አቬራ መንግሥቱ ነጻ ወጥቶ ለእስራኤል ከመሰጠቱ በፊት በሐማስ ታጣቂዎች ታጅቦ
የምስሉ መግለጫ,አቬራ መንግሥቱ ነጻ ወጥቶ ለእስራኤል ከመሰጠቱ በፊት በሐማስ ታጣቂዎች ታጅቦ

ከ 1 ሰአት በፊት

ቅዳሜ ዕለት ሐማስ ባለፈው ዓመት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት ጊዜ አግቶ ከወሰዳቸው አራት ሰዎችን ጨምሮ ስድስት የእስራኤላውያን ታጋቾችን ለቅቋል።

ከተለቀቁት ታጋቾች መካከል በኖቫ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ታድመው ከነበሩት አራት እስራኤላውያን በተጨማሪ የተፈቱት ሁለት ግለሰቦች ቤተ እስራኤላዊው አቬራ መንግሥቱ እና ሂሻም አል ሰይድ ጋዛ ውስጥ ለዓመታት ቆይተዋል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቬራ መንግሥቱ በአውሮፓውያኑ ከ2014 እና ሻሂም አል ሰይድ ደግሞ ከ2015 አንስቶ ነበር በሐማስ ቁጥጥር ሥር የቆዩት።

በወቅቱ ሐማስ ሁለቱ እስረኞች የእስራኤል መከላከያ ኃይል አባላት ናቸው ቢልም የእስራኤል ባለሥልጣናት ሰነዶችን ያየው ሂውማን ራይትስ ዋች ግን ሁለቱም ከወታደራዊ አገልግሎት ውጪ የሆኑ ሲቪሎች ናቸው ብሎ ነበር።

እስራኤል አቪራ መንግሥቱን እና ሻሂም አል ሰይድን ለዓመታት ማስለቀቅ ሳትችል መቆየቷ በቤተሰቦቻቸው እና በሲቪል ቡድኖች ዘንድ ተስፋ መቁረጥ ፈጥሮ ቆይቷል።

ሐማስ ባለፈው ዓመት እስራኤል ውስጥ ዘልቆ በመግባት ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም ከ250 በላይ ሰዎችን አግቶ ወደ ጋዛ ከወሰደ በኋላ ግን የአቬራ ቤተሰብ የልጃቸውን ጉዳይ ዳግም በማንሳት የተለያዩ ዘመቻዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ጥላ ፈንታ አቬራን ለማስመለስ የሚደረገው ንቅናቄ መሪ ስትሆን በወቅቱ ለቢቢሲ “አቬራ መንግሥቱ የተሻለ ዕድል የሚኖረው አሁን ነው ብዬ አምናለሁ። ይሄን ስል በሐዘን ነው” ብላ ነበር።

እስራኤል አቬራ እና ሒሻምን ከሐማስ እስር አስለቅቃ ለዓመታት ማስመለስ አለመቻሏ እንደሚያሳዝናቸው ቤተሰቡ ይናገራል።

አቬራ መንግሥቱ ወደ ጋዛ የገባው በአውሮፓውያኑ 2014 ሲሆን፣ ላለፉት 10 ዓመታት ያህል በሐማስ ቁጥጥር ስር ቆይቷል።

3821 ቀን በእገታ ውስጥ ያሳለፈው አቬራ ሐማስ በ2023 በሕይወት መኖሩን የሚያሳይ ቪዲዮ እስኪለቅ ድረስ ያለበትን ሁኔታ ማንም አያውቅም ነበር።

አቬራ

አቬራ መንግሥቱ እንዴት ሐማስ እጅ ገባ?

