ለመረዳት እንዲሞክሩ አድርጓቸዋል።
ይኹን እንጅ ይህ እስካሁን ከነበረው ልምድ በተለየ ፈጣን መረጃ የቀረበበት፣ ባልተለመደ ሁኔታ ዝርዝር መረጃዎችን የያዘ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ምንም ዓይነት ትንበያ ከመስጠትም ተቆጥቧል።
- ዓለምን የሚዞረው ኢትዮጵያዊ ከዩቲዩብ ምን ያህል ያገኛል?22 የካቲት 2025
- በተሰረቀበት ገንዘብ የተገዛ ሎተሪ አሸናፊ የሆነው ግለሰብ ሽልማቱን ከዘራፊዎቹ ጋር ለመካፈል ጠየቀ22 የካቲት 2025
- የሚደክምዎ እና ሰውነትዎ ድንገት የሚዝል ከሆነ ኃይል ለማግኘት የሚረዱ 5 ቀላል መፍትሄዎች22 የካቲት 2025
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ይህ የቫቲካን መግለጫ የተሰማው ሊቀ ጳጳሱን የሚያክሙ ዶክተሮች፣ ምንም እንኳ ሕመማቸው ውስብሰብ ቢሆንም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጣቸው መድኃኒት መስራት መጀመሩን ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው ።
አርብ ዕለት የሁኔታዎች ጥቂት ለውጥ “በቋፍ ያለውን ነገር” ሊያባብሰው ይችላል ሲሉ ተናግረው ነበር።
ከሕክምና ባለሙያዎቹ መካከል አንዱ እንደገለጸው “ጳጳስ ናቸው፤ ነገር ግን ደግሞ ሰው ናቸው”
ጳጳሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የካቲት 7/2017 ዓ.ም ሆስፒታል የገቡት ለበርካታ ቀናት የመተንፈስ ችግር ካጋጠማቸው በኋላ ነው።
በ21 ዓመታቸው የአንደኛው የሳንባቸው ክፍል እንዲወገድ በመደረጉ፣ በሳንባ አካባቢ በሚከሰት መቆጣት ምክንያት ለሳንባ ኢንፌክሽን በጣም የተጋለጡ ናቸው።
በ12 ዓመታት የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪነት ቆይታቸው፣ በመጋቢት 2023 (እኤአ) ለሦስት ሌሊት ብሮንካይተስ ታምመው መታከማቸውን ጨምሮ፣ ብዙ ጊዜ ሆስፒታል ገብተዋል።
በዓለም ዙርያ ያሉ የሊቀ ጳጳሱ የጤና ሁኔታን በቅርበት የሚከታተሉት የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ይህ ዜና ያስጨንቃቸዋል።
ይህ ዓመት ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሮም ብዙ ቁጥር ያላቸው ጎብኚዎች የሚጠበቁበት እና ለሊቀ ጳጳሱም ትልልቅ የዝግጅት መርሃ ግብር የሚይዙበት የክብረ በዓል ዓመት ነው።
ፖፕ ፍራንሲስ ከእንቅስቃሴ ተገድበው መቆየት የሚፈልጉ ግለሰብ አይደሉም።
በዚህ ሳምንት በሆስፒታል ውስጥ እንኳ ወደ ጸሎት ቤት ሄደው ይጸልዩ፣ ወንበራቸው ላይ ሆነው ያነብቡ እንደነበር ዶክተሮቹ ይናገራሉ።
ይህ ይኹን አንጂ ቫቲካን ከመታመማቸው አስቀድሞ ከምዕመናኑ ጋር በጋራ የእሁድ ፀሎት ለመሳተፍም ሆነ ለመምራት እንደማይታዩ ተናግራ ነበር።
ይህ ማለት በተከታታይ ለሁለተኛው ሳምንት በእንዲህ ዓይነት ስነስርዓቶች ላይ አይሳተፉም ማለት ነው።
ሳምንቱን በሙሉ ለጳጳሱ መልካም ጤንነትን የሚመኙ ሻማዎችን፣ አበባዎችን፣ እንዲሁም ደብዳቤዎችን የያዙ ግለሰቦች ሮም በሚገኘው ጌሜሊ ሆስፒታል ታይተዋል።
ቅዳሜ አመሻሹ ላይ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ምንም ዓይነት ለውጥ የነበረ ባይሆንም፣በአደባባዩ የሚያልፉ ሰዎችግን ዜናውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አንድ ጣሊያናዊ ለቢቢሲ እንደተናገረው “ሮም ውስጥ ከጳጳሱ ጋር በጣም ቅርብ መሆናችን ይሰማናል” ብሏል።
አክሎም “የአሁኑን መግለጫ አይተናል፣ እናም ተጨንቀናል።”