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ከቤተ እስራኤላውያን ቤተሰቦቹ በአውሮፓውያኑ 1986 ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደው አቬራ መንግሥቱ በርካታ አይሁዳውያን ከኢትዮጵያ ከተወሰዱባቸው ምሥጢራዊ ዘመቻዎች መካከል አንዱ በሆነው ‘በዘመቻ ሶሎሞን’ ነበር ከኢትዮጵያ የወጣው።

ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ወደ እስራኤል በተከታታይ በተወሰዱበት ወቅት ከወላጆቹ እህት እና ወንድሞቹን ጨምረው ወደ እስራኤል ሲያቀኑ አቬራ የአምስት ዓመት ልጅ ነበረ።

እስራኤል ውስጥ አሽኬሎን በምትባለው ከተማ ውስጥ ከዘጠኝ እህት እና ወንድሞቹ ጋር ያደገው ኤቬራ መንግሥቱ፣ በጣም ይቀራረቡ የነበረው ታላቅ ወንድሙ ሚካኤል መንግሥቱ መሞትን ተከትሎ በእጅጉ ማዘኑን እና እራሱን ማግለል መጀመሩን ‘ኢዝራኤል ሃዮም’ ድረ ገጽ ዘግቧል።

አቬራ ራሱን ከሌሎች ከመነጠሉ በተጨማሪ ረጃጅም የእግር መንገዶችን በተለያዩ የእስራኤል ክፍሎች ውስጥ ያደርግ ነበር።

ከአስር ዓመት በፊትም በጀርባ የሚታዘል ቦርሳውን አንግቶ ከቤተሰቡ ቤት በመውጣት በጋዛ ሰርጥ እና በእስራኤል መካከል ወደተዘረጋው የደኅንነት ጥበቃ አጥር አምርቶ ነበር።

በስፍራው የነበሩ የእስራኤል ወታደሮች አቬራ የደኅንነት ቀጣናውን እንዳያልፍ ለማስቆም ቢሞክሩም እሱ ግን በአጥሩ ላይ በመንጠላጠል ወደ ጋዛ ሰርጥ ግዛት ዘሎ ገባ።

ወታደሮቹ አቬራ ከአፍሪካ የመጣ ስደተኛ እንጂ እስራኤላዊ መሆኑን ያወቁት የዜግነት መታወቂያውን ካገኙ በኋላ ነበር።

በሐማስ ቁጥጥር ሥር ወደ ምትገኘው ጋዛ ሰርጥ ሾልኮ የገባቸው አቬራ መንግሥቱ ከዚያ በኋላ ደብዛው ጠፍቶ ከቆየ አስር ዓመት ሊሞላው በተቃረበበት ጊዜ በጥር 2023 (እአአ) ሐማስ በሰራጨው ቪዲዮ ላይ ታየ።

ይህ አቬራ ጋዛ ውስጥ በሕይወት መኖሩን የሚጠቁም የመጀመሪያው ማስረጃ ሆነ።

በቪዲዮው ላይ ቤተ እስራኤላዊው “እኔ እስረኛው አቬራ መንግሥቱ ነኝ። እስከ መቼ ነው እዚህ የምቆየው? ከዚህ ሁሉ የስቃይ ዓመታት በኋላ የእስራኤል መንግሥት የት ነው ያለው? ከዚህ ስቃይ ማነው የሚያድነን?” የእስራኤል መንግሥት ካለበት ሁኔታ እንዲያወጣው የሚማጸን መልዕክት አስተላልፎ ነበር።

አቬራ በሐማስ ታጣቂዎች ታጅቦ

አቬራ መንግሥቱ ወደ ጋዛ በሄደበት ወቅት ዕድሜው 28 ዓመት የነበረ ሲሆን ቤተሰቦቹ መለቀቁን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የ38 ዓመት ልጃቸው “10 ዓመት ከአምስት ወራት ከግምት በላይ የሆነ ስቃይ ውስጥ ነበር የቆየው” ብለዋል።

አክለውም “በሕይወት እንዲመለስ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። ጸሎታችን፣ ምልጃችን እና ጥያቄዎቻችን እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ መልስ ሳያገኝ ቆይቶ ነበር” ብለዋል።

“ተወዳጁ ልጃችን፣ ወንድማችን፣ አጎታችን አቬራ” ተመልሷል፣ “ይህንን ጊዜ አንድታከብሩልን እና በእጅጉ የሚያስፈልገንን ሰላም እና እረፍት እንድትሰጡን እንጠይቃለን” ሲሉ የመገናኛ ብዙኃን እንዳይወተውቷቸው ጥሪ አቅርበዋል።

አቬራ ምንም እንኳ በፎቶ ላይ ሲታይ በጥሩ ጤንነት ላይ ያለ ቢመስልም፣ በሥነ ልቦና እጅጉን መጎዳቱን ከቤተሰቡ ጋር በተገናኘበት ወቅት አልፎ አልፎ ከሚያደርጋቸው ምልልሶች ይታይ ነበር ተብሏል።

የአቪራ ዘመድ የሆነው እና እንዲለቀቅ ለረዥም ዓመት ሲወተውት የነበረው ጊል ኤልያስ ለእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የአቪራ መንግሥቱ ወንድም ኢላን እና እህቱ “በተደበላለቀ ስሜት” ሲጠብቁት እንደነበር ተናግሯል።

“ከ10 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የሚያዩት፤ የተደበላለቀ ስሜት ነው ያላቸው” ነበር ያለው።

“እውነቱን ለመናገር ተዓምር ነው። . . . ኮከቦች ገጥመው ወደ ቤቱ ለመመለስ በቅቷል።”

የአቪራ ቤተሰቦች የእስራኤል መንግሥት ተደራድሮ ልጃቸውን እንዲያስለቅቅላቸው የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ለረዥም ጊዜ ተንከራትተዋል።

አንዳንድ የቤተሰብ አባላት የዘረኝነት ጥቃት ጭምር ማስተናገዳቸውን በወቅቱ ተናግረው ነበር።

ለአስር ዓመታት ጋዛ ውስጥ በሐማስ ቁጥጥር ስር የቆየው የኤቬራ መንግሥቱ ጉዳይ ከጋዛው ጦርነት መጀመር በፊት አንስቶ በእስራኤል መንግሥት ላይ ቀላል የማይባል ጫናን ያስከተለ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።

አቬራ ከተለቀቀ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ከአቬራ መንግሥቱ እና ከቤተሰቡ ጋር መነጋገራቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።

“ደስ ብሎኝ ነው የማቅፍህ፤ አጠቃላዩ የእስራኤል ሕዝብም እንደኔው ዛሬ በአንተ ነጻ መውጣት በእጅጉ ተደስተዋል” በማለት የተሰማቸውን መግለጻቸውን የእስራኤል መንግሥት ድረገጽ ላይ የወጣው ዘገባ ያመለክታል።

ይህ አሁን ለቤተ እስራኤላዊው አቬራ መንግሥቱ ከአስር ዓመታት እስር ነጻ መውጣት ምክንያት የሆነው ክስተት የተፈጠረው ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ማብቂያ ላይ ሐማስ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ነው።

ሐማስ በእስራኤል ውስጥ ባካሄደው ድንገተኛ ወረራ በአብዛኛው ሲቪሎች የሆኑ 1,200 ያህል ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሌሎች 251 ሌሎች ደግሞ ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።

እስራኤል በአጸፋው ለ15 ወራት በጋዛ ላይ ባካሄደችው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ አብዛኞቹ ሲቪሎች የሆኑ ወደ 50 ሺህ የሚደርሱ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።

አቬራ መንግሥቱ ከእስር የተለቀቀበት ስምምነት በእስራኤል መንግሥት እና በሐማስ በኩል በተደረሰ ስምምነት መሠረት እስራኤል በመቆዎቹ የሚቆጠሩ እስረኛ ፍልስጤማውያንን እንዲለቅ፣ ሐማስ ደግሞ በእጁ ያሉትን ታጋቾች እንዲያስረክብ በተደረሰ ስምምነት ነው።